May 11, 2019

Source: https://fanabc.com


አዲስ አባባ፣ ግንቦት 3፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሃውቲ አማጽያን የሁዴይዳ  ወደብን ለቀው መውጣት መጀመራቸው ተገለፀ።

የየመን ሃውቲ አማጽያን ሃይሎች በዛሬው ዕለት የሁዴይዳ ሳሌፍ ወደብን ለቀው መውጣት መጀመራቸውን  ሬውተርስ የአይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

እንደ አይን እማኞች ዘገባ  አማጽያኑ በሁዴይዳ ሳሌፍ  የሚገኙ የተለያዩ ጦር መሳሪያዎቻቸውን ከቦታው ማስወጣት ጀምረዋል።

ይህም በየመን ለአራት  አመታት የቀጠለውን  የእርስ በርስ ጦርነት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመቋጨት የሚያስችል መሆኑ ተስፋ ተጥሎበታል ።

የአማጽያኑ ከቦታው መውጣት ተከትከሎም በአካባቢው የሚገኙ የባህር በር ተባቂዎች አማጽያኑ ለቀውት የወጡትን ቦታ መቆጣጠራቸው ተነግሯል።

በስፍራው የሚገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሙያዎችም በቦታው የነበረው የጦር መሳሪያ በሙሉ መውጣቱን በማረጋገጥ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

በየመን የተባበሩት መንግስታቱ ድርጅት ተልዕኮ  ጥዋት ላይ  ባወጣው መግለጫ  የሃውቲ አማጽያን ከዛሬ ጀምሮ ሶስት ወደቦችን ማለትም ሁዴይዳ፣ ሳሌፍ እና ራስ ኢሳ ወደቦች ለቀው እንደሚወጡ ማስታወቁ ይታወሳል።

በየመን ለአራት አመታት የዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭት በርካታ ዜጎችን ለህልፈት ሲዳርግ ፥ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ዜጎችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉን መረጃዎች ያሳያሉ።

ምንጭ፦ሬውተርስ