May 12, 2019

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ከሰሞኑ በክልላዊና ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአብመድ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ በቆይታቸው የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ መነሻና መድረሻ የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ መቀረጹን ተናግረዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ለውጥ መነሻውንና መዳረሻውን የሚያሳይ በጽሑፍ የተዘጋጀ ፍኖተ ካርታ የለውም የሚል ትችት በተደጋጋሚ ሲሰነዘር ሰንብቷል፡፡ ፍኖተ ካርታው ለውጡ የደረሰበትን ደረጃ በደንብ የሚተነትን እና በቀጣይ የሚደርስበትን ደረጃ አቅጣጫ የሚያሳይ በመሆኑ ሰነዱን ከማዘጋጀት ባለፈም በሚገባ ተደራጅቶ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ይህ ሰነድ ለውጡ ከሚፈለግበት ደረጃ ለማድረስ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ የታመነበት ሲሆን በቅርቡ የኢህዴግ ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ተወያይቶ እንዳጸደቀውም ዶክተር አምባቸው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

ሰነዱን በኢህዴግ ምክር ቤት ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሕዝቡ አውርዶ ማወያየትና የተሰማውንም ሐሳብ እንዲሰጥበት ማድረግ እንደሚቻልም አስታውቀዋል፡፡ በርግጥ ከሕዝቡ ፍላጎትና ጥያቄ አንጻር ከፍተኛ ዳተኝነት ቢስተዋልም በድርጅቱ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚከናወነው ማንኛውም የአመራር ሥርዓት በተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ላይ ተመሥርቶ መሆን እንዳለበምት ነው የተናገሩት፡፡ በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ በቅድሚያ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የፖለቲካ አመራሮች በፍኖተ ካርታው ይዘት ዙሪያ ዕውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡ የክልሉ መሪ ድርጅት አዴፓም ይህንን ኃላፊነት ወስዶ በፍጥነት ወደ ሕዝቡ እንዲደርስ ማድረግ ስለሚጠበቅበት በተቻለ ፍጥነት እንደሚሠራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ፍኖተ ካርታውን የተዘጋጀው በድርጅት ቢሆንም መንግሥትም በተለየ አግባብ ተቋማዊ አድርጎ ለተግባራዊቱ መሥራት እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡ የሰነዱ ዋና ዓለማው ሀገራዊ አንድነትን ማምጣትና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማስጠበቅ እስከሆነ ድረስ የድርጅትም ሆነ የመንግሥት ተቋማት እንቅስቃሴያቸውን በተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ልክ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡