May 13, 2019
BBC Amharic

የኢትዮጵያ መንግሥት 13 የስኳር ፋብሪካዎችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለመሸጥ ማስታወቂያ ካወጣበት ቀን ጀምሮ ብዙ የሀገር ውስጥና የውጪ ድርጅቶች እየተመዘገቡና ፍላጎታቸውን እየገለጹ እንደሆነ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ወዩ ሮባ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአውሮፓውያኑ 2016/17 በወጣ መረጃ መሠረት በሃገሪቱ ያሉ ሁሉም ፋብሪካዎች 4 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር የሚያመርቱ ሲሆን ሃገሪቱ የሚያስፈልጋት ግን 7 ሚሊየን ኩንታል ነው።
መንግስትም ይህንን ክፍተት ለመሙላት 4.1 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ከውጪ በማስገባት ሲያከፋፍል ቆይቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሀገር ውስጥ ምርቱን ወደ 40 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ በማሰብ መንግሥት ተጨማሪ 10 ስኳር ፋብሪካዎችን መገንባት ጀምሮ ነበር። የግንባታ ሥራውን ያከናውን የነበረው ሜቴክ ግንባታውን በታሰበለት ጊዜ ማጠናቀቅ ባለመቻሉ መንግሥት ለተጨማሪ ወጪ ተዳርጓል።

ፋብሪካዎቹን መሸጥ ለምን አስፈለገ?
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ አንስቶ ብዙ ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶችን ለግል ባለሃብቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የመሸጥ ሃሳብ ደግሞ አንዱ ነው።
ሃገሪቱ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ ስለነበረችና የተከማቸ የረጅም ጊዜ ብድር መክፈል አለመቻሏ ለዚህ ውሳኔያቸው ገፊ ምክንያት እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑትና በቤልጂየም የዶክትሬት የምረቃ ጥናት ወረቀታቸውን በዚሁ ጉዳይ ላይ እየሰሩ የሚገኙት አቶ ተሾመ ተፈራ እንደሚሉት መንግሥት በሁለት ምክንያቶች ፋብሪካዎቹን ለመሸጥ ተገዷል።
የመጀመሪያው ምክንያት አብዛኛዎቹ ፋብሪካዎች በብድር ስለተገነቡ ግንባታቸው ገና ሳይጠናቀቅ የመክፈያ ጊዜያቸው መድረሱና መንግሥት በቂ የሆነ የውጪ ምንዛሪ ስለሌለው ለተጨማሪ ወጪ ተዳርጓል። ይህ ደግሞ ፋብሪካዎቹን ለመሸጥ አስገድዶታል ብለው ያምናሉ አቶ ተሾመ።
ባለሙያው በሁለተኛነት ያስቀመጡት ምክንያት መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፋብሪካዎቹ ተሸጠው የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መፈለጉን ነው።
አቶ ተሾመ አክለውም በረጅም ጊዜ ውስጥ ፋብሪካዎቹን ወደ ግል ማዘዋወሩ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ፋብሪካዎቹ በአጭር ጊዜ ማምረት ጀምረው ከሃገር ውስጥ ፍላጎት ያለፈ ጥቅም ሊኖራቸው ስለማይችል ከሽያጩ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይችላል።
በረጅም ጊዜ ደግሞ ወደ ውጪ ከሚላከው ስኳር የውጪ ምንዛሪ ማግኘት እንደሚቻል ይናገራሉ።
ኬንያዊው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶክተር ቶኒ ዋቲማ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ፈጣን የሚባል ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች ነው በማለት የስኳር ፋብሪካዎችንም ሆነ ሌሎች የመንግሥት ድርጅቶችን ወደግል ከማዘዋወር ጋር በተያያዘ የኬንያን ተሞክሮ ሲያብራሩ፤ በዘርፉ የሚፈጸሙ የሙስናና የበጀት ምዝበራ ለመቆጣጠርና ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ የግል ባለሃብቶች በማንኛውም መልኩ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ከመቆጠብ ባለፈ ተገቢውን አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ማድረስ ይችላሉ።
መንግሥት እነዚህን ፋብሪካዎች ወደ ግል ባለሃብቶች ሲያዘዋውር ለግንባታና ሥራ ማስኬጃ በብድርም ሆነ ከካዝናው የሚመድበውን ገንዘብ ሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ ለማዋል እንደሚያግዘው ቶኒ ዋቲማ ይናገራሉ።
የኬንያ ተሞክሮም በዚሁ የተቃኘ እንደሆነ አክለዋል።
ከሽያጩ በኋላ የመንግሥት ሚና ምንድነው?
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ወዩ ሮባ እንደሚሉት ፋብሪካዎቹ ወደ ግል ባለሃብቶች ሲዘዋወሩ እንዴት መተዳደር አለባቸው የሚለውን በተመለከተ አዲስ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው።
ሥርጭትና ሌሎችን በተመለከ ደግሞ ወደፊት ውሳኔ የሚሰጥባቸው እንደሆነና ዋጋን በተለመከተ ግን መንግሥት ሳይገባበት በነጻ ገበያው መርህ መሠረት የሚወሰን ይሆናል ብለዋል።
አሁን ባለው አሰራር፣ መንግሥት የስኳር ሥርጭትን በሚቆጣጠርበት ጊዜ፣ እንኳን ነጋዴዎች ስኳሩን በመደበቅ ዋጋ ጨምረው ይሸጣሉ። መንግሥት በስኳር ዙሪያ ያለውን ተሳትፎ እጅጉን ሲቀንስ ደግሞ ተመሳሳይ ተግባሮች እንዳይበራከቱ ስጋት አለ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ተረፈ ግን የግል ባለሃብቶች ዋጋውን መቆጣጠራቸውን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ነው የሚያዩት። ምክንያቱም ይላሉ፤ ባለሃብቶች ቁጥራቸው በርከት ስለሚልና ከፍተኛ የገበያ ውድድር ስላለባቸው የስኳሩን ዋጋ ዝቅ ማድረጋቸው አይቀርም።
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ወዩ ሮባም በዚሁ ሀሳብ ይስማማሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ፋብሪካዎቹን ወደግል ባለሃብቶች ከማዘዋወሩ በፊት የአሰራር ህግና ደንቦቹ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የኬንያው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ቶኒ ዋቲማ ይናገራሉ።
ይህን ማድረገም የተጠቃሚዎችን መብት ለማስከበር፣ የሸንኮራ አቅራቢ አርሶአደሮችን ጥቅም ለማስጠበቅና የገበያ ሁኔታውን ለመከታተል ይጠቅመዋል ብለዋል።
በተጨማሪም ባለሃብቶቹ ትርፍ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ስለሚችሉ የምርት ጥራትን የሚቆጣጠር ጠንካራ ተቋም መቋቋም እንዳለበት ሃሳብ ሰንዝረዋል።
“የኬንያ አርሶአደሮች የተወሳሰበውን የዓለም ገበያ ሁኔታ መከታተልና መረዳት ስለማይችሉ ጠንካራ የአርሶአደሮች ማህበር ተቋቁሞላቸዋል፤ መብታቸውን ማስከበር የሚችልና ከዘመኑ አሰራር ጋር መራመድ የሚችሉ የህግ ባለሙያዎችም በማህበሩ ውስጥ አሉ።” ሲሉ ያብራራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ከምርት በኋላም የማከፋፈል ሥራውን የሚሰሩት ሌሎች ማህበራት ናቸው። ይህ ደግሞ አምራቾች ገበያውን ሙሉ በሙሉ እንዳይቆጣጠሩት ለማድረግ ይረዳል።
ይህን የኬንያውያንን ተሞክሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ከግምት ውስጥ ሊያስገባው እንደሚገባም ቶኒ ዋቲማ ይመክራሉ።
ከዚህ በፊት በነበሩት ተሞክሮዎች የተለያዩ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ለግል ባለሃብቶች ቢሰጡም ግልጽነት ባለመኖሩና ተገቢው የጥንቃቄ እርምጃዎች ባለመወሰዳቸው ስኬታማ እንዳልነበሩ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ተሾመ ያስታውሳሉ።
ከውጪ የሚመጡ ድርጅቶች ፋብሪካው ከሚያወጣው በላይ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ይወስዱና ለአጭር ጊዜ ሰርተው ብድሩን ሳይመልሱ ፋብሪካዎቹን ትተው ካገር ይሸሹ ነበር።
ስለዚህ መንግሥት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ከግምት ውስጥ ማስገባት የማይችል ከሆነ አሁንም ለከፍተኛ ኪሳራና ስኳር እጥረት ሊዳረግ እንደሚችል ባለሙያው ያሳስባሉ።
► መረጃ ፎረም – JOIN US