ከኢዜማ ጀርባ ያሉ እጆች ሲፈተሹ

***ወንድወሰን ተክሉ***

መነሻበቅርቡ የአድስት ድርጅቶችን ህልውናን አክስሞ እንደተመሰረተ የተነገረን ሙሉ በሙሉ የዶ/ር አቢይ መራሹ መንግስት ፕሮጄክት ነው የሚል መረጃ የደረሰኝ ከቀናት በፊት ቢሆንም ተጨማሪና አጠናካሪ የሆኑ መጋቢ መረጃዎችን እስክጨማምር ድረስ መረጃውን ለህዝብ ለማቅረብ አልቻልኩም ነበር፡፡ ዶ/ር አቢይ በሀገሪቷ ውስጥ ያለውን ቁጥር ስፍሩ የበዛውን ድርጅት ጨፈላልቆ አንድ ጠንካራ ሀገር አቀፍ ታማኝ የተቃዋሚ ድርጅት ለመፍጠር ካላቸው ቅን ፍላጎት የተነሳ ረዥም ጊዜ የወሰደባቸውን ኢዜማን የመፍጠር ሀሳብን ከመውለድ ጀምሮ እስከ እውን ማድረጊያውን የፋይናንስ፤ሎጀስቲክስ፤የሞራልና የመረጃም ድጋፍ በመስጠት የድርጅቱን መመስረት ማብሰር ችለዋል ይላል የደረሰኝ መረጃ፡፡

መረጃው አያይዞም የኢዜማ ዋና ዓላማና ተግባራትም

-1ኛ ታማኝ ተቃዋሚ ሆኖ በህብረብሄር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን እያሰባሰበ መሪ በመሆን እንዲቆጣጠር

2በሀገራዊ ድርጅት ስር ታቅፈው በመንቀሳቀስ የሚታወቁትን እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የብሄርተኝነት ቅኝት እየተቀኙ በመደራጀት ላይ ያሉትን እንደ የአማራውን ህዝብ ዓይነቶቹን ፍላጎት ያማላል ያሉትን ኢዜማን በማቅረብ ማቀፍ
3
በአሁኑ ሕገ መንግስት ስር ከጎሳ ተኮር ውጪ ህብረ ብሄር ድርጅቶችም ተጠናክረው መገኘት እንዲችሉ ታስቦበት ነው በማለት ይገልጽና ለዚህ መንግስታዊ ፕሮጄክትና ሀሳብ የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መራሹ አግ7 ብቁ እጩ ሆኖ በመገኘቱ ተስማምቶ እንዲሰራ ተደርጓል ይላል፡፡የመንግስት እጅ በተቃዋሚው ጎራ ውስጥ መጠን ባለፈ ደጋፊነትም ሆነ ጨቋኝነት ሚና ጣልቃ ሲገባ በሀገሪቱ ውስጥ ለመገንባት የሚፈለገውን መሰረቱ ጠንካራ የሆነ እውነተኛ ዴሞክራሲን ምኞትና ፍላጎት ክፉኛ እንደሚያጨልመው ይጠበቃል እንጂ የዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት ደረጃ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ስለማይገመት እንዴትና ለምንስ ማለቴ አልቀረም፡፡

ሆኖም የዶ/ር አቢይ እጅ ወደ ተቃዋሚው ጎራ በወዳጅነት መንፈስ ተለሳልሶ በመግባት ስራ ሲሰራ ይህ ኢዜማን የመፍጠር ሁኔታው የመጀመሪያው እንዳልሆነም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ጠምሩ በተቃዋሚው ጎራ ውስጥ ገብተው ከፈጸሟቸው ተግባራቶች ውስጥ አንዱ በመንግስት ተቺነቱ የታወቀውን ኢሳት ሚዲያ ተቋምን ለሁለት እስከመሰንጠቅ ያበቁ ሲሆን ተቋሙ እሳቸው ባለፈው ዓመት አሜሪካንን በሚጎበኙበት ወቅት ከኢሳት ውስጥ እጅግ የበሰሉ እንደ ሲሳይ አጌና አይነቱ ጋዜጠኞች ብለው አቋማቸውን ከገለጹበት እለት ጀምሮ በተቋሙ ጋዜጠኞች መካከል በእሳቸውን ደጋፊና እሳቸውን ተቃዋሚና ተቺ መካከል በመክፈል ሲያነታርክ ከቆየ በኃላ ሰሞኑን ይህንኑ ተቋም በግምቦት ሰባት በኩል ለመቆጣጠር የተደረገውን ውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴንም ፈጥሮ ዋሽንግተን ያሉት ጋዜጠኞች አዲስ አበባ፣አመስተርዳምና ሎንደን ካሉት በፊት ቀድመው ድርጊቱን በመቃወም መግለጫ እንዲያወጡ እንዳደረጋቸውም ይታወቃል፡፡

የዶ/ር አቢይ ወዳጃዊ እጅ በኢሳት ውስጥ የፈጠረውን ክፍፍል ለጊዜው ላቁመውና ወደተነሳሁበት የኢዜማን አፈጣጠር እንዴትና ከምን አንጻር ለሚለው ግላዊ ጥያቄዬም ጭምር መልስ ይሆናል ብዬ ከተለያዩ ምንጮች ያሰባሰብኩትን እንደሚከተለው አቀርባለሁ

**ኢዜማ የዶ/ር አቢይ አእምሮ ውልድና የመንግስት ፕሮጄክት ነው

ኢዜማ በ2018 ተጽንሶ በ2019 የተወለደ ህብረብሄራዊ ድርጅት ወይም ድርጅቱ እራሱን እንደገለጸው የዜግነት ፖለቲካን የሚያራምድ ፓርቲ ሲሆን ለዚህ ፓርቲ እውን መሆን እንደ አባት የድርጅቱን ሀሳብ አፍላቂው ዶ/ር አቢይ ሲሆኑ እንደ እናት ይህንን የዶ/ር አቢይን ሀሳብ ተቀብለው እውን እንዲሆን ያበቁት የአግ7 አመራርና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ናቸው፡፡

ሀሳቡ የተጸነሰው በ2018 በምንሊክ ቤተመንግስት ውስጥ በዶ/ር አቢይና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መካከል ምስጢራዊ ውይይት (ማለትም ለህዝብ ይፋ ያለተደረገ ውይይት ማለቴ ነው)ወቅት እንደተጸነሰ ይነገራል፡፡ በወቅቱ አቶ አንዳርጋቸው ከእስር የተፈቱበት ወቅት ሲሆን ዶ/ር አቢይ ግልጽ በግልጽ ከአግ7 ድርጅት ጋር በጋራ መስራት እንደሚፈልጉ ለአቶ አንዳርጋቸው ነግረው ይህንንም ለድርጅቱ መሪ ለዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር መክረው ለተግባራዊነቱ እንዲዘጋጁ በመንገር ያሰናብቱዋቸዋል፡፡

እዚህ ላይ የዶ/ር አቢይ በግንቦት ወር 2018 ላይ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ «የአግ7 ድርጅት ከእኛ ጋር እንዲሰራ እፈልጋለሁ» ብለው ምስጢራዊ ጥያቄን እንዲያቀርቡ ያደረጋቸውና ያደፋፈራቸውን ተደጋጋፊ ክስተቶችን እና ድርጊቶችን ስንፈልግ የምናገኘው የአቶ ሌንጮ ለታን ስምና የዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ስም ሆኗል፡፡

/ር አቢይ ገና ለኦህዴድ ሊቀመንበርነት ሳይበቁና የድርጅቱ ጸሃፊ ሆነው ግን ድርጅታቸው ኦህዴድ ከህወሃት ጋር እልህ አስጨራሽ ትግልና ትንቅንቅ በሚያደርግበት በ2017 መገባደጃ ላይ የአግ7 ከፍተኛ አመራርና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አንድ ምስጢራዊ ግምገማና አቃም በህወሃት መራሹ መንግስት ላይ ወስዶ ነበር፡፡ ይህም በ2017 የተወሰደውና ለህዝብም ሆነ ለአጠቃላይ አባላቱ ይፋ ያልተደረገው የአግ7 ግምገማና አቋም እንደሚከተለው

1እንደ አግ7 እምነት የኢህዴድ ድርጅት ሙሉ በሙሉ የለውጥ ኃይል መሆኑና የሚታመን ድርጅት መሆኑን ይገልጽና በምስጢር አብሮ መስራት እንዳለበት ይደንግጋል

2የብአዴንን ድርጅት አመራሩን የለውጥ ኃይል ብሎ ይገልጽና ሆኖም አብዛኛውን ድርጅታዊ ይዘቱን ህወሃት የምትቆጣጠረው ስለሆነ አብሮ ለመስራት የተመቹ አይደሉም ሲል ይገልጻቸዋል

3የደቡብ ህዝቦችን ድርጅት ከህወሃት ጋር በአቻነት በመፈረጅ እነዚህ ኃይሎች በሀገሪቱ ውስጥ የተነሳውን ህዝባዊ ለውጥ ጥያቄ የሚያዳፍኑ አደገኛ ኃይሎች በማለት ያስቀመጣቸው ሲሆን ይህም የአግ7 ምስጢራዊና ድርጅታዊ አቋም በወቅቱ ለአቶ ለማ መገርሳ መራሹ ኦህዴድ እንዲደርሰው ተደርጎ ከእነ አቶ ለማም እጅግ አበረታታች መልስ እንደተሰጠው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የመጋቢት 2018 የኢህአዴግ ድርጅታዊ መሪ ምርጫን በዶ/ር አቢይ አሸናፊነት እንደተጠናቀቀና ዶ/ር አቢይም ቃለመሃላ ፈጽመው ስልጣን ሳይጨብጡ የአግ7 መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በቪ ኦ ኤ ላይ ቀርበው «እኛ የምንታገልለት ለውጥ በእኛ ብቻ ይምጣ አንልም፡፡ ማንም ያምጣው ማን ለውጥ እስከመጣ ድረስ ድርጅታችን ይቀበላል፡፡ በዚህም ምክንያት እኔ ከዶ/ር አቢይ መራሹ መንግስት ጋር እንዳልሰራ የሚያግደኝ ምንም ነገር እንደሌለ ነው እምረዳውና አብሬ ለመስራት ዝግጁ ነኝ» ሲሉም ገልጸው ነበር፡፡

ይህንን ተከትሎም ከሁሉም ተቃዋሚዎች በፊት ቀድመው ወደ ሀገር ቤት የገቡት የአቶ ሌንጮ ለታና ድርጅታቸው ኦዴግ ሲሆን አቶ ሌንጮ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ጉባኤ ተብሎ ሲነገር በነበረው ድርጅት ውስጥ ከአግ7 ጋር አብረው የሚሰሩ በነበረበት የ2017ቱ የኦህዴድ/ብአዴን እና የህወሃት ግብግብ ወቅት ከእነ አቶ ለማ ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆኑ ወሳኝ የሆነ የምክር ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አብዛኛው የዲያስፖራ ህዝብ በአቶ ሌንጮ የሚመራው ኦዴግ ከማንም ቀድሞና እነ አግ7 ያሉበትን ሀገራዊ ጉባኤን ጥሎ ወደ ሀገር በገባበት ወቅት ከሀዲ አግ7 ከዳ እያለ በሚጮህበት ወቅትና ዶ/ር ብርሃኑም ወደ አደባባይ ወጥተው «አቶ ሌንጮ እንደሚሄዱ አልነገሩንም» እያሉ በሚመልሱበት ወቅት አቶ ሌንጮ ለታ ግን አዲስ አበባ ላይ አጠቃላይ የሀገራዊ ጉባኤን እና በተለይም የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መራሹ አግ7 ጋር ዶ/ር አቢይ የሚሰሩበትን መንገድ ሲያመቻቹ እንደነበረና ይህንንም ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሲነገራቸው እንደነበረ ነው አሁን አሁን መረጃዎች እየገለጹ ያሉት፡፡

እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ዶ/ር አቢይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ፈትተው ቤተመንግስት በመጥራት «እኔ ከእናንተ ድርጅት አግ7 ጋር ለመስራት እፈልጋለሁ» በሚል ሀሳባቸውን እንዲገልጹላቸው እንዳስቻለ የሚገመት ሲሆን ሃላም ላይ ወደ አሜሪካ ባቀኑበት የ2018ቱ ሀምሌ ወር ላይ ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ተገናኝተው ምስጢራዊ ስምምነትና መተማመንን ገንብተው በመግባታቸው የዶ/ር ብርሃኑ ነጋን «እኔ ዶ/ር አቢይ ወደ ዴሞክራሲ ያሸጋግሩናል ብዬ 100% አምናቸዋለሁ » ብለው ሲናገሩ እንድንሰማ አድርጎናል፡፡

**የኢዜማ ዋና ዓላማ ምንድነው ??

መንግስታዊ ፕሮጄክት የሆነው ኢዜማ ዋና ዓላም ከጠም ፍጹም በጎነትና ቅንነት የተነሳ ለዴሞክራሲ ግንባታ የሚያስፈልገውን ጠንካራ ተቃዋሚ ለመፍጠር ነው ተብሎ የተገለጸውን ያህል ጠንካራ ግን ታማኝ ተቃዋሚ የሚለው ሀረግ ግን የተነገረውን ቅንነትና በጎነትን የሚያፈርስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ሀገሪቷ ህብረብሄራዊ የሆነ ጠንካራ ድርጅት እንደሚያስፈልጋት የማይካድ ቢሆንም ታማኝ የሆነ የሚለው ቃል ግን የሚመሰረተው ህብረብሄራዊው ጠንካራ ድርጅት ታማኝነቱ ለተቋቋመበት ፕሮግራም፤ዓላማና ለህዝብ ሳይሆን ለኦዴፓ መራሹ መንግስት የሚሆን በመሆኑ ለሀገርና ለህዝብ ሊያበርክት ከሚችለው አስተዋጽኦ ይልቅ ስልጣን ላይ ላለው ገዢ ፓርቲ የሚያደርገው አስተዋጽኦ የሚበልጥ ሆኖ በመገኘቱ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚገነባው ምህዳሩ የሰፋ ዴሞክራሲ እውንነት ሳንካ በመሆን አንጻር ያሰጋል እንጂ የሚያስደስትና የሚደገፍ ሂደት አይደለም፡፡

ሌላው በዚሁ የኢዜማ መመስረት ዓላማ ውስጥ እንዲከውናቸው ከታሰቡለት ውስጥ አንደኛው የሆነው የአማራን ብሄርተኝነትን የመከላከል ተግባር የሚለው ዓላማ በአማራው ህዝብ ላይ የተከፈተን ጥቃት ለነገዱ ብሄርተኝነት መፈጠር መንስኤ መሆኑን ያላገናዘበ እቅድ በመሆኑም የኢዜማን አካሄድ በበጎ እንዳይታይ ያደርጋል፡፡

የአማራን ብሄርተኝነትን ለመከላከል ህዝቡ ሀገር ወዳድ ስለሆነ በዜግነት ፖለቲካ የሚንቀሳቀስ ህብረብሄራዊ ድርጅት ፈጥረን እናቅርብለት ከማለት ይልቅ እየደረሰበት ያለውን በደልና ጥቃት በማስቆምና ብሎም የህዝቡን ሰላም ደህንነትና ተፈጥሮአዊ ህልውናዊ መብቱን በህግ ማእቀፍ የተረጋገጠ በመጠበቅ እንጂ የአማራን ህዝብ ስነልቦናን ያገናዘበ ህብረብሄር ድርጅት በማቅርብ ባለመሆኑ የኢዜማን አመሰራረታዊ ዓላማን ውጤታማ ለማድረግ የሚያዳግት እንዲሆን ያደርገዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡

የጠምር ዶ/ር አቢይ እውነተኛና ልባዊ ዓላማና ፍላጎት በእርግጥም ቅንነትን መሰረት በማድረግ በተቃዋሚው ጎራ ያለውን የመዝረክረክና በጥቃቅን ጎሳተኮር አደረጃጀት ተደራጅቶ ያለውን ሁኔታ ለመቅረፍ እሳቤ አድርጎ የተጸነሰ ሊሆን ቢችልም የኢዜማ ዋና ተዋናይና መሪ ሆኖ የወጣው የግምቦት ሰባት ድርጅትና መሪው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና የኢዜማ አመራሮች ከጠምሩ የተለየና ግላዊ የሆነ ዓላማና ፍላጎትም ሊኖራቸው ስለሚችል ድርጅቱ የጠምሩን ቅን የተባለውን ፍላጎት ተግብሮ ለማሳየት የሚሳነው ስንኩል እንደሚሆን ነው ሁኔታዎች እሚያሳዩት፡፡

የሆነው ሆኖ ዶ/ር አቢይ ከሚመሩት መንግስት ባሻገር የተቃዋሚውን ጎራ የማጠናከር ስራ ውስጥ መዘፈቃቸውም በራሱ የተለየ እድምታና ሁኔታ ስላለው ለዛሬው በዚሁ ጽሁፌን ደምድሜ የኢሳትን በሌላ መጣጥፌ እንደማቀርብ እየገለጽኩ ልሰናበት፡፡

ከፊስቡክ የተወስደ