ተሳታፊዎች

ቢቢሲ በየወሩ የሚያዘገጀውና ‘ቢቢሲ ወርልድ ኩዌስችንስ’ የተባለው አለማቀፍ የክርክር መድረክ ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ተካሂዶ ነበር። ከ200 በላይ ታዳሚያን በተገኙበት ዝግጅት ፖለቲከኞች፣ ተንታኞችና የማህበረሰብ አቀንቃኞች ተሳታፊዎች ነበሩ።

የክርክር መድረኩ ዋነኛ ማጠንጠኛ ሃሳብ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድና ባለፉት 12 ወራት ይዘውት የመጡት ለውጥና እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች ላይ ነበር። ከ100 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ እስካሁንም ለምን መረጋጋት ተሳናት ሲል የመድረኩ አዘጋጅ የነበረው ጆናታን ዲሞቢልቢ ጠይቋል።

በመድረኩ ከተገኙት መካከል ደግሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ኦማር፣ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና፣ የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጸዳለ ለማ እንዲሁም እስክንድር ነጋ ይጠቀሳሉ።

የዐቢይ ለውጥ፡ በመስቀለኛ መንገድ ላይ?

ተስፋዬ ገብረአብ ስለ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ምን ይላል?

ከተሳታፊዎች የመጣው የመጀመሪያ ጥያቄ ደግሞ እውን ጠቅላይ ሚኒነስትር ዓብይ አህመድ ኢትዮጵያን የበለጸገች፣ ሰላማዊና የተረጋጋች ሃገር ማድረግ ይችላሉ ወይ? ነበር።

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት የጀመሩት የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ኦማር ነበሩ። ” በአሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ተረድቶ ወደተሻለ ስፍራ ሊወስዳት የሚችል መሪ ከአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የተሻለ ሰው ሃገሪቱ ታገኛለች ብዬ አላምንም።” ብለዋል።

በጥላቻና መጠራጠር ተሸብቦ የነበረን ህዝብ ወደ ፍቅርና አንድነት ማምጣት እጅግ ከባድ ፈተና ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የማይቻል አይመስለኝም በማለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሃገሪቱን ወደተሻለ ከፍታ ለመውሰድ ከባዱ ፈተና የሚሆንባቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ራሳቸው የሚመሩት ኢህአዴግ ነው ብለዋል።

” ብዙዎቹ የፓርቲው አባላት ለለውጥ የተዘጋጁ አይደሉም፤ ጠቅላዩ ከሚያመጧቸው የለውጥ ሃሳቦች ጋርም አብረው መጓዝ አይችሉም። አሁንም ቢሆን ፈጣን ለውጥ ማምጣት የማይችሉ ከሆነ ህዝቡ መጠየቅ ይጀምራል።”

ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን እየተከተሉት ባለው አካሄድ ሃገሪቱን ወደ ብልጽግና ይመሯታል ብዬ አላስብም በማለት ተከራክሯል።

” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥ ለማምጣት የመረጡት መንገድ የተሳሳተና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚመራ ነው።” ብሏል።

ጋዜጠኛ ጸዳለ ለማ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈተናዎች ከሁለት አቅጣጫዎች እንደሚመነጩ ታስረዳለች። ”ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥና ብልጽግና ሊመጣ የሚችለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የሚመሩት ፓርቲ ራሱን ፈትሾ ለለውጥ ሲዘጋጅና በብሄር ፖለቲካ ሲገዳደል የነበረው ህዝብ ይቅር ለመባባል ሲዘጋጅ ነው” ብላለች።

ተሳታፊዎች

ሌላኛው ተሳታፊዎቹን ያከራከረ ሃሳብ በብሄር ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል ወይስ አያስፈልጋትም የሚለው ጥያቄ ነበር።

በዘር የተከፋፈለውና መስማማት የማይችለው የተማረው ሃይል ራሱን ለመቀየርና ልዩነቶቹን አጥብቦ አብሮ ለመስራት እስካልተዘጋጀ ድረስ ምንም አይነት ለውጥ ሊመጣ አይችልም የሚሉት ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በደንብ ከታሰበበት ፌደራሊዝሙ በራሱ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብለው ያምናሉ።

እስክንድር ነጋ በበኩሉ ከሶስት ሚሊየን በላይ ሰዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆነው ፌደራሊዝሙ ነው፤ አሁንም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዙሪያ አልተሳካላቸውም ብሎ የተከራከረ ሲሆን የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ኦማር ግን ተቃራኒ ሃሳብ አላቸው።

”ከዚህ በፊትም ቢሆን በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ይፈናቀሉ ነበር። ነገር ግን ይህን ያክል ሰዎች ተፈናቅለዋል ብሎ እንኳን ማውራት አይቻልም ነበር። አሁን ግን ሌላው ቢቀር በነጻነት ስለተፈናቃዮቹ ማውራት ጀምረናል” ብለዋል።

አክለውም ”በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሳው ግጭት ሙሉ በሙሉ ሃገሪቱ አልተረጋጋችም ለማለት በቂ አይደለም። ህዝቡ የተቃውሞ ሰልፍ ለመውጣት ፍራቻ አለመሳየቱ በራሱ የሚያሳየው ነገር አለ። ሁሌም ቢሆን ለውጥ ሊመጣ ሲል መንገራገጭ ያለ ነው።”

”መረሳት የሌለበት ሌላኛው ነገር በሃገር ውስጥ የሚፈናቀሉት እንዳሉ ሆነው ለውጡን ለመደገፍና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ወደሃገር ቤት የተመለሱትስ? ” በማለት አቶ ሙሰጠፋ ሃሳባቸውን አጠናክረዋል።

የክልል እንሁን ጥያቄ እዚህም እዚያም?

የለውጡ ጎዳና እስከየት?

የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅም በመድረኩ ብዙ ሃሳቦችን ያንሸራሸረ ጉዳይ ነበር።

ረቂቅ አዋጁ የጥላቻ ንግግር ትርጉም ብሎ ሲያስቀምጥ “ሆን ብሎ የሌላ ግለሰብን፣ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማህበረሰብን ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ፆታን አካል ጉዳኝነትን ዜግነትን፣ ስደተኝነትን፣ ቋንቋን፣ ውጫዊ ገፅታን መሰረት በማድረግ ሆነ ብሎ እኩይ አድርጎ የሚስል የሚያንኳስስ፣ የሚያስፈራራ፣ መድልዎ ወይም ጥቃት እንዲፈፀም የሚያነሳሳ ጥላቻ አዘል መልዕክቶችን በመናገር፣ ፅሁፍ በመፃፍ፤ በኪነ ጥበብ እና እደ ጥበብ፣ የድምፅ ቅጂ ወይም ቪዲዮ፣ መልእክቶችን ብሮድካስት ማድረግ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨትን” እንደሚመለከት ይገልጻል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንደሚለው ኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግር ህግ ያስፈልጋታል። ነገር ግን አተረጓጎሙ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬና ስጋት አለኝ ብሏል።

”ልክ የጸረ ሽብር ህጉ የመናገር ነጻነትን እንደገደበው ሁሉ ይሄኛውም ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።”

ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ደግሞ የጥላቻ ንግግር ህጉ አሳሳቢ ነው በማለት ጀምረዋል። ”ምክንያቱም ህግ ተርጓሚው አካል በነጻነትና ሙሉ መረጃዎችን ይዞ መስራት የማይችል ከሆነ አሁንም ቢሆን ህጉ በተሳሳተ መልኩ ሊተረጎም ይችላል።”

ጋዜጠኛ ጸዳለ ለማ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ በመንግስት መፍረድ ከባድ ነው ብላለች ”በቀላሉ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የሚችሉ አጋጣሚዎች በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጩ የተሳሳቱና ግጭት በሚያስነሱ መልእክቶች ብቻ ለብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል።”

ነገር ግን የህጉ አተገባበር ላይ አሁንም ቢሆን ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ትስማማለች።

የክርክር መድረኩ ከላይ ከተጠቀሱት ሃሳቦች በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የተለያዩ የመንግስት ድርጅቶችና ፋብሪካዎችን ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደግል ባለሃብቶች ለማዘዋወር ያቀረቡት ሃሳብ እንዲሁም በቀጣይ ሊደረግ ስለታሰበው ምርጫ ውይይት ተደርጓል።