May 14, 2019

Source: https://fanabc.com/

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 19 ኛው ዓለም አቀፍ የወጪንግድ ፎረም በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።

የኢፌዴሪ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና ዓለም አቀፉ የንግድ ማዕከል ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር 19 ኛውን ዓለም አቀፍ የወጪንግድ ፎረምን በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት ተስማምተዋል።

ስምምነቱንም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር እና ዓለም አቀፉ የንግድ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኤራንቻ ጎንዛሌዝ ተፈራርመውታል።

በስምምነቱ መሰረትም 19 ኛው ዓለም አቀፍ የወጪንግድ ፎረም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከህዳር 18 እስከ 22 ቀን 2019 ድረስ በአዲስ አበባ የሚካሄደ ይሆናል።

በፎረሙም ከ1 ሺህ በላይ የቢዝነስ መሪዎች ፣ፖሊስ አውጪዎች እንዲሁም የተለያዩ የንግድ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፎረሙ የሚካሄደውም በአፍሪካ ኢንዱስትሪ ሳምንት ወቅት ሲሆን፥ ይህም በአፍሪካ አህጉር ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማስተሳሰርና ለማበረታታት ያስችላል ነው የተባለው።

ፎረሙ በአፍሪካ ተግባራዊ በሚደረገው የነፃ ንግድ እንቅስቃሴ እና ቢዝነስ ዙሪያ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም የተለያዩ የቢዝነስ ሰዎች ሃሳብ የሚለዋወጡበት፣የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች የሚሰጡበት እና የተለያዩ የንግድ ስምምነቶች የሚፈፀሙበት እንደሚሆን ይጠበቃል ።

በተጨማሪም ፎረሙ ወጣቶችን ለተለያዩ አዳዲስ የስራ ፈጠራዎች የሚያበረታቱ ስልጠናዎች የሚሰጡበት እና አዳዲስ የቢዝነስ አማራጮች የሚተዋወቁበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።