May 15, 2019
Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 7 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲሱ የስርአተ ትምህርት ክለሳ የኢትዮጵያን ህዝብ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በሚዳስስ መልኩ ሲካሄድ የነበረው የታሪክ መማሪያ መጽሐፍት ዝግጅት መሰረዙን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሚኒስቴሩ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው እንዳሉት፥ አሁን ላይ የሚሰጠው የታሪክ ትምህርት ፖለቲካዊ እይታው ይበዛል።
ይዘቱም የተመረጡ የፖለቲካ ትርክትን ብቻ ማቀፉ የህዝቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ እሴትን ዘንግቷል ብለዋል።
ይህም ተማሪዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክ በተዛባ መንገድ እንዲረዱ በማድረጉ አካባቢያዊ አስተሳሰቦች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗልም ነው ያሉት።
ባለፉት 7 ዓመታት የኢትዮጵያ የታሪክ ትምህርት መጽሐፍትን ለመከለስ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው፥ በክለሳ ሂደቱ የታሪክ ምሁራንን በማሳተፍ ከተጠናቀቀ በኋላ የተወሰኑ የብሔር ልሂቃን ባለመስማማታቸው መሰረዛቸውን ተናግረዋል።
በዚህም አሁን እየተቀረጸ ላለው የስርዓተ ትምህርት ክለሳ አወዛጋቢ እየሆነ የመጣው የታሪክ ትምህርት በልዩ ትኩረት እንዲሰራም ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የታሪክ ምሁር ዶክተር ተፈሪ መኮንን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያን ያለ ታሪኳ ማሰብ እንደማይቻል ጠቅሰዋል።
አያይዘውም ከዚህ ቀደም የታሪክ ትምህርትን መንግስት ካለመቀበሉም ባሻገር አማራጭ የታሪክ ሰነድና አተያይ ባለማዘጋጀቱ ጉዳቱን የከፋ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ፥ ታሪክ መማሪያ ብቻ መሆን ሲገባው በእኛ ሀገር ግን ያ አልሆነም ብለዋል፤ መንግስት በታሪክ ላይ እጁን ማስገባቱን በመጥቀስ።
የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት በሀገሪቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት በሰነድ ተዘጋጅቶ ለትውልዱ እንዲደርስ መደረጉ በኢትዮጵያ ታሪክና በዜጎቿ ላይ ትልቅ ኪሳራ ማስከተሉንም ዶክተር አልማው አንስተዋል።
ታሪክን በስነዜጋ ለመተካት መሞከሩን ያነሱት ዶክተር አልማው መንግስት ታሪክ ሳይሆን ቴክኖሎጂን እናስተምር በሚል ያዘጋጀው የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ብዙ ውድቀት ማስከተሉንም ይናገራሉ።
የስርዓተ ትምህርት ዳይሬክተሩ አቶ እሸቱ፤ የታሪክ ትምህርት ይዘት፣ የትምህርቱ አቀራረብ፣ አካታችነት ጉድለት እንዳይኖረው እየተፈተሸ ነው ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።
ለዚህም የኢትዮጵያን ታሪክ በጥልቀት ለመፈተሽ የሚያስችሉ የቅድመ ጥናት ፕሮጀክቶች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው ትምህርት ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያነሱት።
የኢትዮጵያን ትክክለኛ ታሪክ ለማዘጋጀትና ለሁሉም የትምህርት ደረጃዎች የሚሰጡ የትምህርትና የማጣቀሻ መጽሐፍትን ለማዘጋጀት መታቀዱንም ገልጸዋል።
በይዘቱም የጥንታዊት ኢትዮጵያ፣ መካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያ፣ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ፣ ከፖለቲካና ሌሎች ጉዳዮች አኳያ በጥልቀት ተፈትሸው እንዲደራጁ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።Filed in:Uncategorized