May 16, 2019
Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን አክስመው በመዋሃድ የመሰረቱት ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የመስረታ ጉባዔ ተካሄደ።
የመስራች ጉባዔው በፓርቲው ፕሮግራም ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ የፓርቲው አመራሮች ምርጫ አካሂዷል።
በመስራች ጉባኤው ላይ የኢህአዴግን ጨምሮ የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካይ ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም የኢትዮጵያን ህዝብና አመለካከት መሰረት ያደረገ ውህደት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የተሻለ ስኬት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተነግሯል።
በሀገር ውስጥ እና በውጭ በተናጠል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን አክስመው ነው ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን የመሰረቱት።
ፓርቲዎቹ ለበርካታ አመታት በብሄራዊና ክልላዊ ማዕቀፍ ሲታገሉ የነበሩ ሲሆን፤ የተፈጠረውን የዴሞክራሲ ምህዳር መስፋትና ሃገራዊ ለውጥ ተከትሎ ጥያቄዎቻቸውንና ፍላጎቶቻቸውን ሊያስተናግድ የሚችል ያሉትን “ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኅብር ኢትዮጵያ)” የተሰኘ አዲስ ውህድ ፓርቲ ለመፍጠር ላለፉት 8 ወራት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
ውህዱን የፈፀሙት ፓርቲዎችም የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት(ሽግግር)፣ ኢትዮጵያችን ህዝባዊ ንቅናቄ (ኢትዮጵያችን)፣ ቱሳ የኢትዮጵያ ትንሳዔ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(ቱሳ)፣ የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት(ኦህዲኅ)እና ደቡብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኮከቦች ቅንጅት(አረንጓዴ ኮከቦች) ናቸው።
በለይኩን አለም