May 17, 2019

Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ስደተኞችን የሚመለከት አዲስ ዕቅድ ይፋ አደረጉ።

ትራምፕ ትናንት ማምሻውን እንዳስታወቁት፥ ከዚህ በኋላ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች የተማሩ፣ ወጣቶች፣ እንግሊዝኛን መናገር የሚችሉ እና የሚሰጣቸውን የስነዜጋ ፈተና የሚያልፉ መሆን አለባቸው።

እንዲሁም አብዛኛዎቹ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች በቤተሰብ አማካኝነት እንደሚመጡ ጠቅሰው፥ ይህንን የማስቀረት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ትራምፕ ትናንት በኋይት ሃውስ በሰጡት መግለጫ ሀገራቸው በቤተሰብ ላይ ተመስርታ ስደተኞችን መቀበሏ ዕውቀትን እንድትገፋ እያደረጋት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

በየዓመቱም የመኖሪያ ፍቃድ ከሚሰጣቸው 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ሰዎች ውስጥ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት በቤተሰብ አማካኝነት ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ዕውቀትን መሰረት ባደረገ መልኩ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ስደተኞች 12 በመቶ እንደነበሩ ጠቅሰው፥ በአዲሱ እቅድ ወደ 57 በመቶ እንደሚያሳድጉትና አስፈላጊ ከሆነም ከፍ ሊያደርጉት እንደሚችሉ አንስተዋል።

አዲሱ ዕቅድ በትራምፕ ከፍተኛ አማካሪና በልጃቸው ባል ጃሬድ ኩሽነር እንዲሁም በሌላኛው ወግ አጥባቂ አማካሪያቸው ስቴፈን ሚለር የተዘጋጀ ነው።

ሆኖም ዕቅዱ በዴሞክራቶችና የስደተኞችን መብት በተመለከተ በሚሰሩ ተቋማት ጠንካራ ተቃውሞ እየቀረበበት ይገኛል።

አዲሱ የትራምፕ እቅድ ስራ ላይ ለመዋል ኮንግረሱን በተቆጣጠሩት የታችኛው የዴሞክራት አባሎች መጽደቅ ይኖርበታል።

ምንጭ፦ቢቢሲ

በአብርሃም ፈቀደ