May 17, 2019
Source: http://ethiodigest.org

በመቅደስ አስራት May 17, 2019
ተስፋና ስጋት!
በዚህ ሳምንት ግንቦት 7 እና 8 እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ በኢትዮጵያ ኤምባሲና በ US Department of State በተዘጋጀው “Ethiopian Partnerships Forum” የመገኘት ዕድል ገጥሞኝ ነበር:: የዝግጅቱ ዋና ዓላማ በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን፦ አሜሪካዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶችን መዋዕለ ነዋያቸውን ኢትዮጵያ ላይ እንዲያፈሱ በኢንቨስትመንትና በፕራይቬታይዘሽን እንዲሳተፉ ለማበረታታ የታቀደ ነው! ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የመንግስት ተቋማትን ወደ ግል ዘርፍ የማዛወር እንቅስቃሴ ስታደርግ የመጀመሪያዋ ባይሆንም መንግስት እስከአሁን ትልልቅ የተባሉ ተቋማትን አንቆ በበላይነት ሲያስተዳድርና ሲመራ መቆየቱ ይታወቃል::
አሁን በሀገሪቱ በነበሩ የተለያዩ ቅራኔዎችና ህዝባዊ አመጾች ጋር ተያይዞ የኢህአዴግ መንግስት በህዝብ ግፊት ተገዶ ካደረገው ለውጥና ከዶ/ር አብይ አህመድ መመረጥ ጋር ተያይዞ መጥቷል ከተባለው አዲስ ለውጥ ጋር በተያያዘ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ እንደ ኢትዮ-ቴሌኮም፦የስኳር ኮርፐሬሽንና ሌሎችም ትልልቅ የሀገሪቱ ኩባኒያዎች ወደ ግል በከፊልና በሙሉ እንደሚተላለፉ እንዲሁም አዳዲስ ተፎካካሪ ኩባኒያዎች ወደ ሀገር ውስጥ በብዛት እንዲገቡ እየተበረታቱ እንደሆነ እየተመለከትን ነው:: ይህ የመነቃቃት መንፈስ በአግባቡ ከተተረጎመ ከህዝባችን ቁጥር ወደ 70% ገደማ የሚሆነውን ወጣት የሰው ሀይል ወደ ስራ ለማሰማራትና የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ለማረጋጋት እንደሚጠቅም እሙን ነው::
ተስፋ
ከጉባኤው የአሜሪካን መንግስትና በሀገሪቱ ያሉ ተቋማት በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ በጉጉትና በተስፋ ትኩረት ሰጥተው እንደሚከታተሉና በትልልቅ የንግድ ዘርፎች ላይም የሀገራቸው ባለሃብቶች እጃቸውን እንዲያስገቡ ትልቅ ጉጉት እንዳላቸው በግልጽ ይስተዋላል። ሌላው ከጉባኤው እንደ ትልቅ ተስፋ የተመለከትኩት ጉዳይ ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊያን በቴክኖሎጂ፦በሀይል አቅርቦትና በተመሳሳይ ትልልቅ ዘርፎች ላይ ያላቸውን እውቀት፦ልምድና ነዋይ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ለማሻገር ያላቸውን ጉጉት ነው። ትውለደ ኢትዮጵያዊያኑ በዚህ ሀገር እጅግ ግዙፍ በሆኑ ትልልቅ ጉባንያዎች በመሪነት ደረጃ የሚሰሩና በሞያቸውና በእውቀታቸው እጅግ የላቁና የተከበሩ የራሳቸው የግል ዘርፎችን አቋቁመው በዚህ ሀገር ተወዳድረው ሰርተው ውጤታማ ሆነውም የተፈተኑ መሆናቸውን ለማየትና ለመስከር እድል አግኝቻለሁ። ሀገራችን በምታደርገው የኢኮኖሚ ሽግግር ለትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ የሰጠችው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ነው። የህዝባችንን ባህላዊና የእምነት እሴት በተሻለ መልኩ የሚረዱት እነዚህ ኢትዮጵያዊ አሜሪካኖች በተለየ መልኩ ትኩተት ተሰጥቶ መበረታታቸው በኢትዮጵያ ለሀገራችንና ለህዝባችንም ከፍተኛ ጥቅም አለው። በዚህ ዘርፍ ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉ የዜግነትና ተመሳሳይ ጉዳዮችንና ፓሊሲዎችን በፍጥንቶ አሻሽሎ ኢትዮጵያ ባለማወቅና በድንቁርና ምክኒያት የገፋቻቸውን ልጆችዋን ነዋያቸውንና ዕውቀታቸውን የምትጠቀምበትን ሁኔታ ማመቻቸት ብልህነት ነው። የነበረውን የገፊነት የፓለቲካ አስተዳደራዊ መዋቅርና የአሰራር ባህልን በቁርጠኝነት ቀይሮ ስርዓቱን በዕውቀት፦ በግልጽ አሰራርና በተጠያቂነት ላይ የመመስረትና ሀገርና ትውልድን የመቀየር ተነሳሽነቱ ከንግግርና ጉጉት የተሻገረና ቁርጠኝነት የሚታይበት ሊሆን ይገባል። አሁን የሚስተዋለው የሀገሪቱ ያልተረጋጋ የኢኮኖሚ ሁኔታ የኑሮ ውድነትና የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ቁርጠኝነት አማራጭ ሳይሆን ሀገራችንን እንደ ሀገር የማቆየት ብቸኛው አማራጭ ነው።
የሚመጡት የኢንቨስትመንት እድሎች ስራን ይዘው መምጣታቸው የሚያጓጓ ጉዳይ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም በዚህ ረገድ ለሀገራችንና ለህዝባችን ዬትኞቹ ባለሀብቶች ቢመጡ ዘላቂ ጠቀሜታ ይኖረዋል? በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ባለሀብቶች ምን ዓይነት ትኩረት ማግኘት አለባቸው? እና የመሳሰሉት ጉዳዮች በሂደቱ ትኩረት ማግኘት ይኖርባቸዋል። ባለገንዘብ ሁሉ ህዝባችንንና ሀገራችንን፦ ባህላችንንና ሀይማኖታዊ እሴቶቻችንን ይጠብቃል ለህዝባችንም ከእጅ ወደ አፍ ባለፈ ተስፋ ይሰጣል ማለት አይደለም። ባለንበት በዚህ ዘመን የባህል፦ የሃይማኖት፦ የራስን አስተሳሰብ እንዲሁም ድህነትና ባርነትን ህዝብ ላይ ለመጫን የመርዝ ጭስና ከባድ መሳሪያ አሰልፎ የሚመጣ ወራሪ አይኖርም። የዘመኑ አድዋ ከገንዘብ ጋር ተግተልትሎ የሚመጣውን የባህል የእሴት የሃይማኖትና የአስተሳሰብ እንዲሁም የዘመናዊ ባርነት ሂደት ለመቋቋምና ለመዋጋት ጉልበትንና ዕቅቀትን አቀናጅቶ በብልህነትና ቁርጠኝነት ለመዋጋት መዘጋጀት ነው:: በዚህ ረገድ ሃላፊነት የተሞላበት አካሄድ ከመንግስትም ከኢትዮጵያዊ ባለ ሃብቶችም ከሚመለከተው ሁሉ ንቃትና ቆራጥነት ይጠበቃል::
በጉባኤው ከመንግስት ተወካዮች የቀረበው የሰራተኞች አስተዳደርን የሚመለከት ፓሊሲ በኢትዮጵያ መንግስት እየተቀረጸ መሆኑን የጠቆመው ክፍል ትኩረቴን ስቦታል። ሰራተኞቹ በብዛት ኢትዮጵያውያን የሚሆኑበት የኢንዱስትሪና የእድገት ጎዳና ለኢትዮጵያዊን ተስፋን እንጂ ዘመናዊ ባርነትን ብቻ ይዞ እንዳይመጣ ፓሊሲዎቹን መፈተሽ መመርመርና ህዝባችን በአግባቡ የሚገባውን በሚያተርፍበት ሁኔታ መቀረጻቸውን ማረጋገጥ በዋናነት የመንግስት ሃላፊነት ቢሆንም በዚህ ረገድ ጉዳዩን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅርብ መከታተልና ፓሊሲዎቹን ለውይይት እያቀረቡ ማስረዳት መረዳትና መፈተሽ እንዲሁም የሚታረሙ ጉዳዩችም ካሉ ማሳየትና አቅጣጫ ማመላከት ተገቢ ነው።
ለውጥ ለኢትዮጵያ አማራጫ ሳይሆን የመኖርና ያለመኖር ግዴታ ነው!
የጉባኤው አስተባባሪዎች ከባድ ጥያቄዎችን ጠይቁ የሚል ግብዣ ልብን የሚያስደስት ክስተት ነበር:: በመሆኑም ታዳሚዎች ቁልፍ የተባሉ ጥያቄዎችን ለመንግስት አካላትም ለዉጡን እየደገፉ ላሉ የአሜሪካ መንግስት አካላትም ለአወያዮች በሙሉ ሰንዝረዋል። አንኳሮቹ ጥያቄዎች የሚያጠነጥኑት በሀገሪቱ የዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ መፈናቀል፦ ከቦታ ወደ ቦታ በሰላም ተዘዋውሮ የመስራት ሁኔታ አስፈሪ መሆን፦ በተለያዩ ተቋማት የሚደርስባቸው ጥቃትቶች ጋር ተያይዞ ያለው ጉዳይ አሳሳቢነት የሚገኙበት ሲሆን ሌላው መንግስት በሀገሪቱ ላሉ ፕሮጀክቶች የሰጠው የትኩረት ቅደም ተከተል መዛነፍ እጅግ እንዳሳሰባቸው ታዳሚዎች ገልጸዋል። የሃይል አቅርቦት ለኢንቨስትመንት በመረታታት ከፍተኛ ሚና እንዳለው እየታወቀ የህዳሴ ግድብን የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከማስጨረስና በዚያ ከሚገኘው ነዋይ ሌሎችን ፕሮጀክቶች ከመቅረጽ ይልቅ መንግስት የአ/አበባ ከተማን ለማስዋብ በሚል ከፍተኛ ገንዘብ ለማፍሰስ ቅድሚያ መስጠቱ የፕሮጀክቱ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የቅደም ተከተል መዛነፍ በከፍተኛ ሁኔታ ይስተዋላል የሚሉ ቅራኔዎች ቀርበዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሳው ነጥብ የህዳሴው ግድብ የውሃ ምንጭ የሆነው የጣና ሃይቅ የአረም ችግር ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ባለበት በዚህ ወቅት ምንም ዓይነት ትኩረት ከመንግስት አለመሰጠቱ እጅግ እንዳሳሰባቸው ትውለደ ኢትዮጵያዊያኑ ተሰብሳቢዎች ጠቁሟል። ሀይል በሃገራችን ከህክምና አገልግሎት ጀምሮ እጅግ በብዙ ዘርፎች እያስከተለ ያለው ችግር ከምንም በላይ ትኩረት ማግኘት ይገባዋል። የሀገሪቱ ትኩረት በቴክኖሎጂና በኢንቨስትመንት ላይ ባተኮረበት በዚህ ሰዓት ዋና ከተማይቱን አዲስ አበባን ጨምሮ በትልልቅ ከተሞች ጭምር ሳይቀር የመብራት አቅርቦት ማግኘት ከፍተኛ ችግር እየሆነ መምጣቱ ግልጽ በሆነበት ሁኔታ መንግስት የፓሮጀክቶቹን ቅደም ተከተሎች መገምገምና መቅደም ያለበትን ማስቀደም እንደሚገባው መጠቆም የግድ ነው።
ሌላው ከፍተኛ ገንዘብ ያላቸው የውጪ ሀገር ኩባኒያዎች ወደ ሀገራችን እንዲገቡ ማበረታታቱ እንዳለ ሆኖ በጥቃቅን ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ሀገር በቀል ባለሃብቶችን ማበረታታትና እንዳይዋጡ መጠበቅ ተገቢ ነው። የግል የፋይናንስ ተቋማቶችን ጨምሮ ሌሎችም የንግድ ዘርፉ ተሳታፊ ኢትዮጵያዊያን ሃብታቸውንና እውቀታቸውን ከትውልደ ኢትዮጵያዊ ባለሃብቶች ጋር አቀናጅተውና ተቀራርበው በመስራት በዚህ በፍጥነት ከመጣ የኢኮኖሚ ሽግግር ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል ማመቻቸት ተገቢ ነው። ኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶች መተማመንና መቀራረብ አብሮ ተቀናጅቶ መስራትን በፍጥነት መልመድ ካልቻሉ በሌሎች ትልልቅ የውጭ ሀገር ኩባኒያዎች የመዋጥ እጣ እንደሚገጥማቸው ሊረዱ ይገባል። ትልልቆቹ የውጪ ሀገር ኩባንያዎች አንዱ ብቻ ከፈለገ ሁሉንም የሀገሪቱን ሃብት የመዋጥ አቅም እንዳለው ልብ ብለን ከሰፈርና ጠባብ አስተሳሰብ የተላቀቀና ዓለም የደረሰችበትን ሁኔታ የሚያማትርና በአንድነት ቆሞ እጣ ፈንታውን ከመነጠቅ የሚያድን ተወዳዳሪ ኢትዮጵያዊ ባለሃብትና ሰራተኛ ማዘጋጀት የመንግስትና የሃላፊነት የሚሰማው ወገን ሁሉ ግዴታ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት በፓለቲካ አስተዳደር ብልግና ምክኒያት በሀገር ደረጃ ሀገራዊ ሃብዋን አሰቃቂ በሆነ መልኩ በገዛ ልጆችዋ የተዘረፈች መሆኑ ግልጽ ነው። ሀገራችን በዚህ ረገድ ያላትን የስህተት ጫፍ አሟጣ የተጠቀመችና ይሄ የተጠራቀመ ስህተት ኢኮኖሚያዊና ሀገራዊ ጉልበትን በአጠቃላይ ያራደና ያዋለለ አሁን ለወደቅንበት የፕሮጀክቶች ፍዘትና ስራ አጥነት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ጭምር የዳረገን ትልቅ ችግር እንደመሆኑ መጠን የተሰጠው ትኩረት መደብዘዝ ደግሞ ፊታችንን በጥርጣሬ ሞልቶታል።
በጉባኤው አወያይ የነበሩ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ዶ/ር አርከበንና አምባሳደር ፍጹም አረጋን ጨምሮ ትልልቅ የለውጡ ተሿሚ ባለስልጣናት ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች፦እድሎች እንዲሁም የመንግስትን የለውጥ ቁርጠኝነት ለታዳሚዎች ለማረጋገጥ ያደረጉት ጥረት ጥሩ ነበር። እንደ አንድ የሀገሩን ጉዳይ በአንክሮ እንደሚከታተል ግለሰብ የተሰማኝ ቅሬታ ግን ወደ ሀገሪቱ በእርዳታና በብድር ከአበዳሪ ሀገራትና የዓለም ባንክን ጨምሮ ከሌሎች ዓለማቀፍ ተቋማት ተገኝቶ የነበረው በብዙ ቢሊዮን የሚገመት እርዳታና ብድር ተመዝብሮ ከሀገር መውጣቱን በተመለከተ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ምንስትር ዶ/ር አብይ የለውጡ ሃይል እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ቢገልጹም ምንም ተከታታይ ስራና ግልጽ የሆነ ተስፋ አለመኖሩ እንዲሁም በዚህ ጉባኤም ሆነ በሌሎች ተመሳሳይ ትልልቅ መድረኮች ይሄንና የሀገር ሰላምና ጸጥታን የመሳሰሉ አንኳር የሀገሪቱ ጉዳዮች ተድበስብሰው እንዲታለፉ የሚሆንበት አካሄድ በንግግርና በተግባራዊ ቁርጠኝነት መሃከል ያለውን ክፍተት እያጎላ ጥርጣሬዎችን እንዲቀጥሉ እንዳያደርግ ስጋቴን አጋራለሁ። ኢትዮጵያ ከምንም ግዜ በላይ በሙስናና በሀገር ምዝበራ ዙሪያ እንዲሁም በዜጎች ሰላም ዙሪያ ቁርጠኛ አቋም ያለው አመራር ትሻለች። በብዙ ስህተቶች መሃከል የዋለለው ህዝቧም ከጥርጣሬ ተገላግሎ በሚደረገው ሁሉ በሙሉ ልቡ እንዲሳተፍ፦ከጥርጣሬ የሚጠብቁ ግልጽና አስተማማኝ አሰራሮችን ለማየት ይሻሉ።ማንኛውም ወደ ሀገራችን የሚመጣ ባለሃብትም ይህንን መረጋጋት ከምንናገረው ብቻ ሳይሆን ከነባራዊ ሁኔታዎች ሳያጣራ ሰባራ ሳንቲሙን ስለማያመጣ በዚህ ረገድ አፍረጥርጦ መነጋገርና መፍትሄ ማበጀት እንጂ አደባብሶ ማለፍ የሚመከር አካሄድ አይደለም።
እናም በቁርጠኝነትና ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ የተገቡትን ተስፋዎችና አንኳር ጉዳዮች በተግባር በመተርጎም ላይ መንግስት እንዲያተኩር ዜጎችም ይህ እንዲሳካ ከእኔ ምን ይጠበቃል ወደሚል ልቦና እንዲመለሱ ተመኘሁ። እውነተኛ ለውጥ ለኢትዮጵያ አማራጫ ሳይሆን የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው!
ዝግጅት ክፍሉ:- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልፃለን!Filed in:Uncategorized