ሰልፍ ተካሄደ
May 17, 2019
Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 9 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የወላይታ ህዝብ ክልል የመሆን ጥያቄው ይመለስ በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ።
ሰላማዊ ሰልፉ በወላይታ ሶዶ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፥ የወላይታ ዞን ራሱን በክልል የማስተዳደር መብቱ ይከበር ዘንድ የተጠየቀበት ነው።
በሰልፉ የወላይታ ህዝብ የክልል ጥያቄ ይመለስ፣ ሀገራዊ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የህግ የበላይነት ሊከበር ይገባል፣ ከአጎራባች ህዝቦች ጋር አለመግባባት እንዲፈጠር ያደረጉ አካላት በህግ ይጠየቁ፣ የመልማት ጥያቄያችን ይመለስ የሚሉና መሰል መፈክሮች ተንፀባርቀዋል።
የዜጎች ሰርቶ የመኖር መብት እንዲረጋገጥም መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበሩ ላይ ሰፊ ስራ እንዲሰራም ጠይቀዋል።
የወላይታ ህዝብ ሀገር ወዳድ መሆኑን ያነሱት ሰልፈኞቹ ኢትዮጵያ የሁሉም ቤት በመሆኗ ዜጋን ማፈናቀል እንዲቆምም ነው የጠየቁት።
ሰልፈኞቹ በተጨማሪም ያልተመለሱ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻችን ይመለሱ የሚል ጥያቄንም አንግበዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳገቶ ኩምቤ በበኩላቸው የዞኑ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ አንስቶ በዞኑ ምክር ቤት መፅደቁን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጅ ወደ ቀጣይ ሂደት ሳይሸጋገር መቆየቱን አንስተው ጥያቄው ህገ መንግስታዊ መልስ ሊያገኝ ይገባዋል ብለዋል።
በሰልፉ በርካታ የብሄሩ ተወላጆች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ወጣቶችና ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን፥ ሰልፉ ያለምንም ችግር በሰላም ተጠናቋል።
በጥላሁን ሁሴን