22 ሜይ 2019

ዛሬ የዓለም የብዝሀ ሕይወት ቀን ‘Our Biodiversity, Our food, Our Health’ በሚል መሪ ቃል ታስቦ ይውላል። ኢትዮጵያም ቀኑን ‘ብዝሀ ሕይወት ሀብታችን፣ ምግባችን ጤናችን’ በሚል ታከብራለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ “የሰው ልጆች ሕይወት መሰረት የሆነውን ብዝሀ ሕይወት እንጠብቅ” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
ብዝሀ ሕይወት የሰው ልጆች ምግብ፣ ጤና ባጠቃላይም የህልውና መሰረት እንደመሆኑ፤ ከፍተኛ ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተለይም የአካባቢ ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ የመላው ዓለም ስጋት መሆናቸውን ተከትሎ የብዝሀ ሕይወት ጥበቃ የዓለም መሪዎች መወያያ አጀንዳም ሆኗል።
በኢትዮጵያ የብዝሀ ሕይወት ሀብት ላይ የተጋረጡ ፈተናዎች የትኞቹ ናቸው? ስንል የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማርዮን ጠይቀናል።
1. የከተማ መስፋፋት
ዶ/ር መለሰ እንደሚሉት፤ በዋነኛነት በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ያለው የከተማ መስፋፋት ነው።
የከተማ መስፋፋት ብዝሀ ሕይወት የሚገኝባቸው አካባቢዎችን ከማጥፋቱ ባሻገር፤ የሕዝብ ቁጥር መጨመሩ ለእጽዋት መመናመን ምክንያት ሆኗል።
“ሰዎች የሚመገቧቸው እጽዋት የሚገኙባቸው አካባቢዎች እየጠፉ መጥተዋል” የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከሁለት ዓመት በፊት የተሠራ ጥናት፤ በየዓመቱ 92ሺህ ሄክታር ደን እንደሚወድም ማሳየቱን ያጣቅሳሉ።
የሕዝብ ቁጥር መጨመር በተለያዩ ፓርኮች ለሚከሰቱ ሰደድ እሳቶች ምክንያትም ነው። በተያያዥም የከተማ መስፋፋት የእጽዋትና እንስሳትን ህልውና አደጋ ውስጥ ከትቷል ይላሉ።
2. መጤ ዝርያዎች
‘ወራሪ’ የሚባሉ ዝርያዎች የኢትዮጵያ የብዝሀ ሕይወት ሀብት እንዲመናመን ምክንያት ሆነዋል።
“በምስራቅ ደቡብ ኢትዯጵያና በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ወደ 1. 8 ሚሊየን ሄክታር ቦታ ይዘዋል። የውሀ አካላትን እያጠፋ ያለው የእምቦጭ አረምን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል” ይላሉ ዶ/ር መለሰ።
መጤ ዝርያዎች፤ እጽዋትና አዝርእት የሚመረቱበት የእርሻ መሬትን ስለተቆጣጠሩ የቀድሞ ሀገር በቀል ምርቶች እየጠፉ ነው።
“ነባር ዝርያዎችን እያጣን ነው። ለምሳሌ እኔ ያደግኩበት ደጋ አካባቢ የነበረው እንጀራ ጣዕምና ሽታም እየተቀየረ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኙ የነበሩ መድሀኒትነት ያላቸው ምግቦችም አደጋ አንዣቦባቸዋል። እንደምሳሌ የሚጠቅሱት ላይዚን የሚባል አሚኖአሲድ የያዘ የገብስ ዝርያን ነው።
እሳቸው እንደሚሉት ከ70 እስከ 90 የሚሆኑ ነባር ዝርያዎች ጠፍተዋል።
• ”የተፈጥሮ ሃብታችንን ለመጠቀም የማንንም ይሁንታ አንጠብቅም”
3. የአየር ንብርት ለውጥ
የመላው ዓለም ራስ ምታት የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ የኢትዮጵያም ችግር ነው።
ዛሬ ዛሬ ቆላ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ወደበረሀነት እየተቀየሩ ስለመጡ ቀድሞ የሚበቀሉ እጽዋት እየጠፉ መምጣታቸውን ዶ/ር መለሰ ይናገራሉ።
የአየር ንብርት ለውጥ በቤትና በዱር እንስሳት ላይም ተጽእኖ ያሳድራል።
4. ብክለት
ብክለት ስንል የብስና የውሀ አካላት ብክለትን ያጠቃልላል።
ጸረ ተባይና ጸረ አረም ኬሚካሎች በሰውና በእንስሳት ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ ነው።
ዶ/ር መለሰ እንደሚናገሩት፤ ንቦችና ዘር የሚያሸጋግሩ ቢራቢሮዎች (ፖሊኔተር) እየጠፉ ነው። ይህም ድርቅ የሚቋቋሙና ቶሎ የሚበቅሉ ዘሮች በስፋት እንዳይሰራጩ ያደርጋል።
የውሀ አካላት በፋብሪካ ፍሳሽና ቆሻሻ መበከላቸው ሌለው ችግር ነው።

ምን ይደረግ?
ዶ/ር መለሰ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያን ብዝሀ ሕይወት ለመታደግ በፖሊሲ የትኩረት አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። የእጽዋት፣ የእንስሳት፣ የውሀ ሀብትና ሌሎችም የተፈጥሮ ሀብቶችን የሚያስተዳድሩ ተቋሞች ውሳኔ ከማስተላለፋቸው በፊት መናበብ ይገባቸዋል።
• ብዝኀ ሕይወት ምንድን ነው? ለምንስ ግድ ይሰጠናል?
“የኢትዮጵያን ብዝሀ ሕይወት የሚጠብቀው ኢንስቲትዩቱ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡም ጭምር ነው። የአየር ንብረት ተጽእኖን መቋቋም የምንችለው ብዝሀ ሕይወትን በመጠበቅ ነው” ይላሉ ዋና ዳይሬክተሩ።
በሽታ መከላከል፣ ከፍተኛ ምርት መስጠትና ድርቅ መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን ከኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዮት ጂን ባንክ በመውሰድ መጠቀም እንደሚቻል ያስረዳሉ።
ከዘመናዊነት ጋር ተያይዘው የመጡ የምግብ አይነቶች እንደካንሰር፣ ስኳርና ደም ግፊት ላሉ ተላለፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምክንያት በመሆናቸው ተፈጥሯዊ ምግብ ማዘውተርንም ይመክራሉ።
የሕዝበ ቁጥር መጨመር ያመጣውን የምግብ እጥረት ችግር ለመፍታት ‘አግሮፎረስተሪ’ የተባለውን መንገድ መጠቀምን እንደ አማራጭ ያስቀምጣሉ። ይህ ደንና የፍራፍሬ ዛፍ በጥምረት የሚመረትበት ዘዴ ነው።