(አብመድ) የታሪክ መምህር ናቸው፤ ለ27 ዓመታት ያክል በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ክርስቶፎር ኒፖት ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ በዚህ ወቅት ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው በሙያቸው ሀገራቸውን እያገለገሉ ነው፤ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በታሪክ አስተማሪነት እየሠሩ ይገኛሉ፤፡ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ፡፡

ሁሉም በሀገሩ ያምራል እና ከስደት መልስ አፈር ፈጭተው፣ ውኃ ተራጭተው ወደ አደጉባት ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው በሙያቸው ተማሪዎቻቸውን ማገልገል በመቻላቸው ደስተኛ እንዳደረጋቸው አጫውተውናል፡፡ ‹‹ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያንዣበበ ያለው አለመረጋጋት እና ቀውስ ሀገሬን ወደ ከፋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊዘፍቃት ነው የሚል ስጋት ውስጥ ጥሎኛል›› ብለውም ፍርሃታቸውን ነግረውናል፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለው መፈናቀል እና አለመረጋጋት በቀጣይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል በሰከነ መንፈስ ካልታየ ትርፉ ኪሳራ፣ ውጤቱ የበለጠ ሞት እና መፈናቀል ሊሆን እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡ ሀገሪቱ ወደ ማትወጣው ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ ከወዲሁ ማስተዋልን እንደሚጠይቅ፣ በዛሬ መነፅር ነገ ምን ሊከሰት እንደሚችል መመልከት እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚያጋጥሟቸውን ጊዜያዊ ችግሮች ተቋቁመው በተባበረ ክንድ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት መፍጠር የቀውሱ መውጫ መንገዳቸው እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የሚበጃቸው ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት የምትመለከት አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያ ስትኖር ነው፤ ካሉት አማራጮች ሁሉ ለከፍተኛ ጥፋት የማይዳርግ ብቸኛው መንገድም ይህ መሆኑን አስቀምጠዋል፡፡
ከሰባት ሺህ ዓመት በላይ ታሪክ እንዳላት ድርሳናት የሚመሰክሩላት ኢትዮጵያ አንድነቷን አስጠብቃ የቆየችው የጥንት አያት ቅድመ አያቶች አንድ ሀገራዊ ዓላማ ስለነበራቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ሰው በሀገሩ መሰደድ እንደሌለበት እና የችግሩን ምንጭ ማድረቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
‹‹የሚሠራ ቢሆን ሁሉም በየጎጡ የሚመኘውን ነፃነት ቢያገኝ መልካም ነበር፤ ግን አይሠራም፡፡ ማኅበረሰቡን ለበለጠ ሰቆቃ ያጋልጣል፡፡ ደግሞም እያየነው ነው፤ ሰዎች በትውልድ ሀገራቸው እየተፈናቀሉ ነው፡፡ የሚታየው ውዥንብር ያለ ጥፋት ሠላም እንደማይገኝ ያለመ ይመስላል›› ነው ያሉት፡፡
ምንም ያክል ተግዳሮቱ ይብዛ እንጂ ለኢትዮጵያውያን የሚዋጣው ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ሀገርነት ሂደት በተሳካ ሁኔታ ማከናወኑ እንደሆነና በርካታ የኢትዮጵያ የታሪክ ክስተቶች ያረጋገጡትም ይህንን ሀቅ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
የተሰባሰቡ ማኅበረሰቦች የሠላም እና የብልፅግና ማሳያዎች እንደሆኑና በተቃራኒው በጥቃቅን ልዩነቶች የተናቆሩና የተበታተኑ ደግሞ የሰቆቃ እና የሽብር ሰለባ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
‹‹ሰው ስብዕናው የሚረጋገጠው ሰፊ እና ጥልቅ ማኅበራዊ ግንኙነት በመፍጠሩ ነዉ፤ ሰው ስልጡን ነው የሚባለው ከሌሎች እንስሳት በተለየ በአንድነት ተባብሮ ታላቅ ስኬቶችን ማከናወን በመቻሉ ነዉ፤ ከዋሻው እና ከመንደሩ ወጥቶ ሀገራዊ አንድነትን መሥርቶ መኖር በመቻሉ ነው›› ያሉት ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያውያን የቆየ ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን መመሥረት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
ይሁን እንጅ አንዳንዶቹ ሰፊውን ስብስብ በጥርጣሬ ወይም በስጋት እንደሚመለከቱት መታዘባቸውን እና በእርሳቸው እምነት እንደዚህ ዓይነት እሳቤ ያላቸው ሰዎች ከሌላው ጋር ሲዘነቁ የራሳቸውን የሚያጡ የሚመስላቸው ሰዎች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
‹‹ለግለሰቦችም ይሁን ለቡድን መብቶቻችን መከበር ጠንካራ ኢትዮጵያን መመሥረት ቁልፍ ነው፤ ከዋሻው እንውጣ ስንል ከዋሻው ወጥተን ለመኖር የሚስችለን ሰዋዊ ባሕሪ ስላለን እንጠቀምበት ለማለት ነው፤ ይህ ባሕሪ በሰለጠነው፣ በዚህ ዘመን በውይይት እና በድርድር ሊዳብር ግድ ይላል›› በማለትም የአንድነትን እና የመጠናከርን ማኅበራዊ ኃይል ገልፀውታል፡፡
በእርግጥ አሁን ባለው ተጨባጭ የሀገራችን ሁኔታ ያነሱትን ሐሳብ የማይስማሙበት ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ የሐሳቡ መኖር በብዙ ችግሮች ማዕከል ተወጥራ የምትገኘውን ኢትዮጵያን ለመጠገን ብርቱ ሥራን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቋሚ ነው፡፡
‹‹ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሔ በማስቀመጥ ከገባንበት ዝቅጠት መውጣት አለብን›› ያሉት ፕሮፌሰር ሹመት ሁሉም ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለበት መክረዋል፡፡
ያንዣበበው የቁርሾ እና ሁከት አዝማሚያ ከቁጥጥር ወጥቶ ወደ ለየለት ሥርዓት አልበኝነት እንዳያመራ ኃላፊነት የሚሰማው ሁሉ የየግሉን ሀገራዊ አደራ በትጋት መወጣት እንዳለበትም መክረዋል፡፡
ዜጎች ያላቸውን ሙሉ አቅም ለዕለት ቁጣ ማብረጃ ሳይሆን ለዘላቂ ሀገራዊ ዓላማ ግንባታ ሊያውሉት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ሐኪሞች የሕክምና ተማሪዎችን ሲያሰለጥኑ የሚጀምሩት ‹‹ቢያንስ ጉዳት አታድርሱ›› በሚል ምክር መሆኑን ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም ቢያንስ አሁን ያለውን አስጊ ሁኔታ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ መጠንቀቅ እንደሚገባው መክረዋል፡፡
አንዳንዴም ‹‹ሁሉም ራስ ወዳድ ሲሆን፣ መፈናቀሉ ሲጠና፣ ተስፋ በመቁረጥ ‹ምነው ደፍርሶ በጠራ› የሚል አቋም ያላቸው ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ›› ያሉት ፕሮፌሰር ሹመት እንደዚህ ዓይነት ድምዳሜ የማያዋጣ፣ አደገኛ ምኞትና ብስለት የጎደለው ውሳኔ እንደሆነ ነው ተናገሩት፡፡
እንደ እርሳቸው ዕይታ የደፈረሰው ሁሉ ላይጠራ ይችላል፤ አንዳንዴም ‹‹ደፍርሶ ጠርቷል›› ከተባለ በኋላ ጠራ የተባለው አማራጭ ተስማሚ ላይሆን ይችላል፡፡ ሶሪያ እና ሊቢያ እየገጠማቸው ያለውን የቀውስ ክስተት በማጣቀሻነት በማንሳት የቀጣይቷን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ከወዲሁ መታደግ የሚቻልበትን መንገድም አመላክተዋል፡፡
የሥራ አጡ ቁጥር ከሠራተኛው ከሚበልጥበት፣ መሬት የገንዘብ ምንጭ በሆነበት፣ ከሚመገበው ጦም አዳሪው በበዛበት በዚች ሀገር ‹‹ደፍርሶ ይጥራ ማለት ‹ከጫጩት ፊት ፈንግል› እንደማውራት ይቆጠራል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ‹‹የውኃ ሙላት እያሳሳቀ ይወስዳል›› እንዲሉ በየቦታው የሚታየው መፈናቀል እንዳይገፋና ወደ ነውጥ ጎርፍ እንዳይወስድ ከወዲሁ መጠንቀቁ የሚበጅ መሆኑን መክረዋል፡፡
እንዲህ ካለው አደገኛ አካሄድ መከላከል የሚያስችል፣ ደመ-ነፍሳዊ እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ፣ የደቦ ፍርድ እንዲወገድ አርቆ