ሐራ ዘተዋሕዶ

May 23,2019

በጅግጅጋ በአላባ በአጣዬ የቤተክርስቲያን ጥቃት

***

***

/ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፤ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ/

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የዛሬ ኀሙስ ከቀትር በኋላ ውሎው፥ በአገር የሰላም ጉዳይ፣ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግርና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ላይ በሚደርስባቸው ጫና እና አድልዎ ላይ አተኩሮ ተወያይቷል፡፡ በአጀንዳ ተ.ቁ(3) የሰፈረውና አብዛኛውን የጉባኤውን ሰዓት የወሰደው፣ ወቅታዊው የአገር ሰላም ጉዳይ፣ በርካታ ሐሳቦች በስፋት ተንሸራሽረውበታል፡፡ “ያልተነካ ነገር የለም፤ ብዙ ሐሳቦች ተንሸራሽረዋል፤” ያሉት የስብሰባው ምንጮች፣ የሰላም እና የዕርቅ ዐቢይ ኮሚቴ እንዲቋቋም መወሰኑን ገልጸዋል፡፡  

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ የሚቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴው፣ ስድስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትንና ሦስት የመምሪያ ሓላፊዎችን በአባልነት የያዘ ሲኾን፣ ችግሩ የታየባቸውን ክልሎች ያገናዘበ የአህጉረ ስብከት ጥምር ንኡሳን ኮሚቴዎች እንደሚኖሩት ተመልክቷል፡፡

እንቅስቃሴውን በበላይነት የሚያስተባብሩት ዘጠኙ የሰላም እና ዕርቅ ዐቢይ ኮሚቴው አባላት፡- የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ የሻሸመኔ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ፣ የምሥራቅ ወለጋ – ቄለም ወለጋ – ሆሩጉድሩ አህጉረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ የጠቅላይ ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊ መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ፣ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዋና ሓላፊ አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት እና መ/ር ምትኩ ከንቲባ ናቸው፡፡

በዐቢይ ኮሚቴው ሥር፣ አህጉረ ስብከት በጥምረት ንኡሳን ኮሚቴዎችን የሚያቋቁሙባቸው አካባቢዎች፣ ለጊዜው አራት ያኽል ናቸው፡፡ የአሶሳ፣ የወለጋ፣ የመተከል እና የባሕር ዳር ሊቃነ ጳጳሳት – በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፤ የሰሜን ጎንደር፣ የሁመራ፣ የወልዲያ፣ የመቐለ ሊቃነ ጳጳሳት – በአማራና በትግራይ ክልሎች፤ የደቡብ ወሎ፣ የሰሜን ሸዋ፣ የአፋር፣ የሶማሌ፣ የምሥራቅ ሐረርጌና የድሬዳዋ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት – በምሥራቅና መካከለኛው ኢትዮጵያ፤ እንዲሁም የቦረና፣ የሐዋሳና የወላይታ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት – በጉጂ እና በጌዲዮ የመሳሰሉት አካባቢዎች ያለውን ችግር ይፈታሉ፡፡

ንኡሳን ኮሚቴዎቹ፥ ሰፊና ተከታታይ የሰላምና የስብከተ ወንጌል ስምሪት እያመቻቹ ግጭትንና ጥቃትን ይከላከላሉ፤ ያስቆማሉ፤ ሕዝብን ከሕዝብ ያቀራርባሉ፤ ይሸመግላሉ፤ ያስታርቃሉ፡፡ በእነርሱ ደረጃ ሊፈቱ ካልቻሉ ለዐቢይ ኮሚቴው በሚያደርሱት መረጃ መሠረት፣ በፌዴራል ደረጃ ወደሚመለለከታቸው አካላት እያቀረበ በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኙ ያደርጋል፤ ከመሠረታቸው ስለሚፈቱበት ኹኔታ አካሔዶችን እየቀየሰ ስምሪት ያካሒዳል፤ የሰላምና ሕዝብን ከሕዝብ የማገናኘት ሓላፊነትም ተጥሎበታል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳሰስ

“ግጭቶችና አፈታታቸው – አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ እይታ” በሚል ርእስ፣ ለዐቢይ ኮሚቴው መቋቋም መነሻ የኾነውን ጽሑፍ ለምልአተ ጉባኤው ያቀረቡት፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ “በመሠረቱ ሕዝብ እና ሕዝብ አልተጣላም፤ የተጣሉት ፖሊቲከኞች ናቸው፤” ይላሉ፡፡ ችግሩ የፖሊቲከኞች ኾኖ እያለ ወደ ሕዝብ እያወረዱ ሕዝቡ በማያውቀው ጉዳይ ለማባላት ስለሚሞክሩ የእንቅስቃሴውን አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡ በተለይም የቤተ ክርስቲያን ልጆች የኾኑ እርስ በርስ የመገዳደል ኹኔታ ለቤተ ክርስቲያንም ታሪክ፣ ለሕዝብም ለራሱ አሳፋሪ መኾኑን ገልጸው፣ ከዚህ አንጻር አህጉረ ስብከት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሊሠሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

“ከተስፋ ይልቅ በቀቢጸ ተስፋነት፣ ተረጋግቶ ከመኖር ይልቅ ፍርሃትና ስጋት፣ ከመተማመን ይልቅ እርስ በርስ መጠራጠር፣ ተከባብሮና ተፋቅሮ ከመደማመጥ ይልቅ መናናቅ፣ ከመሰባሰብ ይልቅ መለያየት ወዘተ… በገነነበት ኹኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው ቢባል ጊዜው የሚያሳየንን መግለጽ እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም፤” ያሉት ብፁዕነታቸው፤ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሰላም ባህል እንዲዳብር፣ ቤተ ክርስቲያን በየተቋሞቿ የሰላም፣ የዕርቅና የአብሮነት ስሜት እንዲጎለብት የማስተማር ሓላፊነቷን አውስተዋል፡፡ ከአገሪቱ ጋራ ካላት ታሪካዊ ቁርኝት፣ ሰፊ መሠረት ያላት የብዙኃን ኢትዮጵያውያን መሪ ከመኾኗ አኳያ፣ ሰላምና መልካም አስተዳደር የማስፈን ድርሻዋን በግንባር ቀደምነት መፈጸም እንዳለባት ተናግረዋል፡፡

ዛሬም እንደ ትላንቱ ከፊት ቀድማ የሰላም አምባሳደር ኾና ለመምራት፤ የዕርቅ፤ የፍቅር፤ የፍትሕ፤ የይቅርታ አለኝታነቷን ለማስመሰክርና በረከቷን ለመናኘት ያስችሏታል በሚል ከዘረዘሯቸው ተግባራት ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፤

በምልአተ ጉባኤው አጀንዳ ተ.ቁ(4) እና (5) የተያዙት፥ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግር እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ላይ ስለሚደረጉ ጫናዎች፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ መወያየት የጀመረ ሲኾን፣ ሳይቋጭ አድሯል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ባልዋለችበት እየከሠሠ የሚያቃጥል፣ ካህናትዋንና ምእመናንዋን የሚገድል፣ የሚያንገላታና የሚያሳድድ የውስጥና የውጭ ኀይሎች ቅንጅት ስለ መኖሩ፣ በምልአተ ጉባኤ ግንዛቤ መያዙ ተጠቁሟል፤ ለምን? እነማን ናቸው ይህን የሚሠሩት? በምን እንፈታዋለን? የሚሉ ጥያቄዎችንም አንሥቷል፡፡ ጥቂት በማይባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን በሥርዓተ እምነታቸው መሠረት እንዳይለብሱ፣ በአግባቡ እንዳይጾሙ የመሳሰሉትን የእምነት ነፃነት መገፈፍ ጉባኤው መክሮበታል፡፡

ዜግነታዊና ሰብአዊ መብቶች እንዲሁም ሥርዓተ እምነትን በነፃነት እንዳይፈጸም የሚያደርጉ በደሎች፣ መንግሥት በፍጥነት ማስቆም እንዳለበት አቋም ተይዟል፤ “ማስቆም የማይችል ከኾነ ሌላ ጉዳይ ነው፤” ያለው ምልአተ ጉባኤው፣ የሰላምና የዕርቅ ዐቢይ ኮሚቴው በዚህ ረገድ የሚያከናውናቸው ተግባራት እንደተጠበቁ ኾነው፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሚኒስትሮችና የጸጥታ አካላት ጋራ በግልጽ የመነጋገሩን አስፈላጊነት አምኖበታል፡፡ ለዚህም የተለያዩ አማራጮች የቀረቡ ሲኾን፣ የችግሩን አስከፊነት የሚገልጽ ደብዳቤ በቅድሚያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጽፎ፣ በእርሳቸው አማካይነት ይመለከታቸዋል የሚባሉ አካላትን ከፍተኛ ሓላፊዎች ለይቶ በመጥራት ለማነጋገር መታሰቡ ተጠቁሟል፡፡ ADVERTI