May 23, 2019
Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማይክሮሶፍት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሁለተኛውን የሙከራ ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ መክፈት እንደሚፈልግ ገለጸ።
ይህ የተሰማው በኬንያ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም የቴክኖብሬይን ኩባንያ አመራሮች ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ነው።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ የኢንፎርሜሽን መልካም እድሎችና በቀጣይ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ተሳትፎ በሚያደርግባቸው መስኮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
ቴክኖብሬይን ናይሮቢ የሚገኘውን በአፍሪካ የማይክሮሶፍት ብቸኛ የሙከራ ማእከል ያስተዳድራል።
በውይይቱ ወቅትም የኩባንያ ማኖጅ ሻንከር ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በቴክኖሎጂ፣ በፐብሊክ ፋይናንስ አስተዳደር፣ በስልጠናና ማማከር፣ በታክስና ገቢዎች አስተዳደር፣ በቢዝነስ ስራዎች በስፋት መሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
ዋና ስራ አስኪያጁ በኢትዮጵያ ውስጥ የጀመረውን ኢንቨስትመንት ለማስፋት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው፥ እስካሁን መንግስት እያደረገላቸው ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
ቴክኖብሬይን ከኬንያ በተጨማሪ በዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ማላዊ፣ ሩዋንዳ እና ዛምቢያ ቅርንጫፍ ከፍቶ በመስራት ላይ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በታንዛኒያ፣ ጋና፣ ማላዊ፣ ዚምባብዌ እና ላይቤሪያ በሰራቸው የዘመናዊ መታወቂያ አሰጣጥና የታክስና ገቢ አሰባሰብ ስራዎች መስራቱንም በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።