ሁሌ እናስታውሳቸው
ተቀብሮ እንዳይቀር
አኩሪ ታሪካቸው!!!!!!!
ጌታቸው ጥሩነህ ማን ነው??
የጌታቸው ጥሩነህን ፎቶግራፍ በማግኘት ለተባበረኝ ለወንድሙ ተስፋ ሚካኤል ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡ አሁን የታሪክ ማህደሩን የተሟላ ያደርገዋል፡፡ በድጋሚ አመሰግናለሁ!!!
ተወርዋሪዉ የኢሕአፓ ተጋዳይ (ምንጭ ጎሕ መጽሔት ፤ጥቅምት ፩፱፺፬ ዓ.ም )
“አሸምቆ” በሚል ቅጽል ስም ነበር የሠፈር ጓደኞቹ የሚጠሩት ።በተፈጥሮዉ እልኸኛና አትንኩኝ ባይ ፤ በማኅበራዊ ሕይወቱ ደግሞ ከሰዉ ጋር ተግባቢና ተጫዋች ነበር ።በጓደኞቹ ዘንድ ተከባሪ የሆነዉን ያህል ከጠላቶቹ ሳይቀር በአይምሬ ጀግንነቱ አድናቆትን አትርፏል። አራት የትግል ጓዶቹ የሚገኙበትን ቡድን ለፍልሚያ እየመራ ድርጅታዊ ተልዕኮዉን ለመወጣት ከቤቱ ወጥቶ እስከቀረባት ሕዳር ፮ ቀን ፩፱፻፸ ዓ.ም ማለዳ ድረስ በከፍተኛ ፲፩ ቀበሌ 02 ዉስጥ ነበር ኗሪነቱ ። የዚሁ ከፍተኛ የኢሕአፓ ተጠሪም ነበር ።
ጌታቸዉ ጥሩነህ በ፩፱፻፵፪ ዓ.ም መጋቢት ወር በዕለተ ኪዳነምህረት(፲፮) ፤ ገዳም ሠፈር ነበር የተወለደዉ ።ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኑ በተለይ ወላጅ እናቱ ወጥቶ እስከሚገባ አያምኑትም ነበር ። በዚሁ ጽኑዕ ፍቅር የተነሳም ነበር ፤ በእናቱ በወይዘሮ ጥሩነሽ ወልደኪሮስ ስም ለመጠራት የበቃዉ ።ከ፩ኛ እስከ ፭ተኛ ክፍል አርበኞች ፤ ከ፮ተኛ እስከ ፰ተኛ ደግሞ በቁስቋም (እቴጌ ጣይቱ ብጡል ) ተምሯል ። ከዚያም ከ፱ እስከ ፲፪ኛ ክፍል ድረስ በቀድሞዉ ተፈሪ መኮንን አጠቃላይ ሁለተኛ ት/ቤት ተከታትሏል ። ትጉህ ተማሪ ነበር ። በአንድ ዓመት ሁለት ክፍሎችን ያለፈበት ጊዜ የመኖሩን ያህል ከንጉሡ እጅ ሽልማቶችን ለመቀበል የበቃ ተማሪ ሊሆን በቅቷል ።በአለማያና በባህር ኃይል ኮሌጆችም ትምህርቱን ተከታትሏል ።
አለማያ ኮሌጅ ይማር በነበረበት ጊዜ የሃገሪቱ ተማሪዎች በጉልተኛዉ ሥርዓት ላይ ያደርጉት የነበረዉ አመጽ እጅጉን ተፋፍሞ ነበር ። እናም አንድ ወቅት ላይ ጉደር ይገኝ በነበረዉ የራስ መስፍን ስለሺ እርሻ ዉስጥ በጎተራ በተቀመጠ ጤፍ ላይ እሳት ተለቀቀበት ። በእርሻዉ ላይ የነበረዉ የወይን ተክልም ተጨፈጨፈ ።የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተማሪዎች መሆናቸዉ በመጠርጠሩ ጌታቸዉን ጨምሮ ከየሥፍራዉ እየታፈሱ ወደ ሰንዳፋ ተወስደዉ ታሰሩ ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም በሥራ እንዲቀጡ ከሰንዳፋ ወደ ጎጃም ጠቅላይ ግዛት ተወሰዱ ። ጌታቸዉ ጠያቂ አልነበረዉም ። እንዲያ የሚወዱት እናቱ ፤ እሱን ፤ ታናናሾቹን አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጃቸዉን ጨምሮ አራት ቤተሰባቸዉን የሚያስተዳድሩት ሳንባ ነቀርሳ ሆስፒታል ዉስጥ በጤና ረዳትነት ተቀጥረዉ በሚያገኟት አነስተኛ ደመወዝ ነበርና ወደ ጎጃም ሄደዉ ሊጠይቁት አልቻሉም ።
ከአንድ ዓመት እስራት በኋላ ተፈትቶ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰዉ ጌታቸዉ የአለማያ ትምህርቱን አቋርጦ በባህር ኃይል ኮሌጅ በእጩ መኮንንነት ተቀጥሮ ወደ ምጽዋ አቀና ።እዚያም ሳለ በተደጋጋሚ ጊዜ እየታሰረ ተፈትቷል ። ሆኖም ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋል ሥልጠናዉን አጠናቅቆ በ፩፱፻፷፰ ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል ። መኖሪያዉን በከፍተኛ ፲፩ ቀበሌ 0፪ ዉስጥ በሚገኘዉ የእናቱ ቤት ያደረገ ሲሆን በኢሕአፓ ዉስጥ ተሰልፎ በሕቡዕ መንቀሳቀሱን ቀጥሎበታል ።በዚሁ እንቅስቃሴዉ ወቅት ትጋቱንና ብቁ አመራር ሰጪነቱን ከማስመስከሩም በላይ ከሌሎቹ ጓዶቹ ጋር በመሆን የድርጅታቸዉን ሥራ በትጋት ሲያቀላጥፉ ቆይተዋል።
ወቅቱ ደርግና የመኢሶን ሎሌዎቹ ኢሕአፓን በጸረ-አብዮተኛነት ፈርጀዉ የተንቀሳቀሱበት ፤ ደም የጠማቸዉ የሥርዓቱ አጫፋሪዎችም ታጥቀዉ ወጣቱን በየአካባቢዉ መፍጀት የጀመሩበት የትንቅንቅ የሽብር ጊዜ ነበር ።ኢሕአፓም በበኩሉ ሕልዉናዉ አጠያያቂ ደረጃ ላይ በወደቀበት በዚያን መሰሉ ሁኔታ ዉስጥ ራሱን መከላከልና አጸፋዉን ለመመለስ በመገደዱ ከጠላቶቹ ከሚላኩበት የሞት መልዕክተኞች ጋር በየአቅጣጫዉ በመፋለም ላይ ነበር ።በዚህ መሰሉ ቀዉጢ ዉስጥ ነበር እንግዲህ ጌታቸዉ ጥሩነህ ድርጅቱን ኢሕአፓን ለመታደግ በፍልሚያዉ ሜዳ ጠላቶቹን እንደወጡ ማስቀረት የጀመረዉ ።በሚደርሰዉ መረጃ መሠረት፤ የደርግ አሳሽ ቡድኖች በሚንቀሳቀሱባቸዉ አካባቢዎች አብዛኛዉን ጊዜ ብቻዉን በመሄድ ፤ በሌላዉ ጊዜ ደግሞ ከትግል ጓዶቹ ጋር በመሆን የዕኩያኑን ግንባር በአረር እየተረከከ ፈጥኖ በመሰወር ከቶ አቻ አልነበረዉም።
በነበረዉ ፈጣን የትምህርት አቀባበልና በወታደራዊ ቅልጥፍናዉ በአዛዦቹ ሳይቀር የተሞገሰዉ ወጣቱ ጌታቸዉ በምጽዋዉ የባህር ኃይል ኮሌጅ ቆይታዉ የቀሰመዉ ትምህርት፤ በግልም በጓደኞቹ ዘንድ የነበረዉ ተደማጭነት በፍልሚያዉ መስክ የሚሰጠዉን ተልዕኮ ሁሉ ያለአንዳች ግድፈት ለመወጣት አስችሎታል። ጠላቶቹ እስከፍጻሜዉ ድረስ ማንነቱንም ሆነ መግቢያና መዉጫዉን በፍጹም አያዉቁም ነበር ። በስሙ ብቻ ግን ይሸበሩ ፤ በዝናዉ ብቻም ይበረግጉ ነበር ።ይህ ሁሉ ሆኖ ፤ ጌታቸዉ ከምጽዋ ከተመለሰ በኋላ አንድም ቀን እንኳ ከቤቱ ዉጭ አድሮ እንደማያዉቅ ቤተሰቦቹ መስክረዉለታል። ለየት ያለ ድርጅታዊ ሥራ ካላስመሸዉ በስተቀርም ወደቤቱ የሚገባዉ በጊዜ ነበር ።ዘወትር ጠዋት ከቤቱ ሲወጣ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ስለሚያዩት የኢሕአፓ ተሳትፎዉ ለረዢም ጊዜ እንዳይታወቅበት ረድቶታል።ከርሱ ይልቅ ተስፋ ሚካኤል ታዬ የሚባለዉ ታናሽ ወንድሙ በኢሕአፓ አባልነት ተጠቁሞበት በአሁኑ ወረዳ ‘፫ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ መቆየቱን ስናጤን ጌታቸዉ ራሱን በሕዝብ መሃከል የሰወረበትን ከጥበብ የተጠጋ ብልሃት እናደንቃለን።
ሕዳር ፮ ቀን ፩፱፻፸ ዓ.ም
የጌታቸዉ ወላጅ እናት ወ/ሮ ጥሩነሽ ወልደኪሮስ በጤና ረዳትነታቸዉ ከሌሎቹ ባልደረቦቻቸዉ ጋር በመሆን ወደ ኤርትራ እንዲዘምቱ ከተደረገ ሰነበተ ።የጌታቸዉ ታናሽ ወንድም ተስፋ ሚካኤልም በኢሕአፓነት ተጠቁሞ ከታሰረ ቆዬ ። ቤቱ ዉስጥ የቀሩት ጌታቸዉና ትንሽ እህቱ ብቻ ነበሩ ።
ጌታቸዉና አራት የትግል ጓዶቹ ፤ አጸደወይን ሰቡ ዘገየ ፤ ተካ (በቅጽል ስሙ ዛጋምባ)፣እና ጥላሁን (ሁሉም የሽሮ ሜዳ ልጆች ናቸዉ ) ከ ጌታቸዉ የኋላሸት ጋር በመሆን በዕለቱ የመጨረሻዉን የከተማ ዉስጥ ግዳጃቸዉን ከተወጡ በኋላ አሲምባ ፤ ካልሆነም ሱዳን ለመግባት ወስነዋል ። ደብረብርሃን ተወልዶ ጨርቆስ ያደገዉ ጌታቸዉ የኋላሸት ከስመ ሞክሼነታቸዉ ወዲያ ለጌታቸዉ ጥሩነህ የቅርብ ጓደኛዉ ነበር ።ባህር ኃይል ኮሌጅ አብረዉ በዕጩ መኮንንነት ሲሰለጥኑ ከመቆየታቸዉም በላይ አብረዉ ጠፍተዉ ወጥተዋል ። እናም ጌታቸዉ ጥሩነህ በዚያን ዕለት ማለዳ ፤ እህቱ ስምረት ደመረ ያቀረበችለትን ቁርስ ከተመገበ በኋላ ጓደኞቹ ዘንድ ደርሶ እንደሚመለስ ነግሯት ከቤት ወጣ።ከአምስቱ የኢሕአፓ ጓዶቹ ጋር ቀደም ብለዉ ከተቀጣጠሩበት ቦታ ከተገናኙ በኋላ በተመደበላቸዉ ኩምቢ ቮልስዋገን መኪና ተሳፈሩ ። የዚያን ዕለቱ ዒላማቸዉ ጭራቁ የደርግ ሰዉ በላ ቀልቤሳ ነገዎ ነበር ። ግንባሩን በአረር ለመፈርከስ ተሰናድተው ፤ ወደሚገኝበት ከፍተኛ ፱ ገሰገሱለት ።
ደርግ ምስጢሩን እንዴት ሊደርስበት እንደቻለ እንቆቅልሹ እስከዛሬም አልተፈታም ። አምስቱን ጓዶች ጭና የምትገሰግሰው ኩምቢ ቮልስ ቀጨኔ ድልድይ ላይ እንደደረሰች አንድ መሳሪያ የታጠቀ ሰዉ በድንገት ከተሸሸገበት ወጣና እንዲቆሙ የግዳጅ ምልክት ሰጣቸዉ ። እንደተባሉትም አደረጉ ። ሰዉዬዉም ወዲያዉኑ ወደመኪናዋ ቀርቦ መታወቂያቸዉን እንዲያሳዩት አዘዛቸዉ ።ጌታቸዉ ጥሩነህ መታወቂያዉን አዉጥቶ በማሳየት ላይ ሳለ መከበባቸዉን የተገነዘቡት ጓዶች አንዳች ፈጣን ርምጃ መዉሰድ እንደሚገባቸዉ አምነዉበታል ። እናም አጸደወይን ከመኪናዉ ወርዳ በስተጀርባዉ ዞረችና ወታደሩን መትታ ጣለችዉ ።በዚያዉ ቅጽበት ደፈጣ ላይ የነበሩት በርካታ ወታደሮች ካደፈጡበት ሆነዉ እንዳይነቃነቁ አዘዟቸዉ ። አምስቱ የኢሕአፓ ጓዶች ግን ትዕዛዙን ከቁምነገር ሳይጽፉ የነፍስወከፍ መሣሪያዎቻቸዉን በፍጥነት አንስተዉ ከመኪናዋ በቅልጥፍና ወርደዉ ከግዙፉ ወታደራዊ ኃይል ጋር ለመፋለም ቦታ ቦታቸዉን ሲይዙ ጥይት በላያቸዉ ዘነበባቸዉ ።
የተኩስ ልዉዉጡ አይሎ ቀጠለ ። ጌታቸዉ ጥሩነህም ቦታ እየቀያየረ ከፊት ለፊታቸዉ መሽገዉ ከሚታኮሱት ወታደሮች አብዛኛዎቹን ጣለ ። ከራሱ ወገን ጥላሁንና ተካ (ዘጋምባ) ተመትተዉ ሲወድቁ የተመለከተዉ ጌታቸዉ ፤ አጸደወይን ሰቡንና ጌታቸዉ የኋላሸትን እንዲያመልጡ ነገራቸዉ ። ለዚህም በሽፋን እየተታኮሰ ሲከላከልላቸዉ ቆየ ። በዚህ መሀከል ፤ ግራኙ ጌታቸዉ ግራ እጁን በመመታቱ እንደልቡ መታኮስ አልቻለም ።ሁኔታዉን በማስተዋሉ፤ የትግል ጓዱን በዚያ መሰሉ ቅጽበት ዉስጥ ጥሎ ለማምለጥ ያልፈቀደዉን ሞክሼዉን (ጌታቸዉ የኋላሸትን) እንዲያመልጥ ጎተጎተዉ ። እርሱ ግን ማምለጥ ካልቻለ እጁን እንደማይሰጥና ራሱን እንደሚያጠፋ ወስኖ ነበር ። እናም በፍጻሜዉ ሰዓት የቀረችዉን አንዲት ጥይት የጎረሰዉን መሣሪያ አፈሙዝ ወደገዛ ራሱ በማለም መተኮሻ ቃታዉን ሳበዉ ።….፣ ወዲያዉኑም ፤ሁሉም ነገር ጸጥ-ረጭ አለ። ስሙ ሲጠራ ጠላት የሚያሸብረዉ የኢሕአፓዉ ተወርዋሪ ተጋዳይ ጌታቸዉ ጥሩነህ ፤ ለትግሉ በወደቁቱ አያሌ የኢሕአፓ ቆፍጣና ጀግኖች ፈለግ ከጠላቶቹ ሲተናነቅ ወደቀ፤-ለታላቁ ዓላማዉም ተሰዋ ። ክብር ሞቱ ለሰማዕት ።
***********
በሥፍራዉ የነበሩት ወታደሮች የጌታቸዉ ጥሩነህን ሞት ለደርግ ጽ/ቤት በሬድዮ አስታወቁ ። ደርጎችም ሁነቱን ታላቅ ግዳይ አድርገዉ በመቁጠራቸዉ አስከሬኑን ወደ ቤተ መንግሥት አስወሰዱትና በሬዲዮአቸዉም መረሸኑን አስነገሩ ። በቁም ሳለ መዉጫ መግቢያ ያሳጣቸዉን ሳተና በሞቱ አዩት ።
ጌታቸዉ የኋላሸት ከሞት ቀለበት አምልጦ ከጊዜ በኋላ ይህን ታሪክ ለማስጻፍ በቃ ። አጸደወይን ደግሞ ካመለጠች በኋላ የወርቅ ሀብሏን ተቀብለዉ ቤታቸዉ ዉስጥ በሸሸጓት አንዲት ሴት ጠቋሚነት ተይዛ ፊቷ በሳንጃ ተዘልዝሏል ። የጌታቸዉ ጥሩነህ ትንሽ እህት ወንድሟ በተሰዋበት ዕለት በአረመኔዉ ቀልቤሳ ነገዎ በሚመራ አሳሽ ቡድን ከቤቱ ተወስዳ ከመሰቃየቷም በላይ ለረዢም ጊዜ ታስራ ቆይታለች ። ወላጅ እናቱ ከሔዱበት የኤርትራ ዘመቻ ሲመለሱ የተቀበላቸዉ በቀበሌ የታሸገ ቤት ነበር ።
ጌታቸው ጥሩነህ በአሁኑ ሰአት ከወያኔ ጋር እየተዋደቀ ላለው ወጣት ትውልድ አርአያና ምሳሌ ነው። በጣም እንኮራበታለን!!!!!
አንድነት ሃይል ነው!!!
የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል !!
