SourceURL:https://haratewahido.wordpress.com

ሐራ ዘተዋሕዶ

et-600x387

***

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በተለያዩ አካባቢዎች፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየተፈጸሙ ስለሚገኙ ግፎች፣ ትላንት የጀመረውን ውይይት ዛሬም ቀጥሏል፡፡ “ስለ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግር ጉዳይ” በሚል በአጀንዳ ተ.ቁ(3) በቀጠለው በዛሬ ዓርብ፣ ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. የቀትር በፊት ስብሰባው፣ ከየአህጉረ ስብከቱ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቀረቡ ሪፖርቶችን አድምጧል፡፡

ጎሣ ተኮር በኾነና በቤተ ክርስቲያን ጥላቻ ላይ ተመሥርተው በተፈጸሙ ጥቃቶች፥ የተገደሉና የተፈናቀሉ ካህናትና ምእመናን፣ የተመዘበሩና የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ሪፖርት በየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት በዝርዝር ቀርቦ ተሰምቷል፡፡ በጅማ፣ በኢሉ አባቦር፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ፣ በድሬዳዋ አህጉረ ስብከት፣ በተለያየ ደረጃ የደረሱ ጥቃቶች በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡

ግጭቶችን ሽፋን በማድረግና በቀጥታ የደረሱት ጥቃቶች ዘግናኝነት እንዲሁም፣ በአንዳንድ ምእመናን ላይ ከኢትዮጵያዊ ባህል ውጭ በአስከሬናቸው ሳይቀር የተፈጸመው ግፍ፣ የምልኣተ ጉባኤውን አባላት አስቆጥቷል፡፡ “ትኩሳት ፈጥሯል” በማለት የገለጹ አንድ ብፁዕ አባት፣ በየክልሉ፣ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናን መብቶች በግላጭ እየተረገጡ መኾኑ ቅዱስ ሲኖዶሱን በእጅጉ ማሳዘኑን ተናግረዋል፡፡  

ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳናቸው እንዳሉት፣ የቤተ ክርስቲያን ሐዊረ ፍኖት ጸዊረ መስቀል እንደ መኾኑ በፈተና የተሞላ ቢኾንምከመቸውም ጊዜ በላይ ራስን የመከላከል አስፈላጊነት በቅዱስ ሲኖዶሱ ታምኖበታል፡፡ በግጭቶች እና ጥቃቶች ገፈት ቀማሾቹ እኛው ብንኾንም፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጉዳዩን የተመለከተው፣ ከአጠቃላይ አገራዊ ሰላምና አንድነት መጠበቅ አኳያ እንደኾነ የተናገሩት ብፁዕ አባት፣ “ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን የምንታደግበትን፣ ችግሩን ለዘለቄታው የምንቋቋምበትን ስትራተጂ እንነድፋለን፤” ብለዋል፡፡

ከዚያ በፊት ግን፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት እና የክልሎች መስተዳድሮች፣ እየደረሰብን ያለውን ግፍ ጥልቀትና ምሬት ማሳወቅና ለመፍትሔውም ፊት ለፊት ማነጋገር እንደሚያስፈልግ፣ በዛሬው ውይይት አቋም መያዙን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ኹኔታውን በዝርዝር በማብራራትና የቀረቡትን ሪፖርቶች በአስረጅነት በማስደገፍ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥያቄ ለማቅረብና በእርሳቸውም አማካይነት ይመለከታቸዋል የተባሉ አካላት ተለይተው ጥሪ እንዲደረግላቸው ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡ የቀትር በኋላ ውሎውም፣ ለሰነድ ዝግጅቱ ግምገማ ትኩረት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

በጅማ እና በኢሉ አባቦር አህጉረ ስብከት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ የተፈጸ ፎች

በጅማ ሀገረ ስብከት፡-

በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ፣ በአሕዛብ እየተፈጸመ ያለው በደልና ግፍ ከዚኽ በታች በጥቂቱ ተዘርዝሯል፡፡

ሊሙ ኮሳ ወረዳ፡- በወረዳው ያሉት ክርስቲያኖች ከዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በሠፈራ መኖር የጀመሩ፤ በኋላም በደርግ ጊዜ ወታደር የነበሩትም ሲኖሩበት ቆይተዋል፡፡ በሊሙ ኮሳ ወረዳ፣ በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ብቻ፣ ዘር ተኮርና የሃይማኖት ጥላቻ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን የማጥፋት ዘመቻ በስፋት እየተካሔደ ይገኛል፡፡

ይኸውም፣ ክርስቲያኑን እየነጣጠሉ በየቀኑ በየጫካው መግደልና ብዙዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲሰደዱ የተለያዩ ዛቻዎችን ማድረስ ናቸው፡፡ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ካሉት ወረዳዎች፣ በሊሙ ኮሳ ወረዳ ብቻ፣ ከ2009 – 2011 ዓ.ም. ድረስ ከተፈጸሙት አሠቃቂ ግድያዎች፣ ዝርፊያዎችና የቤት ቃጠሎዎች ውስጥ ለአብነት ያህል የሚከተሉት ተጠቅሰዋል፡፡

1. በሊሙ ኮሳ ወረዳ ጋሌ ሠርጤ (ቡርቃ ጉዲና እና አዲስ ልማት) ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመ ግፍ፡-

2. በጋሌ ጅማቴ ቀበሌ፣ በጫፎ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመ ግፍ

3. በጉርሙ መካነ ጥበብ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመ ግፍ

በዚህ አካባቢ ያሉ ክርስቲያኖችም ከላይ በአጎራባች አጥቢያዎች ላይ እንደተፈጸመው ኹሉ፣ አሠቃቂ መከራዎች እየደረሱባቸው ይገኛል፡፡ በጥቂቱ ለመግለጽ ያህል፡-

4. በሊሙ ሰቃ ወረዳ

5. አምቡዬ የምትባል ከተማ ላይ (ከሊሙ 17ኪ.ሜ ወደ ጅማ)፣ “ኦሮሞ ብሎ ኦርቶዶክስ የለም” ብለው ጫና በማሳደር፣ አንድ አባወራ፣ ባለፈው የ2011 ዓ.ም. ዐቢይ ጾም በማስገደድ እንዲሰልም ተደርጓል፤ ባለቤቱ ግን፣ “ጾም እስኪፈታ ድረስ ልቆይ” ብላ ምክንያት በመስጠት ቆይታለች፡፡

የቄስ ቢተው መልእክት፡- “ክርስቲያን በየአቅጣጫው እየተገደለና እየተሰደደ ነው፤ ለችግራችንም የሚደርስልን አልተገኘም፡፡ በዚህ ዙሪያ ኦርቶዶክስ ተዳክማለች፡፡ እኔም ከዚህ በኋላ፣ ኦርቶዶክስ ረዳት የላትምና በየትኛው ቦታ ቢሆን ቄሰ ገበዝ ኾኜ አላገለግልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን መብቷን ማስከበር አለባት፡፡ ሕገ መንግሥቱም ቢኾን፣ ለኹሉም እኩል የሚሠራ ከኾነ መተግበር አለበት፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው ይህ ሠቆቃ ለክርስቲያኖች ከደረሰ(ከተማልኝ)፤ ከዚህ በኋላ ብሞትም አይቆጨኝ፡፡”

በኢሉ አባቦር ዞን፤