May 24, 2019

Posted by: ዘ-ሐበሻ

የብሪታኒያን ከአወሮፓ ኅብረት መውጣትን (Brexit) ማስፈፀም አለመቻላቸው በማመን ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ተሬዛ ሜይ ሥራቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸውን አስታወቁ። ዴቪድ ካሚሮንን ጨምሮ በብሬክሲት ሰበብ ስልጣን የለቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ቁጥር ወደ ሁለት ሊያድግ ነው ማለት ነው።

ከሶስት ዓመታት በፊት ቀኝ ክንፍ ፓለቲከኞች “አገራችንን ከአውሮፓ ኅብረት አገዛዝ ነፃ እናወጣለን፤ የራሳችንን አገር ማንም ሳይገባብን ራሳችን በራሳችን እናስተዳድራለን፤ ከአውሮፓ ኅብረት ከወጣን ስደተኞችን እንቀንሳለን፤ ለአውሮፓ ኅብረት የምንልከውን ገንዘብ አገራችን ውስጥ አስቀርተን እንለማለን፤ ከሌሎች ጋር ከምንሆን ይልቅ ብቻችንን ብንሆን በበለጠ ፍጥነት እናድጋለን፤ … ” እያሉ ሕዝብን በስሜት ቀስቅሰው በጠባብ ብልጫ አሸነፉ። ያንን ሕዝበ ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ ግን ውሳኔው እንደመስጠት ቀላል አልሆነም። አገሪቷ ዙርያው ሁሉ ገደል ወደ ሆነ ማጥ ውስጥ ገብታ መውጣት አቅቷቷል።

ከአሁን በኋላም ቢሆን ብሪታኒያ ከዚህ አጣብቂኝ እንዴት እንደምትወጣ መገመት ከባድ ነው። ከበባድ ጥያቄዎችን መመለለ የማይፈራ የነበረው ስቴቨን ሀውኪንም “ስለ ብሬክሲት አትጠይቁኝ፤ አላውቅም፤ የሚያውቅ ያለም አይመስለኝም” ዓይነት ነገር ተናግሮ ነበር፤ አፈሩ ይቅለልለትና። እኔም ብሬክሲት እንዴት እንደሚጠናቀቅ ትንበያ ለመስጠት አልዳዳም፤ አገሪቷን እየናጣት ስለመሆኑ ግን በየቀኑ የምታዘበው ጉዳይ ነው።

ይሁን እንጂ ሁላችንም ከብሬክሲት የምንማራቸው በርካታ ቁምነገሮች አሉ። ጥቂቶቹን ልዘርዝር

1. ብሬክሲት ፓለቲካን ከስሜት አለመለየት አደጋው የከፋ መሆኑ ማሳያ ነው። የስሜት ፓለቲካ በተረጋጋ አገር ውስጥ ይኸን ያህል ውጥንቅጥ ከፈጠረ ባልተረጋጋ አገር ውስጥ ምን ሊፈጥር ይችላል ብሎ ማሰብ ይሰቀጥጣል። አስፍቶና አርቆ ሳይታሰብ “ከሌሎች በበለጠ እንጠቀምበታለን፤ እናተርፍበታለን” ያልነው ውሳኔ ውሎ አድሮ እኛኑ የሚጎዳ ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ነው። ፓለቲካ የሰከነ አዕምሮ ያላቸው ሰዎች ሥራ ማድረግ ይገባል።

2. ብሬክስት የተቋማት ሚና ጎልቶ የታየበት ነው ብዬ አምናለሁ። በአለፉት ሶስት ዓመታት ብሪታኒያ የቆመችው ጠንካራ ተቋማት ስሏሏት ነው እንጂ እንደ ፓለቲከኞቿ ቢሆንማ ኖሮ እስካሁን እንደ ዩጎስላቪያ ተበታትና ነበር። ፓርላማው በአጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ሽባ በሆነበት፤ ሁለቱም ዋና ዋና ፓርቲዎች በቅራኔዎች በተዳከሙበት በአሁኑ ጊዜ አገሪቷን ያቆማት የመንግሥት አስተዳደሩ (ሲቪል ሰርቪሱ) ነው።

3. ብሬክሲት፣ ችግሮች በጣም ቢወሳሰቡም እንኳን መፍትሄ ይኖራቸዋል የሚል እምነት እንዲኖረን ያደርጋል። ብሬክሲትን በቅርበት የተከታተለ ማንኛውም ሰው ብሪታኒያ እንዴት ባለ ማጥ ውስጥ እንደገባች ይረዳል። ዓለምን ስትገዛ የነበረች ታላቅ አገር እያነሰች መጥታ አሁን የተረፏትን አራት ግዛቶችን (ኢንግላንድ፣ ዊልሽ፣ ስኮትላንድና ሰሜን አየርላንድን) አስማምታ ማቆየት አዳግቷቷል። ብሬክሲት የአገር አንድነት ጉዳይን ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል። ሆኖም ከሀሳብ ፍጭት መፍትሄ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት የሚያስደምም ነው። ፓለቲከኞቿ እየተጫጫሁና እየተተራረቡም ቢሆን የሚያስማማ መፍትሄ ለማግኘት ይጥራሉ።

4. የብሬክሲት አያያዝ የመንግሥትና የፓርቲ ስልጣን ከአገር ጥቅም በላይ አለመሆኑ ያሳየ ነው። በአለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ መንግሥት ከያዘው አቋም በተፃፃሪ ድምጽ ለመስጠት ሲሉ ስልጣናቸው የለቀቁ የካብኒ ሚኒስትሮች ብዛት የሚገርም ነው። የካቢኒ አባል ሆኖ ካቢኔው ተቃውሞ በፓርላማ ድምጽ መስጠት የሚያስገምት በመሆኑ ብቻ ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን አንድ ድምጽ ለመስጠት ሲሉ በርካታ ሰዎች የሚስትርነት ስልጣናቸውን ሲለቁ ማስተዋል ለእንደኛ ዓይነት የዲሞክራሲ ተማሪ የሚያስገርም ነው። ከሚኒስትሮችም በላይም እነሆ በዚህ ጉዳይ ሁለተኛዋ ጠቅላይ ሚኒስትር በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ። ይህ ለእኛ ትልቅ ትምህርት ነው።