By Zaggolenews. የዛጎል ዜና

ሰሞኑን በአገሪቷ እየተናፈሱ ካሉት ወሬዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ መመስረት አንደኛው ነው። ከዚህ በፊት የተለያዩ ፓርቲዎች እንዳቋቋሟቸው ህብረት፣ ቅንጅት፣ አማራጭ ኃይሎች፣ መድረክን እንደመሳሰሉት ፓርቲዎች ሁሉ ይህም እንደነሱ ይዳከማል ይፈርሳል፤ የሚሉ ግምቶች በአንድ በኩል ሲኖሩ በተቃራኒው አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ኢዜማ የተሻለ ሊሆን ይችላል የሚሉም አልታጡም።

 በኢትዮጵያ የፓርቲዎች ታሪክ ውስጥ ከተለያዩ ፓርቲዎች ተቀናጅተው የሚመሰረቱ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ውጪ አንድ ፓርቲ ሆነው በመዝለቅ መንግሥት ሲመሰርቱ አልታየም። ይልቅ የመፈረካከስ እና የመሰንጠቅ አደጋ ሲያጋጥማቸው ተስተው ሏል። ኢዜማ ግን እንዲህ እንደማይሆን እና መንግሥት እስከመሆን ሊዘልቅ እንደሚችል የተናገሩት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ ናቸው። ይህንን እና ሌሎች ጥያቄዎችን አክለን ከኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ ጋር ቃለምልልስ ያካሄድን ሲሆን፤ ከኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ ጋር የነበረንን ቆይታ እንዲህ አቅርበንላችኋል።

አዲስ ዘመን፡- የኢዜማ የመመስረት ዓላማ ምንድን ነው?

ዶክተር ጫኔ፡- በዜግነት እና በግለሰብ መብት ላይ ትኩረት አድርጎ የቡድን መብትን ማረጋገጥ የሚችል አንድ ሁሉን አቀፍ ፓርቲ መመስረትን ዓላማው አድርጓል። ከዚህም ባሻገር ፕሮግራሞቹ በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለውን ምስቅልቅል ለማስቀረት በሕዝብ ውሳኔ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝምን ማደራጀትንም ያካተተ ነው። የአገሪቷ መሪ አመራረጥ ፕሬዚዳንታዊ እንዲሆን እና ተጠሪነቱም ለሕዝብ እንዲሆን የማድረግ ፍላጎትም አለው። በተጨማሪ ማህበራዊ ፍትህ የማስፈን ዓላማንም አንግቧል። ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰውን ሀብታም እና በዝቅተኛ ደረጃ ያለውን ድሃውን በማመጣጠን ምስቅልቅሉን ያቃልላል። የኢኮኖሚ ሥርዓቱን ቢያንስ ድሃው ኅብረተሰብ መካከለኛ ገቢ ወደሚባለው የኑሮ ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግ አቅዷል። ዓላማው ድሃውን ተጠቃሚ ማድረግ፤ አቅርቦት እና ፍላጎትን ማጣጣም፤ መንግሥት በሕግ በተወሰነ ደረጃ ድሃውን ሊረዳየሚችልበትን የኢኮኖሚ መዋቅር መቅረፅ እና ማስተካከል በዚህም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ነው።

አዲስ ዘመን፡- ማህበራዊ ፍትህ ማስፈን እና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ሲሉ በምን መልኩ እንደሆነ በደንብ አብራሩት?

ዶክተር ጫኔ፡- ማህበራዊ ፍትህ ሲባል በትርጉም ደረጃ ማህበራዊ ነክ ጉዳዮችን ብቻ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ማህበራዊ ፍትህ ያጣውን ሕዝብ ተጠቃሚ እናደርጋለን ስንል በኢኮኖሚ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ማለታችን ነው። በተለያየ ምክንያት የገበያ ሥርዓቱ አንዴ እላይ አንዴ እታች የሚወጣበትን ሁኔታ ማስተካከል ያስፈልጋል። ድሃው ኅብረተሰብ ውስጥ ሴቶች እና ሕፃናት፣ ሥራ አጥ ወጣቶች፣ አዛውንት እንዲሁም ልዩ ትኩረት የሚሹ የአካል ጉዳተኞች በግለሰብ ደረጃ መብታቸው የሚከበርበት ሁኔታ መኖር አለበት ብለን እናስባለን።

በአጠቃላይ እነዚህ ሰዎች በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በመሳሰሉት ዙሪያ እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ሥርዓት ተዘርግቶ ድጋፍ የሚሹትምርት ውስጥ ገብተው ራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቶ እና ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል ዓላማችን ነው። ይህ እንዳይጓደል መልካም አስተዳደር ሰፍኖ ራሳ ቸው ሊመራቸው የሚፈልጉትን መምረጥ እና የማይፈልጉትን ማውረድ የሚችሉበትን ቀጥተኛ ተሳታፊ የሚያደርጋቸውን የፖለቲካ ሥርዓት በመመስረት በአቅም እና በብቃት ላይ የተመሰረተ ከባቢያዊ መስተዳድርን መመስረት እንዲችሉ ያንን መሠረት አድርገን እንሰራለን።

አዲስ ዘመን፡- ጥሩ! ከአሁኑ ኢዜማ በፊት ህብረት፣ ቅንጅት፣ አማራጭ ኃይሎች፣ መድረክ እና ሌሎችም የፓርቲ ስብስቦች ነበሩ። ብዙዎቹ ግባቸው ምርጫን ማሸነፍ በመሆኑ ከምርጫ በኋላ መሰነጣጠቅ እና መዳከም ታይቶባቸዋል። እናንተ ደግሞ እንደገለፁልኝ መንግሥት ሆናችሁ ማህበራዊ ፍትህ የማስፈን ግብ አለን ብላችኋል። በእርግጥ መበታተን የኢዜማ ስጋት አይደለም?

ዶክተር ጫኔ፡- ልክ ነው፤ እንዲህ ዓይነት ታሪክ ነበረ። የምርጫ 97ትን ታሪክ እንደማስተማሪያ በመቁጠር ሂደቱን ለማስተካከል በጣም ጥንቃቄ በማድረግ ምህዳሩን በማስፋት ቀድሞ ለማሰብ ጥረት አድርገናል። ቅሬታዎች ሲፈጠሩ እንዴት ይፈታሉ? የሚለውን አስቀድሞ በማሰብ ላለመፈረካከስ ከየት መጀመር እንዳለበት ተለይቷል። ስለዚህ መጀመሪያ አዲሱን ፓርቲ ለመመስረት ፈቃደኛ የሆኑ ሁሉም ፓርቲዎች የአባሎቻቸውን መረጃ በመሰብሰብ በወረዳ ደረጃ የማቀላቀል ሥራ ሰርተዋል።

አንድ ላይ አባሎቻችንን ካዋሃድን በኋላ አንድ የበፊት አመራር ችግር ልፍጠር እንኳ ብሎ ቢነሳ ፓርቲውን የመፈረካከስ ዕድሉ አይኖረውም። ምክንያቱም ቀድሞ በወረዳ ደረጃ አባላቶች ስለተዋሃዱ እና በወረዳ ደረጃ ራሳቸውን እንዲመሩ ሥራ አስፈፃሚ ስለተመረጠ የሁሉም የፓርቲ አባላቶች ተሳትፎ ወረዳ ላይ የሚያበቃ በመሆኑ የግለሰቦች አለመግባባት ፓርቲውን አይሰነጥቀውም።

ፓርቲውን በወረዳ ደረጃ የሚመሩ አባላት 3 ወንድ፣ ሴት እና አካል ጉዳተኛ ካላቸው አንድ አንድ ጨምረው በአጠቃላይ ከየወረዳው አምስት ሰው ተወክሎ ለጠቅላላጉባኤው መጥቷል። እኔም የመጣሁት በዚያ መልኩ በወረዳ ተወዳድሬ ነው፤ ሌሎቹም እንደዚያው፤ የተወዳደርነው ደግሞ እንደግለሰብ ነው። ባለን የፖለቲካ ተሞክሮ እና በነበረን ቁርጠኝነት የወረዳ አባላቱ በአብላጫ ድምፅ መርጠውናል። መሪዎቹም የተመረጡት በዚሁ መልክ ነው። ከዚህ በኋላ አንድ የፓርቲ መሪ አፈንግጫለሁ ቢል የሚነጠለው ግለሰቡ እንጂ ፓርቲው አይወጣም። ስለዚህ በዚህ መልኩ ቀድመን ስለሰራን የመፈረካከስ ሁኔታ አይፈጠርም።

አዲስ ዘመን፡- የተመረጠው እንደግለ ሰብ ነው። አንድ የፓርቲ አመራር ቢያፈነግጥ የሚወጣው ራሱ ነው ቢሉም ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ መሪ፣ ምክትል መሪ፣ ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር እያላችሁ የሥልጣን ክፍፍል አድርጋችኋል። ብዙ ጊዜ ፓርቲዎች ሲቀናጁም ሆነ ሲዋሃዱ ልዩነት የሚመ ጣው እኔ ልምራ እኔ ልምራ በሚል ነው። ይህ ችግሩን ለማቃለልና ለማቻቻል ነው? ወይስ በእርግጥ ለምን ይህን ያህል አመራር ተመረጠ?

ዶክተር ጫኔ፡- ይሄ ቀደም ሲል የነበረው የፖለቲካ ሥርዓታችን የፈጠረው አስተሳሰብ እንጂ የአሁኑ እንደውም ትክክለኛ እና ዓለም አቀፋዊ አካሄድ ነው። የፓርቲ መሪ እና የፓርቲ ሊቀመንበር የሚለው ሥልጣንን ለመከፋፈል አይደለም። የፓርቲ መሪ የሚለው መንግሥታዊ መዋቅርን ይዞ የሚሄድበመንግሥት ሥራ ውስጥ የፓርቲን ጣልቃ ገብነት የሚከላከል ነው። አሁን እንደሚታየው በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ የኢህአዴግ መሠረ ታዊ ድርጅት እዚያው ውስጥ አለ፡ በቢሮ ደረጃ አንድ ለአምስት ውስጥ ሳይቀር አደረጃጀት ውስጥ እስከታች ኢህአዴግ ወርዷል። ያ ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲኖር አድርጓል። ነገር ግን ሊቀመንበሩ የፓርቲ ሥራውን ሲሰራ የመሪው ድርሻ ግን በአጠቃላይ መንግሥታዊ የሆኑትን በሚኒስትር ደረጃ ያለውን ይሰራል። ከወዲሁ በፌዴሬሽን፣ በተወካዮች ምክር ቤት ደረጃ በአጠቃላይ ምርጫን የተመለከተውን በሙሉ መንግ ሥታዊ መዋቅሮችን በሙሉ ተከትሎ የሚሰራው የፓርቲው መሪ ነው። በአ ሜሪካ ትራምፕ የፓርቲ መሪ ነው የሪፐብ ሊካን ሊቀመንበር ደግሞ ሌላ ነው። እንግሊዝ ላይ ትሬሳ ሜይ የፓርቲው መሪ ናት፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ደግሞ ሌላ ነው።

እኛ ለሙስና በር እየከፈትን ለራሳችን እንዲመቸን እየደረብነው እንጂ አካሄዳችን ትክክል አልነበረም። እኛ ግን የምንፈልገው የፓርቲውን እና የመንግሥትን ሥራ መለየት ነው። ስለዚህ አካሄዳችን የፖለቲካ አደረጃጀቱን ለይቶ የሚሰራ በመሆኑ ትክክለኛ አካሄድ ነው። ሕዝብን ግራ ሳያጋባ የመንግሥት አደረጃጀት እና የፓርቲ አደረጃጀትን ለይቶ የሚሄድ ሲሆን፤ ይህ ለኢትዮጵያ በትክክል ይመጥናል። ይህ ሥልጣንን ለመከፋፈል አይደለም። በወረዳ ደረጃ ሳይቀር ይህን አደረጃጀት የምንጠቀም ሲሆን፤ የመንግሥት አሠራር በፓርቲ ተፅዕኖ ውስጥ እንዳይገባ ነፃና ገለልተኛ የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር እንዲኖር ታስቦ የተሰራ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁን አንድ ብትሆኑም ሰባት ቀድሞ ስለነበራችሁ የነበራችሁ ዓላማ፣ግብ እና ስትራቴጂ የተለያየ ነበር። አሁን በእርግጥ ዓላማችሁ አንድ ዓይነት ሆኗል?

ዶክተር ጫኔ፡- ከዚህ በፊት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አካሄድ አንዳንዶቹለዘብተኛ ሊብራሊዝምን ሌሎቹ ደግሞ ቀጥተኛ ሊብራሊዝምን ኢትዮጵያ ላይ እንተገብራለን ብለው የሚታገሉ ናቸው። ነገር ግን ነባራዊውን ሁኔታ ከግምት ያስገባ አልነበረም። ምክንያቱም ሊብራሊዝም በራሱ ነፃ የገበያ ሥርዓት ይፈልጋል። በውድድር አብዛኛው ኅብረተሰብ ሀብት ማፍራት የሚችልበትን ሁኔታ የሚፈጥር ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ይህ በአሁኑ ሰዓት የሚያራምድ አይደለም። ከ85 በመቶ በላይ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ነው። መካከለኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ በብዛት ያልተፈጠረበት እና መካከለኛ ገቢ ውስጥ የገባው ሰው ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ሊብራሊዝም ወይም ነፃ ገበያ ቢተገበር ለጥቂት ባለሀብቶች ተገዢ የመሆን ሥርዓት ስለሚፈጥር አያዋጣም።

ለምሳሌ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ዓላማው ከሶሻል ዴሞክራሲ ተነስቶ ለዘብተኛ ሊብራሊዝምን ማራመድ ነበር። ይህን ሲል ግን በሕግ በተገደበ መልኩ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል ይላል። አሁን ግን የሕዝቡ ኑሮ እስኪሻሻል ያንን ማድረግ እንደማይቻል በመወያየት ለማህበራዊ ፍትህ ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት መተማመን ላይ ተደርሷል። ሌሎች አገሮች በአጭር ጊዜ ከድህነት የተላቀቁበት አስተሳሰብ ማህበራዊ ፍትህ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ሁሉም ሊስማማበት ችሏል። ስለዚህ የብዙኃኑ የኑሮ ደረጃ እስኪሻሻል ይህ የተሻለ ነው በሚል አገሪቷን ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉም መስማማት ተደርሷል።

አዲስ ዘመን፡- ፌዴራሊዝም ላይ ያላችሁ አቋምስ ምንድን ነው?

ዶክተር ጫኔ፡- ፌዴራሊዝም ለአስተዳ ደር አመቺ በመሆኑ እኛም የምንከተለው የፌዴራሊዝም አወቃቀርን ነው። የመል ካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ሰው በየአካባቢው የሚተዳደርበትን እና የሚመራበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ለአስ ተዳደር አመቺነት እጅግ ወሳኝ ነው። ነገር ግን ፌዴራሊዝምን እንከተላለን ብንልም እኛ ኢህአዴግ የዘረጋውን ቋንቋ፣ ዘርን እና ብሔርን ማዕከል ያደረገ አከላለልን አንጠቀምም።

ይህ ብሔርን ማዕከል ያደረገ አካሄድ ትክክል ባለመሆኑ ላለፉት ሦስት ዓመታት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት አጥፍቷል። ስለዚህ ይህ ለኢትዮጵያ አይበጅም የሚል እምነት አለን። ከዚያ ይልቅ ፌዴራሊዝሙ ለአስተዳደር እና ለልማት አመቺ በሆነ መልኩ፤ አብሮነትን የሚያጠናክር፣ የሰው ኃይል ፍሰትን መሠረት አድርጎ ለመጠቃቀም በሚበጅ መልኩ እንዲካሄድ እንፈልጋለን። ምናልባት መልክአ ምድራዊ ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ተራራ ጀርባ ከዚህ ወንዝ ጀምሮ በማለት የአካባቢው ሰው አካባቢውን እንዲያስተዳድር እናደርጋ ለን። ከዚህ ውጪ ዘርን ማዕከል ያደረገ አከላለል ለግጭት ለሞት ለስደት የዳረገ በመሆኑ መቆም አለበት የሚል እምነት አለን።

አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ ፌዴራሊ ዝሙን ከብሔር ውጪ በመልከአምድር እናድርግ እንደተባለው ማድረግ ይቻላል? ለ27 ዓመታት አማራነት፣ ኦሮሞነት፣ ደቡብነትም ሆነ ሶማሌነት ተገንብቷል። ያንን ማጥፋት ይቻላል? ተቀባይነቱስ እንዴት ይሆናል?

ዶክተር ጫኔ፡- ይህ የፖለቲካ መሪዎች አምጥተው የጫኑት እንጂ ሕዝብ የፈለገው አይደለም። እውነት ለመናገር የብሔር ፌዴራሊዝም የሕዝብ ፍላጎት አይደ ለም። የአማራ ብሔር፣ ይሄ የኦሮሞ ብሔር ተባለ ደቡብ ሲደረስ ደግሞ 56 ብሔረሰብ ተጨፍልቆ በአንድ ላይ ተቀምጧል።

አመሰራረቱ ቋንቋ ቢሆንም ደቡብ ላይ ደግሞ ቋንቋ መሠረት አልተደረገም። አማራ ውስጥም አማራ በሚል ቢካለልም በክልሉ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች አማራ እየተባሉ ነው። ይህ ደግሞ ግጭት እየፈጠረ ይገኛል። የአገው ብሔረሰብ አማራ አይደለሁም ቢል መከልከል አይችልም። የቅማንት ጉዳይም አለ። የጉሙዝ፣ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ አሶሳ ላይ አብረው መኖር ይፈልጋሉ። ነገር ግን መዝረፍ እና መግረፍ የሚፈልጉ የፖለቲካ ቡድኖች የብሔር ግጭትን በማምጣት መሸሸጊያ አድርገው በብሔር እየከፋፈሉ መቆየት ይፈልጋሉ። ይህ የሕዝብ ፍላጎት አይደለም። ይህ መቆምአለበት፤ የሕግ የበላይነት መስፈን አለበት። ኅብረተሰቡ የምኖረው እዚህ አካባቢ ነው ካለ አትኖርም ብሎ መከልከል አይቻ ልም።

ደቡብ ክልል ውስጥ ተደጋጋሚ በር ካታ የክልል እንሁን ጥያቄ እያቀረቡ ነው። በቀረበው ጥያቄ መሠረት ከ50 በላይ ክልል ማዋቀር ይቻላል ወይ? ለሁሉም ክልል ሁኑ ብሎ ቢፈቀድ ኢኮኖሚው ያንን ማድረግ ይችላል? ከዚያ ይልቅ የተለያዩ መስተጋብሮች አሉ። ዝምድናችን፣ መዋለዳችን፣ የንብረት ዝውውራችን፣ የገበያ መስተጋብራችንን ማጎልበት እና ማስተካከል ይገባል። ስለዚህ ኢህአዴግም ቢሆን አካሄዱን ማሻሻል አለበት። ሕገመንግሥቱ ሊሻሻል ይገባል። ለዚህ መፍትሄ የሚሆን አጠቃላይ መልካም አስተዳደርን የሚያሰፍን የመፍትሔ ፌዴራሊዝም አካሄድ ሲኖር ነው። ኢዜማ የመፍትሔ ፌዴራሊዝም እንደሚያመጣ በፖሊሲ ትንተናው ላይ አስቀምጧል። ወደ ፊት በማኒፌስቶ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል። ኢዜማ ወደ ፊት ያንን የምርጫ መወዳደሪያው ያደርገዋል።

አዲስ ዘመን፡- ኢዜማ አሁን ያሉትን የክልል እንሁን ጥያቄዎች ሊያስቀር በሚችል መልኩ አዲስ ፌዴራሊዝምን ያዋቅራል ማለት ነው። ጥያቄያቸውስ እንዴት ይሆናል?

ዶክተር ጫኔ፡- ይህ የሚሰጠው ለሕ ዝቡ ነው። ሲዳማ ክልል ልሁን ካለ ክልል የመሆን ደረጃዎች አሉ። ኅብረተሰቡን በትክክል ሊያስተዳድር የሚችል መሆኑን፣ የኢኮኖሚ ምንጭ ያለው መሆኑን፣ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ያለው መሆኑን፤ ከፌዴራል ጋር ያለው ትስስር ታይቶ እና ክልል መሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደማይፈጥር ተረጋግጦ ክልል መሆን ይችላል። ነገና ወደፊት ሕዝቡ ፌዴራል መንግሥቱን እንዳይጠይቅ ሪፈረንደም ተደርጎ በሕዝብ ውሳኔ ክልል ማድረግ ይቻላል። ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ከ84 ያላነሱ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ።

 ሁሉም ክልል እንሁን ቢሉ ይህንን ማድረግ ይቻላል ወይ ቢባል አይቻልም። ይልቁኑ በመልከአ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በአብሮ የመኖርእሴት በቋንቋ ትስስር የተሻለ አካባቢውን ሊያለማ እና ሕዝቡን ሊጠቅም የሚችል ትስስር ከተፈጠረ ግን ጥያቄው እየቀረ ይሄዳል፤ ዋነኛው ጉዳይ የኢኮኖሚ ጥያቄ ብቻ ይሆናል። መንግሥት አካባቢውን እያለማ የአካባቢውን ኅብረተሰብ ካሳደ ገው ጉዳዩ ይሟሽሻል። ይህ ካልሆነ ግን በትልልቅ ክልሎች ውስጥ ራሱ መሰነ ጣጠቅ አለ። አማራም ሆነ ኦሮሞ ሦስት አራት ቦታ የሚሰነጣጠቅበት ዕድል በጣም ሰፊ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢዜማን ምርጫ ቦርድ ያውቀዋል?

ዶክተር ጫኔ፡- በመሠረቱ ምርጫ ቦርድ ሊያዘን አይችልም። ነገር ግን ሌሎች ፓርቲዎች በራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በጠቅላላ ጉባኤያቸው ወስነው አዲሱን ፓርቲ ለመመስረት ፈቃደኛ በመሆናቸው ከታች ከወረዳ ጀምሮ አባላትን ማዋሃድ ተችሏል። በአዲስ ፎርም አባላት የሰማያዊ፣ የኢዴፓ ተብለው ሳይከፋፈሉ ሁሉም የኢዜማ አባል ሆነው ተመዝግበዋል።

አዲስ ዘመን፡- ነገር ግን ቀድመው ሰባቱ ፓርቲዎች ኢዜማ ከመሆናቸው በፊት ከስመዋል?

 ዶክተር ጫኔ፡- ይህንን በየፓርቲያ ቸው መጠየቅ ይሻላል። እኛ ስናስተሳስር ፓርቲዎች በጠቅላላ ጉባኤያቸው ራሳቸ ውን አክስመው አዲስ ተመስራች ፓርቲ ውስጥ መግባት አለብን ብለው የወሰኑበትን ሪፖርት ያመጡ ፓርቲዎች በአዲሱ ፓርቲ ውስጥ እንዲገቡ አድርገናል።

አዲስ ዘመን፡- ኢዴፓስ በትክክል ፈርሷል?

ዶክተር ጫኔ፡- አዎ መጋቢት 1 ቀን በጠራነው ጉባኤ ፈርሷል። ፓርቲው ከመጋቢት 1 በኋላ ያሉትን ንብረቶች የሂሳብ ሪፖርቶችን አጣርቶ ለአዲሱ ፓርቲ ሀብት ሆነው እንዲዘዋወሩ ወስኖ ያንንም የሚያደርግ ሦስት አባላት ያሉት ኮሚቴ መርጦ ወደ አዲሱ እንዲዘዋወር ወስ ኗል። ይህን ሃሳብ ያቀረበው ደግሞ ራሱ ጉባኤው ነው።

አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2011