አቶ ገዱ አንዳርጋቸው – ከዱሮ እስከ ዛሬ ሃቁን ይፋ አደርጉ

By Zaggolenews. የዛጎል ዜና

‹‹አማራ ሊወርህ ነው፤ ተነስ! ታጠቅ›› እያሉ ሕዝቡን እየቀሰቀሱ እንደ ሆነ የትግራይን ሕዝብ ወንድሙ በሆነው የአማራ ሕዝብ ላይ ለማዝመት እየተዘጋጁ እንደ ሆነ አውቃለሁ… የክልላችን ምክር ቤት በዝግ ተወያይቶበታል፤ የውስጥ ሰላማችንንና አንድነታችንን ከሚፈታተኑ አደገኛ አዝማሚያዎች እንዴት መጠበቅ እንዳለብንም አይተናል። የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የክልሉ ኢኮኖሚም ሆነ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታው መሸከም ከሚችለው በላይ ሠራዊት እያሠለጠነና እያስታጠቀ መሆኑን በበቂ ማስረጃና መረጃ አረጋግጠናል…

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራን ክልል በርዕሰ መስተዳድርነት ለአምስት ዓመታት ሲመሩ ቆይተው በቅርቡ ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸውአስረክበው ለጊዜው በእረፍት ላይ ይገኛሉ፤ ገና የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ጸረደርግ ትግሉን የተቀላቀሉት አቶ ገዱ የት እንደ ተወለዱ፣ የትእና ምን እንደ ተማሩ፣ በምን በምን የሥራ ዘርፎች እንዳገለገሉና የቤተሰባቸው ሁኔታ ምን እንደሚመስል፣ በአሁኑ ወቅት ለምንሥልጣናቸውን ማስረከብ እንደፈለጉ ጠይቀናቸው ዝርዝር መልስ ሰጥተውናል፤ 

ተወልድው ያደጉት በቀድሞው አጠራር ወሎ ክፍለ ሀገር ዋድላ ድላንታ አውራጃ ዳውንት ወረዳ በአሁኑ ደግሞ ሰሜን ወሎ ነው፤ መጀመሪያ የቤተክርስቲያን ትምህርት ተማሩ። ከዜያም ወደ መደበኛው ትምህርት ተዛወሩ። የመጀመሪያ ደረጃትምህርታቸውን ዳውንት አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ወገል ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተማሩ። አስራ አንደኛ ክፍል እያሉ ማለትም በ1982 ዓመተ ምህረት አካባቢውን ኢህአዴግ ሲቆጣጠረው ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ትጥቅ ትግሉ ገቡ፤ ያቋረጡትን የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የቀጠሉት መደበኛ በሆነ መንገድ እንደሆነ ይናገራሉ።

ወደ ስራው ዓለም ከገቡ በኋላ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ  በልማት አስተዳደር / ዴቨሎፕመንት አድሚኒስትሬሽን/ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከዚያም ስራ ተመድበው ከቆዩ በሁዋላ በ1997 ዓመተ ምህረት  በተቋማዊ አስተዳደር /ኦርጋናይዜሽናል ሊደርሽፕ/ አሜሪካን አገር ከሚገኝ ፓስፊክ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ ማግኘት ችለዋል።

በወረዳ፣ በዞን ደረጃ በፖለቲካና በአስተዳዳሪነት ሰርተዋል።   ጀምሮ በተለያዩ ሃላፊነቶች ሲሰሩ ቆይተው በ1997 ዓመተ ምህረት መጨረሻ አካባቢ የአማራ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ ፣  ከዛም በክልሉ የፓርቲው ጽሕፈት ቤት እስከ 2001 ዓመተ ምህረት ካገለገሉ በሁዋላ ከ2001 እስከ 2006 ዓመተ ምህረት በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት የአማራ ክልልን መሩ። ከ2006 ታህሳስ እስከ የካቲት 2011 ዓመተ ምህረት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነበሩ።

ዘመን፡– ከብዙጊዜዕረፍትየለሽሥራበኋላነውዕረፍትየወጡት፤ዕረፍትእንዴትይዞዎታል?

አቶገዱ፡– እስከ አለፉት ሶስት ቀናት ድረስ (ቃለ ምልልሱን በ10/07/11 ነበር ያደረግንላቸው) የጀመርኋቸው ስራዎች ስለነበሩ እነሱን በማጠቃለል ላይ ነበርሁ፤ ዕረፍቴን ከጀመርሁ ሁለት ሶስት ቀን ሆነኝ። ለብዙ ዓመታት ፋታ አልነበረኝም። አሁን ቢያንስ ከቤተሰቦቼ ጋር የምመካከርበት፣ የምንነጋገርበት፣ ቤተሰብ የምጠይቅበት ጊዜ ነው፤ የማነባቸውን መጻሕፍት የማደራጀት ሥራም እየሰራሁ ነው፤ እና የእረፍቱ አጀማመር በጣም ቆንጆ ነው።

ዘመን፡– የቤተሰብጉዳይካነሱአይቀርየቤተሰብሁኔታዎምንይመስላልʔ አግብተዋልልጆችስአሉ?

አቶገዱ፡– አዎ ባለትዳር ነኝ፤ ሁለት ሴት ልጆችም አሉኝ፤ የወንድም፣ የእህት፣ የዘመዶች ልጆችም ከኔ ጋር አሉ።

ዘመን፡– ዕረፍትሲያገኙቤተሰብምንተሰማውʔ

አቶገዱ፡– በጣም ደስተኛ ነው የሆኑት፤ ስራ ላይ የቆየሁበት ጊዜ በጣም የተጨናነቀ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ በተከሰተው የለውጥ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊትም ዕረፍትም ፋታም አልነበረኝም። አብዛኛውን ጊዜ በስራ ነበር ያሳለፍሁት። በዚህ ምክንያት ከቤተሰብ ጋር የነበረኝ ግንኙነት ቁጭ ብሎ ለመነጋገር የሚያስችል አልነበረም። ሰሞኑን የተፈጠረውን አጋጣሚ /ዕረፍት መሆኔን/ ቤተሰቦቼ በከፍተኛ ደስታ ነው የተቀበሉት፤ ለማኅበራዊ ግንኙነታችን የተሻለ ጊዜ አድርገው ነው የወሰዱት።

ዘመን፡– ለዘመድለቅሶወይምሰርግሄደውያውቃሉʔ

አቶገዱ፡– አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ሰርግም ለቅሶም ብዙም አልሄድም። እንደምታውቀው ይሄ በእኛ ባህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፤ አብዛኛውን ጊዜ ይህንን የምትሸፍነው ባለቤቴ ነች እንጂ እኔ በለቅሶውም በሰርጉም በማኅበራዊው ኑሮ በኩል ደከም ያልሁ ነኝ ማለት እችላለሁ።

ዘመን፡– የክልሉሕዝብለእርስዎከፍተኛአክብሮትእናፍቅርእንዳለውይገለፃል።በግራምበቀኝምየሚነሱጉዳዮችአሉ።ክልሉውጥረትውስጥየገባበትበሚመስልወቅትየእርስዎከኃላፊነትመነሳትትክክልነውብለውያምናሉʔ

Lema-Gedu-Abiy

አቶገዱ፡– ለክፉ ውጥረት ዳርገውኝ የነበሩ ዓመታት አልፈዋል ብዬ ነው የማስበው፤ አካባቢውም አሁን በአብዛኛው ሰላም የሰፈነበት ነው። እርግጥ አሁንም የተወሰነ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች አሉ፤ 2007፣ 2008፣ 2009፣ እና 2010 ዓመተ ምህረትም በተወሰኑ አካባቢዎች ችግሮች ነበሩ። አሁን በንፅፅር ከተመለከትነው የተሻለ ወቅት ነው። እናም በዚህ ወቅት የእኔ ከኃላፊነት መልቀቅ ተገቢነት አለው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ከ1998፣ 1999 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በክልሉ ውስጥ ከመጀመሪያው ረድፍ፣ ቁልፍ በሆነ ኃላፊነት ላይ ነበርሁ። ወይም ደግሞ ቁልፍ ከሆነው የክልሉ ኃላፊነት ቦታ ላይ ነው የቆየሁት። በክልሉ በተካሄዱ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የዴሞክራታይዜሽን፤ በአጠቃላይ በጥሩውም፣ በመጥፎውም ላለፉት አስራ ሁለት አስራ ሶስት ዓመታት በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ነው የቆየሁት፤ ረጅም ጊዜ አገልግያለሁ። ረጅም ጊዜ በወንበር ላይ መቆየት ደግሞ በአንድ በኩል በሕዝብ ዘንድ እንድሰለች ያደርገኛል፤ ለራሴም ቢሆን ተመሳሳይ ህይወት አሰልቺ ነው፤ መሰለቻቸት ሲፈጠር በሥራ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፤ ያኔ የወደደኝ፣ ያከበረኝ ሁሉ ሊጠላኝ ይችላል፤ ያ ከመሆኑ በፊት ቦታውን ለሚመጥን ሰው ማስረከብ ነበረብኝ።

ስለዚህ በየጊዜው በተለይ ቁልፍ ቦታ ላይ ያለ አመራር የተወሰነ ጊዜ አገልግሎ ለሌላ በአዲስ መንፈስ፣ በትኩስ ወኔ ኃላፊነቱን ቢያስረክብ ኅብረተሰቡን ወደ ፊት በማራመድ ረገድ የተሻለ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ጊዜውን እየቆጠርሁ ‹‹ይችኛይቱን ልለፋት ይሄኛውን›› እያልሁ የምቀጥል ከሆነ የወንበር በሽታ ይመጣል፤ ይሕ የአፍሪካ መሪዎችን የሚጠናወት ደዌ መሆኑ ታውቋል። እናም የወንበር በሽታ ይዞኝ እዚያው ወንበር ላይ መሟሟት እንዳይመጣ በማሰብ ነው ኃላፊነቴን ያስረከብሁ። የለቀኩበት ወቅትም በጣም ተገቢ ወቅት ነው። የአማራን ሕዝብ መምራቴ ለእኔ እንደ ትልቅ እድል ነው የምቆጥረው።

ይህን ያህል ጊዜ በኃላፊነት ስመራ ከህብረተሰቡ ጋር በጥሩ ግንኙነት በመቆየቴ እድለኛ ነኝ ብዬ መውሰድ እችላለሁ። በመንግሥቱም በድርጅቱም መዋቅር በኅብረተሰቡ ዘንድ በበጎ የምታይ ሰው ሆኜ እና የተለያየ ድጋፍ እየተደረገልኝ፣ አንዳንድ ጊዜም ደፈር ያሉ ውሳኔዎችን እንድወስን ማበረታቻ ከህብረተሰቡና ከአመራሩ ስለነበረኝ ትልቅ ክብር አድርጌ ነው የምወስደው፤ ያም ሆኖ ግን ሕብረተሰቡ የሚደግፈኝ፣ የሚፈልገኝ፣ የሚወደኝም ቢሆን፣ የሚያከብረኝም ቢሆን፤ ሁልጊዜ ወንበር ላይ መቆየት ጠቃሚ ነው ብዬ አላምንምና በዚያ ምክንያት ነው። አንድ ቦታ ላይ ረጅም ጊዜ ከማገልገል እየቀያየሩ ሕዝብን ማገልገል ይቻላል የሚል እምነት ስላለኝ ነው።

ዘመን፦ክልሉንበመሩባቸውዓመታትገጠመኝየሚሉትከባድነገርምንነበር?

አቶገዱ፦በሥራ ዓለም በቆየሁባቸው ዘመናትም ሆነ ክልሉን በኃላፊነት በመራሁባቸው አምስት ዓመታት እንደ 2008 ዓ.ም. አይነት ፈተና በፍጹም ገጥሞኝ አያውቅም፤ ጊዜው እጅግ በጣም ፈታኝ ነበር። ሁኔታውን ከባድ ያደረገው በየጊዜው እየተጠየቁ መልስ ያልተሰጠባቸው በርካታ የሕዝብ ፍላጎቶች ነበሩ፤ ለኅብረተሰቡ ጥያቄዎች አለመመለስ ዋናው ምክንያት ጥያቄዎችን አሳንሶ የመመልከት ችግር ስለነበረ ነው። የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት በወቅቱ አለመመለሱ ደግሞ ቅራኔዎች እየተባባሱ እንዲመጡ ሰፊ ዕድል ፈጠረ፤ እናም ታምቆ፣ ታፍኖ የኖረው የሕዝብ ስሜት ድንገት እንደ እሳተ ገሞራ ፈነዳ።

ያንን ተከትሎም ክቡር የሆነው የወገኖቻችን ሕይወት ጠፋ፤ በርካታ ንብረት ወደመ፤ ያ ጊዜ እጅግ በጣም ያሳዝነኛል፤ ይጸጽተኛል፤ የሕዝቡን ፍላጎት በወጉ መረዳትና ጥያቄዎቹን በወቅቱ መመለስ ቢቻል ኖሮ ያ ሁሉ አሳዛኝ ክስተት እንዲፈጠር ምንም እድል ሊኖረው አይችልም ነበር። በውቅቱ በተፈጠረው ግርግር ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆች እጅግ በጣም ያሳዝኑኛል፤ ጥረው፣ ግረው ያፈሩት ንብረት ወድሞ ሰላማዊ ዜጎች ባዶ እጃቸውን ቀርተው ሲያዝኑና ሲቸገሩ ማየት ጤናማ አእምሮ ላለው ሁሉ የሚዘገንን ነበር።

የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት በወቅቱ አለመመለሱ ደግሞ ቅራኔዎች እየተባባሱ እንዲመጡ ሰፊ ዕድል ፈጠረ፤ እናም ታምቆ፣ ታፍኖ የኖረው የሕዝብ ስሜት ድንገት እንደ እሳተ ገሞራ ፈነዳ።

የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት ትኩረት ተሰጥቶት በየመድረኩ የሚያነሳቸው ጥያቄዎቹ በውቅቱ ተመልሰው ቢሆን ኖሮ ያን ያህል የሰው ሕይወት አይጠፋም፤ ያን ያህል ንብረትም አይወድምም ነበር፤ እና 2008 ዓ. ም. በሕይወቴ ሙሉ የማልረሳው ዘግናኝ ወቅት ነበር። ሁኔታውን የከፋ የሚያደርገው በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያለን ያንን አስቀያሚ አጋጣሚ ማየት በጣም ይዘገንን ነበር።

ዘመን፦የተደሰቱባቸውጉዳዮችይኖሩይሆን?

አቶገዱ፦በ2008 ዓ. ም ያንን የመሰለ አሳዛኝ ወቅት አልፈን በ2010 መጋቢት መጨረሻ አካባቢ የነበሩት ዕለታት በጣም ውጤታማና ከልቤ የተደሰትሁባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ እውነት ለመናገር እንደ ሕፃን የፈነደቅሁባቸው ሳምንታትና ዕለታት ስለነበሩ መቼም ልረሳቸው አልችልም። የደስታዬ ምክንያቱ ወደአስፈሪ አዘቅት እየተገፋች የነበረችው ሀገራችን ወደነበረ ክብሯ ልትመለስ የምትችልበት ተስፋ የታየበት እድል ስለፈጠርን ነው።

ለአስራ ሰባት ዕለታት ከፍተኛ ፍጭት ካደረግን በኋላ ሊታሰብ ከማይችል ውሳኔ ላይ መድረሳችን፣ እሱን ተከትሎ የመጣው ዘርፈ ብዙ ለውጥ፤ ለምሳሌ በሌሉበት ሞት ተፈርዶባቸው የነበሩ ፖለቲከኞች ወደሀገራቸው ገብተው በሀገራቸው ጉዳይ በሰላም እንዲወያዩ መደረጉ፣ እንዲዘጉ በይፋ ተወስኖባቸው የነበሩ መገናኛ ብዙኃን ከስደት ተመልሰው በነጻነት እንዲሠሩ እድል ማግኘታቸው፣ በሰባራ ሰንጣረው እየታፈሱ እስርቤት ታጉረው የነበሩ ዜጎች ሁሉ እንዲፈቱ መደረጉ፣ በዚህም በእየእስር ቤቱ ሲፈጸም የነበረውን ዘግናኝ ገመና የሀገራችን ሕዝብ እንዲያውቀው መደረጉ ሥርዓቱ ምን ያህል አደገኝ ቁልቁለት ውስጥ ወርዶ እንደነበር አመላካች ነው። ያንን አስከፊ አዘቅት መሻገር በእውነቱ እጅግ ፈታኝ ነበር፤ እግዚአብሔር ይመስገን አልፈነዋል፤ እና በፖለቲካ ሕይወቴ እጅግ የተደሠትሁበት ጊዜ ቢኖር መጋቢት 2010 ዓ.ም ነው ብዬ አምናለሁ፤ ሕልም የሚመስል ጊዜ ነው ያሳለፍነው።

…በመንግሥት ተቋማት ሕዝብን በአግባቡ ከማገልገል ይልቅ ልጅና የእንጀራ ልጅ አድርጎ የመፈረጅ፣ እየተሳሳቡ የመጠቃቀም፣ ከዲሞክራሲ አኳያም ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸም፤ በተለይ አማራና ኦሮሞን ታርጌት አርጎ የማጥቃትና የማሳደድ ሁኔታዎች ረፍት የሚነሱ ነበሩ

ዘመን፦ለአስራሰባትቀናትበዘለቀውየጥልቅተሐድሶወቅትእርስዎንለማሰርየሚፈልጉወገኖችእንደነበሩናድጋፍ  ለማግኘትሲባልምድምጽመሰጠቱይነገራል፤ምክንያቱምንነበር?

አቶገዱ፦ሐሳቡ አልነበረም ማለት አልችልም ሊኖር ይችላል፤ ይህ ታዲያ በጀርባ እንጂ ፊትለፊት የወጣ የእስር ጉዳይ የለም፤ በ2008 ዓ.ም የነበረው የሕዝብ እንቅስቃሴ መሠረቱ የእኛው ድክመት ነው ብዬ አምን ነበር፤ ይህንም ፊትለፊት አነሳ ነበር፤ በሰላማዊ መንገድ የሚያነሳቸው ጥያቄዎቹ በወቅቱና በተቻለ አቅም ሊፈቱለት ካልቻሉ ሕዝቡ መቼም ቢሆን ዝም ሊል እንደማይችል፣ ታግሶ ታግሶ አንድ ቀን ሲነሳ ደግሞ ሊከተል የሚችለው መዘዝ ብዙ እንደሚሆን አምን ነበር።

ከፍትሐዊነት አኳያ፣ በተለይ ከመሠረተ ልማት አኳያ ብዙ እንከኖች ነበሩ፤ ለምሳሌ በመንግሥት ተቋማት ሕዝብን በአግባቡ ከማገልገል ይልቅ ልጅና የእንጀራ ልጅ አድርጎ የመፈረጅ፣ እየተሳሳቡ የመጠቃቀም፣ ከዲሞክራሲ አኳያም ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸም፤ በተለይ አማራና ኦሮሞን ታርጌት አርጎ የማጥቃትና የማሳደድ ሁኔታዎች ረፍት የሚነሱ ነበሩ። እኒያ ሕገወጥ ድርጊቶች እንዲታረሙ በይፋ መነጋገር ጀምረን ስለነበር ያ የማያስደስታቸው ወገኖች ለእስርም ሆነ ለሌላ ጥፋት ቢያስቡኝ የሚደንቅ አይሆንም።

በተለይ ከ97 ዓ. ም ወዲህ የፖለቲካ ምሕዳሩ እየጠበበ የመጣበት ወቅት ነበር፤ የሕዝቡን ጥያቄና ፍላጎት ከማስተናገድ ይልቅ እየተጠቃቀሱ ራስንና መሰልን መጥቀም፣ መሳሳብ፣ ሕግን ገሸሽ አርጎ የሕዝቡን ሐብትና ንብረት እንደ ፈለጉ የመዝረፍና የግልና የተወሰኑ ኃይሎችን ብቻ ጥቅም የማስጠበቅ አደገኛ ድርጊት ውስጥ የተገባበት ሁኔታ እየተስፋፋ ሄዶ ነበር፤ ይህን የሚያየው የሀገራችን ሕዝብ ደግሞ ትግሥቱ እየተሟጠጠ፣ በድርጅታችን ኢሕአዴግ ላይ ፍጹም እምነት እያጣ የሄደበት ሁኔታ ተከስቶ ነበር። እና እኔም ይህን ጠባብ የቡድን ፍላጎት በፍጹም አልቀበለውም ነበር፤ በዚህ የተነሳ በተለይ ከትግራይ ወንድሞቻችን ጋር አለመግባባት ነበር።

የፍትሕ እጦት፤ ሰዎች ያለምንም ምክንያት እየታደኑ መታሠር፣ መደብደብና መሰቃየት፣ የደረሱበት መጥፋት፣ እንዲያም ሲል አካለ ጎደሎ ማድረግ ወዘተ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሱበት ሁኔታ ነበር። ይህን የመሠለ ጉዳይ ሲፈጸም ዝም ብሎ መመልከት ተገቢም ሞራላዊም ስላልነበረ ይህ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲታረም እንታገል ነበር፡

በዚህ የተነሳ በ2007 እና 2008 ዓ. ም በድርጅታችን ውስጥ ከፍተኛ መጠራጠር እየተፈጠረ ስለሄደ የእርስበርስ ግንኙነታችን መሻከር ጀምሮ ነበር የሚል አቋም ነበረኝ። የመሠረተ ልማት ሥርጭቱ ፍትሐዊ አለመሆን፣ የፍትሕ እጦት፤ ሰዎች ያለምንም ምክንያት እየታደኑ መታሠር፣ መደብደብና መሰቃየት፣ የደረሱበት መጥፋት፣ እንዲያም ሲል አካለ ጎደሎ ማድረግ ወዘተ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሱበት ሁኔታ ነበር። ይህን የመሠለ ጉዳይ ሲፈጸም ዝም ብሎ መመልከት ተገቢም ሞራላዊም ስላልነበረ ይህ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲታረም እንታገል ነበር፡፤

ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች በሥርዓትና በዲሞክራሲያዊ አግባ እንዲፈቱ እንታገል ስለነበር ይሕ ያስከፋቸው ወገኖችም መልካም ነገር እንደማያስቡልኝ አውቃለሁ፤ ከሁሉም በላይ አማራ በሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይ በትጋት ከመሥራት አልፎ ከሌላው ወገኑ ተነጥሎ በመጥፎ ነገር እንዲታሰብ የማድረግ አማራን የመጫን ሁኔታ በተግባር አለ ብዬ አምን ስለነበር ይህ ሕገወጥ ድርጊት እንዲቆም፣ ሕዝብ በገዛ አገሩ ላይ እንዳይሳደድ፣ እንዳይገደልና ሐብት ንብረቱ በሕገወጥ መንገድ እንዳይዘረፍ የቻልሁትን ጥረት አድርጌያለሁ፤ ሕብረተሰቡ እየተገፋ ሲሄድ፣ ሕዝቡን የማንበርከክ፣ የማፈንና በጅምላ የማሰር ሁኔታ እየገፋ ሲሄድ ‹‹እየተካሄደ ያለው ስራ ትክክል አይደለም›› ብዬ ታግያለሁ በዚህ አቋሜ የተከፉ ወገኖች ነበሩ፤ ያም ሆኖ እኔን ማጥቃት የተፈለገው ውስጥ ለውስጥ እንጂ በይፋ እንዲሆን አልተፈለገም።

ዘመን፦በጥልቅተሐድሶግምገማችሁወቅትኮ ‹‹የሕወሀትየበላይነትየለም›› ብላችሁወጥታችሁነበር።

አቶገዱ፦በኢህአዴግ አመራር ደረጃ የለም ቢባልም እታች ያለው የኢሕአዴግ አባልና ሕዝቡ ግን በፍጹም ሊቀበሉት አልቻሉም ነበር ‹‹ዋናው ነገር ፍረጃ አለ የለም ሳይሆን በተግባር የሚታየው እርስበርስ መጠራጠር፣ መናናቅ፣ የነበረው ድርጅታዊ ዲሲፕሊን ወደ ጎን ተገፍቶ እንደፈለጉ የመፋነን፣ ቁልፍ የኢኮኖሚ ተቋማትን በቡድን ወርሮ የመጠቃቀም ሁኔታ ዐይን በአወጣ መልኩ እየተካሄደ ነው፤ አድልዎ አለ፤ ጸረ ዲሞክራሲ አሠራር እየተንሠራፋ ነው፤ ምዝበራ አለ፤ በውድድር ሳይሆን ከዚያም ከዚያም እየተጠራሩ (በኔትወርክ) ያለአቅም ሥልጣን ላይ ቁብ ማለት ሁሉ አለ›› እያለ ነበር አባሉና ሕዝቡ። እና አጠቃላይ ሁኔታው ይህን ይመስል ስለነበር ‹‹የሕወሀት የበላይነት የለም›› የሚለውን ሐሳብ የበታች አካሉ ፈጽሞ አልተቀበለውም ነበር።

የአባሉም የሕዝቡም ግፊትና ወኔ እየጎለበተ ሲሄድ ሁሉም ከፍርሀትና ከአድርባይነት ቆፈኑ እየተላቀቀ መሄድ ጀመረ፤ በተለይ የካቲት 2010 የተሻለ መደፋፈር የታየበት፣ በግልጽ የመተቻቸትና የመነቃቀፍ ሁኔተዎች የተስተዋሉበት ወር ስለነበር በታሪካችን የተለየ ቦታ ሊሠጠው የሚችል ነው። በዚህ ምክንያት መጋቢት 2010 ለመጣው ተሥፋ ሰጭ ለውጥ መሠረቱ የተጣለው የካቲት ላይ ነው ብዬ አምናለሁ።

ዘመን፦በኢሕአዴግደረጃየነበረውአመራርምንንመሠረትአድርጎነው ‹‹የሕወሀትየበላይነትየለም›› ያለውበከፍተኛአመራሩናበአባሉመሀልእንዲህያለሰፊልዩነትየተፈጠረውስለምንይመስልዎታል?

አቶገዱ፦እንደ ነገርሁህ ከየካቲት 2010 ዓ. ም. በፊት መፈራራት፣ መሸፋፈን ነበር፤ ይህ ታዲያ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው አድርባይነት እንጂ ምንም ሊሆን አይችልም። አድር ባይነትኮ ሌላው ሥር የሰደደ ችግራችን ነበር።

ዘመን፦ዶክተርዐቢይንጠቅላይሚኒስትርአድርጎለመምረጥየብአዴንአዴፓድርሻከፍተኛእንደነበርበማኅበራዊሚዲያውበሰፊውሲወራነበር፤እውነትነውእስኪሂደቱንወደኋላመለስብለውያስታውሱን?

አቶገዱ፦እንደሚታወቀው በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት ነበር፤ በተለይ አቶ ለማና ዶክተር ዐቢይ ወደሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለመላ አገሪቱ ሊጠቅም የሚችል ለውጥ ማምጣት የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነበር። በአማራ ክልልም ተመሳሳይ መናበብ ስለነበር መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር ማለት ይቻላል። የሕዝቡ ጠንካራ ፍላጎት በአግባቡ ካልተስተናገደ ሀገሪቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ልትወድቅ እንደምትችል ይፋ የወጣበት፣ ሕዝቡ ትግስቱ አልቆ አደባባይ የወጣበትና ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ፊትለፊት መጋፈጥ የጀመረበት ወቅት ነበር፤ ለዚህ ፈጥጦ ለወጣ ችግር ተገቢውን መልስ አለመስጠት ውሎ አድሮ ምን ሊያስከትል እንደሚችል በግልጽ የወጣበት ነበር።

Image result for oromara

የእነ አቶ ለማ መምጣት የህዝቡን የለውጥ ጥያቄ ለመመለስ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ እውነት ነው፤ በዚህ መሠረት ከኦሕዴድ ጓዶች ጋር ጥሩ መደማመጥ ስለነበር ያመንንበትን ሠርተን ዶክተር ዐቢይ ወደሊቀመንበርነት እንዲመጡ ተደርጓል፤ ይህ ሲባል ሌሎች እህት ድርጅቶችና ጓዶች ምንም ድርሻ አልነበራቸውም ማለት አይደለም። ሁሉም የየበኩሉን ገንቢ ድርሻ ተወጥቷል። ትልቁ ነገር ምንድን ነው? ቀደም ብዬ እንደጠቀስሁት ከየካቲት 2010 ዓ. ም. ጀምሮ የነበረው መፈራራት፣ መሸፋፈን ጥላ ተገፍፎ ሁሉም የመሰለውን፣ የሚያምንበትን ጉዳይ በይፋ መናገር፣ አቋሙንም ያለምንም ማቅማማት የማራማድ ሁኔታ ተከስቶ ነበር፤ የዚያ ያዚያ ድምር ውጤት ምርጫውን የተሳካ አድርጎታል ብዬ አምናለሁ።

ዘመን፦የህወሀትየገዥነትዘመንያበቃው ‹‹እሳትናጭድናቸው›› ሲባሉየነበሩትአማራናኦሮሞጥቅምት 25/2010 .ባህርዳርላይያካሄዱትንጉባኤተከትሎነውየሚሉወገኖችአሉ፤እውነትነው?

aaaa.jpg

አቶገዱ፦ይኸ እውነት ነው፤ በቆየንባቸው 27 ዓመታት ሁለቱ ታላላቅ ሕዝቦች በጥርጣሬ እንዲተያዩ፣ እርስበርስ እንዲፈራሩና በባላንጣነት እንዲሰለፉ ሠፊና ተከታታይ ሥራ ሲሠራ ነበር፤ የሚያገናኟቸው ታላላቅ ጉዳዮች ወደ ጎን እየተገፈተሩ በሚያለያዩአቸው ጥቃቅን ነጥቦች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በትጋት እየተሠራ ነበር። ያ ለ27 ዓመታት በትጋት የተሠራበት የማባላት ሥራ ‹‹ፍሬ አፍርቷል፤ አማራና ኦሮሞ ዳግም ላይገናኙ ተለያይተዋል›› ብለው ያምኑ ስለነበር ነው ‹‹እሳትና ጭድ ናቸው›› ብለው በድፍረት መናገር የቻሉት።

ትልቅ ስህተት የፈጸሙትም እንዲህ አይነት እምነት በውስጣቸው ሲያሳድሩ ነው፤ ምክንያቱም አማራና ኦሮሞ ማንም ቢወድም ቢጠላም ሊለያዩ የሚችሉ አይነት ሕዝቦች አይደሉም፤ ማንም ኃይል ሊበጥሰው በማይችለው የዘመናት ቆይታ ባካበቱት ጽኑዕ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ድር የተጋመዱ ናቸው፤ ይህን እውነት ስለማይረዱ ለ27 ዓመታት ሙሉ ከንቱ የደከሙ ወገኖች ነበሩ፤ በሁለቱ ሕዝቦች መሀል ያለውንና የነበረውን እውነት በውል ሳይረዱ ለ27 ዓመታት የዘሩት መጥፎ ፕሮፓጋንዳ ፍሬ የያዘላቸው መስሏቸው ነው እንዲያ በድፍረት መናገር የቻሉት።

በመሠረቱ ይህ ንቀት ነው፤ ሁለቱን ሕዝቦች ዝቅ አድርጎ የማየት በሽተኛ አስተሳሰብ። የራስን የበደል እድሜ ለማራዘም በሁለቱ ሕዝቦች መነገድ የማያዋጣ መሆኑን፣ አለማዋጣት ብቻ ሳይሆን ከባድ ኪሳራ መሆኑን የተረዱበት አጋጣሚ የተፈጠረው ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ. ም. ባሕርዳር ላይ የተካሄደውን ጉባኤ ተከትሎ በተሠሩ ሥራዎች በመጣ ውጤት ነው ብዬ አምናለሁ። እና የሁለቱ ሕዝቦች ጤናማ ግንኙነት ሴራ ሲጎነጉኑበት የነበሩ ኃይሎችን የተንኮል ድር በጣጥሶ በመላ አገሪቱ የምናየውን ለውጥ አምጥቷል።

ዘመን፦ሕወሀትእርስዎንከኃላፊነትለማስነሳትብዙጊዜሞክሮአልተሳካለትምይባላል፤እውነትነው?

አቶገዱ፦ልክ ነው፤ ብዙ ሙከራ ነበረ፤ ውሳኔዎችን በጋራ እንደምናስተላልፍ ቢታወቅም የሚነሱ የፍትሐዊነትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ ሰበብ መፈለግና የመጣውን ሕዝባዊ ጫና ወደ ግለሰቦች የመግፋት ሁኔታዎች ነበሩ፤ በይፋም በሥውርም እኔን የሚቃወሙት ‹‹በአማራ ሕዝብ ውስጥ የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ አመጽ የሚመራው እሱ ነው›› ከሚል የተዛባ አስተሳሰብ ተነስተው ነው፤ ጥያቄዎቹ በአግባቡ ካልተመለሱ፣ ፍትሐዊ አሠራር ከጠፋ፣ አንዱ ልጅ፣ ሌላው የእንጀራ ልጅ ከሆነ ሕዝቡን ምንም ኃይል ሊያስቆመው እንደማይችል መገንዘብ አቅቷቸው ነው ችግሩን ሁሉ እየሰበሰቡ ለግለሰቦች ያሸክሙ የነበረው። እና ድርጊቱ በድርጅት ደረጃ የተካሄደ ነው ማለት ባያስደፍርም አልተሳካም እንጂ ብዙ ሙከራ እንደ ነበር ግልጽ ነው።

ዘመን፦በህወሀትናየቀድሞውብአዴንመሀልየሰፋልዩነትእየታየየሄደውየወልቃይትንናየራያንሕዝቦችመብትለማስከበርበሚደረግ ግብግብመሆኑይነገራል፤ምንያህልእውነትነትአለው?

አቶገዱ፦ልክ ነው፤ አንዱ ምክንያት እሱ ሊሆን ይችላል። ቀደም ሲል ጀምሮ በሕብረተሰቡ ውስጥ የማንነት ጥያቄዎች ነበሩ፤ ግን ጥያቄዎቹ እንደጊዜው ሁኔታ ሞቅና ቀዝቀዝ ሲሉ ቆይተዋል እንጂ መቼም ቢሆን ጥያቄዎቹ ያልተነሱበት ጊዜ የለም። ነገር ግን ‹‹ጥያቄዎች ትክክል አይደሉም›› ብሎ የሚያምን አመራር ነበር፤ ነገሩ እየተካረረ ሲሄድ ጥያቄዎቹ ይበልጥ እየገፉ መጡ።

ለጥያቄዎቹ ሕግን መሠረት ያደረገ መልስ ከመስጠት ይልቅ የኃይል እርምጃ ወደመውሰድ ሲገባ በተለይ ከ2006/2007 ዓ. ም. ጀምሮ በውስጣችን የነበረው ጤናማ ግንኙነት እየሻከረ መሄድ ጀመረ፤ አሁንም ተስፋ አልቆረጥንም ነበርና ‹‹ጥያቄውን በኃይል ማፈን አይቻልም፤ ሕግን መሠረት ያደረገ መፍትሔ እንዲሰጠው ምቹ ሁኔታ ይፈጠር›› የሚል ጥያቄ አነሳን፤ ይህ ጥያቄያችን ግንኙነታችንን ይበልጥ እያሻከረው ሄደ፤ በዚህ ምክንያት ጥያቄው በክልልም በአገር አቀፍ ደረጃም እያደገ መጣ ማለት ነው። በመሆኑም እንደተባው በእህት ድርጅቶች መሀል ይፋ የወጣ መጠራጠርና የጎሪጥ መተያየት የተከሰተው የወልቃይትና የራያ ሕዝብ ጥያቄዎችን በሕግ ከመፍታትና ካለመፍታት ጋር በሌላም በኩል ‹‹የራያም ሆነ የወልቃይት ጉዳይ ያለቀ የደቀቀ ጉዳይ ስለሆነ ዳግም መነሳት የለበትም›› ከሚለው ወገን ጋር የተከሰተ አለመግባባት ነበር።

‹‹አማራ ሊወርህ ነው፤ ተነስ! ታጠቅ›› እያሉ ሕዝቡን እየቀሰቀሱ እንደ ሆነ የትግራይን ሕዝብ ወንድሙ በሆነው የአማራ ሕዝብ ላይ ለማዝመት እየተዘጋጁ እንደ ሆነ አውቃለሁ

ይህንን እንደ አንድ ምክንያት ልንወስደው ብንችልም ከመሠረተ ልማት፣ ከፍትሕ እና መልካም አስተዳደር፣ ከሰው ኃይል ምደባ፣ ወዘተ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ሌሎች ጉዳዮችም በእህት ድርጅቶች መሀል መጠራጠርን የፈጠሩበት ሁኔታ ነበር።

ዘመን፦ ‹‹ሕወሀትበአማራክልልሕዝብላይሠራዊትለማዝመት 1.2 ሚሊዮንታጣቂዎችንአሠልጥኗል›› ሲሉታዋቂውፖለቲከኛአቶአንዳርጋቸውጽጌሰሞኑንሲናገሩተደምጠዋል፤መረጃውንእንዴትያዩታል?

አቶገዱ፦‹‹አማራ ሊወርህ ነው፤ ተነስ! ታጠቅ›› እያሉ ሕዝቡን እየቀሰቀሱ እንደ ሆነ የትግራይን ሕዝብ ወንድሙ በሆነው የአማራ ሕዝብ ላይ ለማዝመት እየተዘጋጁ እንደ ሆነ አውቃለሁ፤ ክልሉ ቀርቶ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሊሸከመው የማይችል ኃይል እያሰለጠኑ መሆኑ የአደባባይ እውነት ነው፤ ስለዚህ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አባባል ትክክል ለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ይኸ ለምን እንደሚደረግም ግልጽ ነው። በሕገወጥ መንገድ ሕዝብን የዘረፉ፣ ዘርፈውም አንድ አካባቢ የከተሙ ወገኖች አሉ፤ የዘረፉትን የሕዝብ ሀብትና ንብረት መብላት የሚችሉት ግርግር ሲኖር ብቻ ነው ብለው ያመኑ ይመስለኛል። ስለዚህ ያን በዘረፋ የተገኘ ሀብት ለመብላት ‹‹ሌላ አማራጭ የለንም›› ብለው ደምድመዋል።

ለገመናቸው ምሽግ ይሆን ዘንድ እንደ ብቸኛ ምርጫ የወሰዱት ሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች ማባላትና ሁለቱ ሲፋለሙ በመሀል የግል ሕይወታቸውን መግፋት ነው፤የእነሱ ሕይወት እንከን አያግኘው እንጂ ድሃው ቢያልቅ፣ ወንድም ከወንድሙ ቢተላለቅ ለእነሱ ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፤ ለዚያ ነው የጦርነት ነጋሪት ሌት ከቀን በመጎሰም ላይ ያሉት። ነገር ግን የትግራይ ሕዝብ ከማንም በላይ የጦርነትን አስከፊነት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ከአማራ ወንድሙ ጋር ይዋጋል የሚል እምነት የለኝም።

ዘመን፦የአማራክልልምክርቤትበቅርቡባካሄደውስብሰባው‹‹በሕወሀትበኩልየተንኳሽነትአዝማሚያዎችእየታዩስለሆነከዚህድርጊቱ ይቆጠብ›› የሚያሳስብጠንከርያለመግለጫአውጥቷል፤ይህንለማለትየሚያበቃተጨባጭማስረጃአለብለውያምናሉ?

አቶገዱ፦በጉዳዩ ላይ የክልላችን ምክር ቤት በዝግ ተወያይቶበታል፤ የውስጥ ሰላማችንንና አንድነታችንን ከሚፈታተኑ አደገኛ አዝማሚያዎች እንዴት መጠበቅ እንዳለብንም አይተናል። የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የክልሉ ኢኮኖሚም ሆነ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታው መሸከም ከሚችለው በላይ ሠራዊት እያሠለጠነና እያስታጠቀ መሆኑን በበቂ ማስረጃና መረጃ አረጋግጠናል፤ በመሆኑም ይህ ለማንም የማይጠቅም የጦርነት አስተሳሰብ እንዲቆም፣ ይልቁንም እንደ አንድ የቤተሰብ አባል በፍቅር የኖሩ ሕዝቦችን እንነጥላቸው ብንል እንኳ በምንም መንገድ ሊነጠሉ የማይችሉ፤ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖትና በሥነልቡና የተጋመዱ በመሆናቸው ሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች ወደጦርነት መግፋት ተገቢ አለመሆኑን ብቻ ሳይሆን ወንጀል መሆኑን አይተናል።

በመሠረቱ የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች በጦርነት የሚፈላለጉበት ምንም ምክንያት የለም፤ ረጅሙን የሀገራችንን ታሪክ ብናይ ባላባት ከባላባት ወይም አንዱ መሥፍን ከአቻው ጋር የያደርገው የ‹‹ገብር፤ አልገብርም›› አይነት መቃቃር ካልሆነ በየትኛውም አካባቢ ቢሆን ሕዝብ በሕዝብ ላይ የዘመተበት፣ ሕዝብ የሕዝብ ጠላት የሆነበት አጋጣሚ በፍጹም አልነበረም፤ የለምም። ዛሬ ከመሬት ተነስተን ሕዝቡን ለጦርነት የምናሰልፍበት ምንም ምክንያት የለም ብለን እናምናለን። ጦርነት በምንም መለኪያ የሚፈለግ ጤናማ ምርጫ አይደለም፤ ችግሮቻችን ሁሉ ፖለቲካዊ በመሆናቸው ፖለቲካዊ መፍትሔ ብቻ ነው የሚያስፈልጋቸው ብዬ አምናለሁ።

እናም ‹‹አማራ ሊወጋህ ነው፤ ሊወርህ ነው›› የሚለው ተገቢ ያልሆነ ቅስቀሳ እንዲቆም ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ የሚከቱ የሐሰት ቅስቀሳዎችና ዘመቻዎች መልክ እንዲይዙ ነው ምክር ቤቱ ያሳሰበው። አማራና ትግራይን ለጦርነት የሚጋብዝ ምንም መሠረታዊ ምክንያት የለም ነው መልእክቱ፤ የማንግባባቸውን አንዳንድ ጉዳዮች ቁጭ ብለን መፍታት እንጂ እዚያና እዚህ ሆኖ ‹‹ይዋጣልን›› ማለት ለማንም አይበጅም ነው ያልነው።

ዘመን፦የትግራይናየአማራሕዝብለጦርነትይፈላለጋልብለውያምናሉ?

አቶገዱ፦በፍጹም አላምንም፤ የአማራና ትግራይን ሕዝቦችኮ ዛሬ የፈጠርናቸው፣ ስንፈልግ የምናዋጋቸው፣ ሲያሻን ደግሞ እንደ ጨርቅ በልካችን የምንሰፋቸው አይደሉም። ደርግን ለመጣል በተደረገው መራራ ትግልም ሆነ ከዚያ በፊት አገራችንን ለመውረር የመጡ አገር ደፋሪዎችን በጋራ ሲመክቱ የኖሩ፣ አንዱ ሲሞት ሌላው እየተተካ አገሩን በአጥንቱ አጥር ጠብቆ ያቆየና ታሪካዊ መሠረት ያላቸው በጠንካራ ቤተሰባዊ ሐብል የተሣሰሩ ወንድማማች ሕዝቦች ናቸው።

ሆኖም እብዶች አይጠፉምና ‹‹እስከ ዘላለሙ ግጭት ሊፈጠር አይችልም›› ብሎ መደምደም አይቻልም። ‹‹ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል›› እንዲሉ በአማራ ላይ የሚካሄደው ‹‹ሊወርህ ነው›› አደገኛ ቅስቀሳ ሕዝቡን የማያደናግርበት ምንም ምክንያት ላይኖር ይችላል፤ እናም በውሸት ላይ ተመሥርቶ ነጋ ጠባ በሚካሄደው አፍራሽ ቅስቀሳ ምክንያት ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ወደ አልታሰበ አቅጣጫ ቸኩለው እንዳይገቡ ነው የእኛ መግለጫ ምክንያት።

ዘመን፦እርስዎናዶክተርደብረጽዮንገብረሚካኤልበሃይማኖትአባቶችአማካይነትመስማማታችሁበመገናኛብዙኃንሲታይነበር፤ስምምነቱከምንደረሰናነውየጦርነትቅስቀሳየተጀመረው?

አቶገዱ፦ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች እንዲቃቃሩ የሚደረገው አፍራሽ ቅስቀሳ አሳስቧቸው የሃይማኖት አባቶች ሁለታችንን ለማስማማት አስበው፣የሀገራችን ጉዳይ ዕረፍት ነስቷቸው ለማስታረቅ ያደረጉትን ጥረት አሁንም እናከብራለን፡ በዕለቱ ‹‹በእኛ በኩል የመጀመሪያዋን ጥይት ለመተኮስ ቀዳሚ አንሆንም›› ብዬ እንደ ተናገርሁት አሁንም ያንን ቃል እንጠብቃለን፤ ሆኖም ሲተነኩሱን፣ ሲገድሉን ዝም ብለን እናያለን ማለት አይደለም።

ሁለታችን (ዶክተር ደብረጽዮን እና አቶ ገዱ መሆናቸው ነው) ፊትለፊት ተገናኝተን ከተነጋገርን በኋላም የጦርነት ቅስቀሳው፣ ወታደራዊ ሥልጠናውና ማስታጠቁ ሊቆም አልቻለም፤ እርቅ የሚባለው ደግሞ በሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች እኩል ሲጠበቅ እንጂ አንደኛው በያዘው የተሳሳተ መንገድ ቀጥሎ ሌላኛው በየዋህነት ቁጭ ብሎ የሚመጣውን ሲጠብቅ አይደለም። በዚህ ምክንያት ነው ግራ ቀኙ ቅስቀሳው እየተካሄደ ያለው።

ሆኖም ሕዝቡ እውነታውን ሲረዳው፣ አማራ የትግራይ ወንድሙን የመውረርም ሆነ የመጉዳት ዓላማ እንደሌለው ሲገነዘብ አሁን የሚታየው ግርግርና አፍራሽ ቅስቀሳ ሁሉ ይሰክናል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ሕዝብ በሰላም ሥራውን እንዲሠራ፣ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ የጋራ ጠላቱ የሆነውን ድህነትን በተባበረ ክንዱ እንዲዋጋ መቀስቀስ እንጂ በገዛ ወገኑ ላይ እንዲሰለፍ ሌት ከቀን መሥራት ከጤነኛ አእምሮ የሚፈልቅ አስተሳሰብ አይደለም። ሁለቱን ሕዝቦች ልናዋጋቸው ይቅርና እንዲጠራጠሩ ማድረግም የለብንም ብዬ አምናለሁ።

ዘመን፦ሥልጣኑንከሕወሀትእጅፈልቅቀውያወጡትየዚያንጊዜዎቹብአዴንናኦህዴድነበሩ፤በአሁኑወቅትግንሆድናጀርባሆነዋልእየተባለነው፤እውነትይሆን?

አቶገዱ፦በዚህ ሐሳብ አልስማማም፡ የማይካደው ነገር ምንድን ነው? በሀገራችን የጽንፈኝነት ፖለቲካ አለ፤ ስሜት ቀስቃሽ ሐሳቦችን እያነሱ አማራና ኦሮሞን ለማዋጋት የሚደረጉ አጉል አዝማሚያዎች አሉ፤ እና እነሱ የሚፈጥሩት ውዥንብር አለ፤ ‹‹ሆድና ጀርባ ሆነዋል›› የሚለው የተሳሳተ ሐሳብ መነሻውም ይኸው ነው እንጂ ሁለቱ ፓርቲዎች እንዲህ በቀላሉ ሆድና ጀርባ ሊሆኑ የሚችሉበት ምንም ምክንያት የለም፤ ሁለቱ ሕዝቦች ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ. ም ባሕርዳር ላይ ሲገናኙ ያስተማሩን 

 ነገር አለ፤ ያንን አደራ ረስተን ዛሬ ልንለያይ አንችልም፤ የጀመርነው አገራዊ ጉዳይ የልጆች ጨዋታ አይደለም። ይልቁንም ሊከፋፍሉን፣ ሊነጣጥሉን፣ ከዚያም ሊያዋጉን ሌት ከቀን የሚሠሩ ጽንፈኛ ኃይሎችን ነው በጋራ መዋጋት ያለብን፤ እነሱን በንቃት መመከት ያስፈልጋል።

ዘመን፦‹‹ለውጡተቀልብሷል፤ህወሃትስልጣኑንምኢኮኖሚውንምብቻውንአግበስብሶይዟል› እየተባለሲተችነበር፤ኦዴፓምስሙተቀየረእንጂየታየለውጥየለም፤እንዲያውምአማራንእየገፋሥልጣኑንለብቻውእየጠቀለለነው›› የሚባለውንአስተያየትስእንዴትይመለከቱታል?

አቶገዱ፦እዚያም እዚህም የሚታየውን አለመረጋጋት መነሻ በማድረግ ‹‹ለውጡ ተቀልብሷል፤ አዴፓም በኦዴፓ ተክዷል›› እያሉ በመረጃ መረቦች ወከባ የሚፈጥሩ ሰዎች አሉ፤ አንዳንዶች ፖለቲካዊ እውነታውን (ጉዳዩን) ሳይረዱት በስሜት ተገፋፍተው፣ ሌሎች ደግሞ አማራና ኦሮሞን የማባላት ተልኮ ተሰጥቷቸው፣ ለዚህም ትልቅ በጀት ተመድቦላቸው በአማራና ኦሮሞ ስሞች ሁለቱን ታላላቅ ሕዝቦች ለማፋጀት ሌት ከቀን የስድብ አይነት ሲያዥጎደጉዱ የሚውሉ የሚያድሩ አሉ፤ እሱን በአግባቡ ሳይረዱ በስሜታዊነት የሚበሳጩና ውዝግብ ውስጥ የሚገቡ፣ ሁኔታውን ለማርገብ የሚሠሩ፣ የሀገራችን አንድነትና ሰላም አሳስቧቸው ምክር የሚለግሱ፣ ወዘተ ብዙ አይነት ወገኖች አሉ።

በማኅበራዊ ሚዲያው የሚዘንበውን የተሳሳተ መልእክት ያየ ሁሉ ‹‹ኦዴፓ እና አዴፓ ተለያይተዋል፤ ምደባውን ሁሉ ኦዴፓ ጠቅልሎ ይዞታል›› ሊል ይችላል፤ ነገር ግን እስከማውቀው ድረስ ያለአንዳች ምክክር ምደባ አይከናወንም፤ አመራር የሚመደበው በጋራ ምክክር ነው ማለት ነው። የዚህ ምክንያቱ ምንድነው መሰለህ ፖለቲካችን ችግር ስላለበት ነው። እንጂ በከፍተኛ አመራር ላይ የሚመደቡት ሰዎች በጋራ በሚደረግ ምክክር ነው።

ሆኖም ምደባው ወይም አመራር ምደባ ላይ ምንም እንከን የለም ልልህ አልችልም፤ ለነገሩ ምደባ መሆን ያለበት በውድድር (በሜሪት) ነው፤ ምክንያቱም ሀገራችን ውስጥ ያሉት አማራና ኦሮሞ ብቻ አይደሉም በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች አሉ፤ ለሁሉም ሥልጣን ይታደል ቢባል የሚቻል አይደለም። ለምሳሌ ሃያ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አሉ፤ በሃያዎቹ ቦታዎች ላይ ሊመደብ የሚችለው የሰው ኃይል ሃያ ብቻ ነው፤ በኮታ ከሆነ የምንወጣው አይመስለኝም፤ ግን አንድ እውነት ደግሞ አለ፤ በማንኛውም መንግሥታዊ ኃላፊነት ላይ የሚመደብ ሰው በብሄራዊ ማንነቱ ሳይሆን በብቃቱ፣ ባለው ህዝባዊ ፍቅሩ፣ በትምህርት ዝግጅቱና ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል ባለው ቁርጠኝነት መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ።

ሕዝብን በቅንነት የማያገለግል ከሆነ፣ ዘር እየቆጠረ አድልዎ የሚፈጽም ከሆነ ማንም ቢሆን መመደብ የለበትም። አሁን ፖለቲካችን የሰከረ፣ ያልሰከነ ስለሆነ ነው በሆነ ባልሆነው ነገር እየተመዘዘ ሕዝብን ለማበጣበጥ እየተሮጠ ያለው።

ለውጡ ብዙ ተግዳሮቶች አሉበት፤ ስለሆነም ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፤ በተለያዩ ኃይሎች ዘንድ ስለለውጡ ያለው አመለካከት ችግር ያለበት ነው፤ ለውጡ እንዳይሳካ፣ በሀገራችን ሰላም እንዳይሰፍን፣ ዲሞክራሲ እንዳያብብ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዳይኖር ብዙ የሚጥሩ አሉ፤ ቆም ብሎ ማሰብና የሚገጥሙንን ፈተናዎች ሁሉ በጥበብና በማስተዋል እየፈቱ መሄድ ያስፈልጋል፤ ከሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ የመን፣ ሊቢያና ኮሶቮ መማር አለብን፤ ከመናናቅ፣ ከመናቆርና እርስበርስ ከመወነጃጀል አንዳች ትርፍ አይገኝም፤ ይልቁንም ባለብዙ ፀጋ የሆነችውን አገራችንን በጥንቃቄና በፍቅር ልንይዛት፣ ልናለማትና በጋራ ልንጠቀምባት ይገባል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከአሁን የተሻለ ጊዜ ይኖራል ብዬ አላስብም፡

ዘመን፦በአሁኑወቅትለሀገራችንምሆነለክልሉፈታኝየሚሉትጉዳይምንድንነው?

አቶገዱ፦ፖለቲካችን ስሜታዊነት የሚበዛበት ነው፤ጽንፈኛ ፖለቲካ በብዙ ገጽታ እየታየ ነው፤ እነዚህን ሁኔታዎች መልክ ማስያዝ ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ ግን በሰብአዊነት፣ ሰዎች በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ መፍጠር ለሕዝቦች አብሮነት የሚጨነቅ ፖለቲካ መምጣት አለበት ነው የምንለው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ የሚያጋጥሙ ችግሮች አሉ፤ የመፈናቀል ሁኔታ አለ፤ ህብረተሰቡ ስጋት ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ በሰፊው ይታያል።

ፖለቲካችን ላይ ዋነኛ ችግር አድርጌ የማየው አለ፤ እሱም ጫፍና ጫፍ የሚረግጡ ኃይሎች አዝማሚያ ቀላል ቦታ የሚሰጠው አለመሆኑ ነው፤ ይኸ ህብረተሰቡን ስጋት ውስጥ እያስገባው ነው። ሁለተኛው ችግር ሀገራችን በፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደነበረች ለማንም ግልጽ ነው፤ ነገር ግን ይኸ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያልፈታቸው ችግሮች አሉ። አሁንም

 ሥራ አጥነት አንገብጋቢ የህብረተሰቡ አጀንዳ ነው። የኑሮ ውድነት ወይም በጥቅል ድህነት ብለን ልንወስደው እንችላለን፤ ይህም ስር የሰደደ ችግር ነው።

ከሁሉም በላይ የከፋ የሚሆነው ደግሞ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ መስክ ያሉትን ችግሮች መፍታት የሚችሉ ብቃት ያላቸው ተቋማት የሉም። የተለያዩ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ሕዝብን ማርካት በሚቻልበት አግባብ መምራት መሸከም የሚችሉ ተቋማት የሌሉ መሆናቸው እንደ ሦስተኛ ችግር/ምክንያት ሊወሰድ ይችላል። እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ተቋም ካለ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መፍታት ይቻላል፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የጸጋ፣ የተፈጥሮ ሀብት/ ችግር ያለባት ሀገር አይደለችም። ከፍተኛ ወጣት ኃይል ያለባት ሀገር ነች። ነገር ግን ይኸን ኃይል አስተባብሮ በፀረ ድህነት ትግሉ ማሰለፍ የሚያስችሉ ተቋማት መኖር አለባቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ገና በሚገባው ደረጃ እንዳልመጣ፣ ፖለቲካችን በእጅጉ ኋላቀርነት የሚጠናወተው ነው። ወደተስተካከለ ሁኔታ የሚወስዱ የዲሞክራሲ ተቋማት ያስፈልጋሉ፤ እነዚህ መገንባት አለባቸው ማለት ነው።

የለውጥ እንቅስቃሴው በብዙ መልኩ እየተፈተነ ይሄዳል፤ ነገር ግን አማራጭ የለም። ለውጡን ዳር ለማድረስ የሚጎድሉንን እየሞላን የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በትግል እያስተካከልን መራመድ አለብን። በተለይ ደግሞ ነጻነት አጥቶ ታፍኖ የኖረ ሕዝብ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የኋላ ኋላ መፈንዳቱ አይቀርም፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሀገሪቱን አደጋ ላይ ይጥላል። ስለዚህ ዲሞክራሲን ማስፈን በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዜጎችን የትም ቦታ በሰላም የመኖር መብት የማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ተደጋግፈው ተወራርሰው መሄድ መቻል አለባቸው። እነዚህ ጉዳዮች ዘለቄታ የሚኖራቸው የኢኮኖሚ ልማቱ (ጸረ ድህነት ትግሉ) ተጠናክሮ ሲሄድ ነው። ስለዚህ እነዚህን አቀናጅቶ የማስኬድ ጉዳይ የወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካ ወሳኝ አጀንዳ ነው ማለት ይቻላል።

ዘመን፦ ‹‹ሳልሰራውየቀረሁት›› ብለውየሚቆጩበትነገርየለም?

Image result for lema megersa in amhara region

አቶገዱ፦በጣም ብዙ፤ አንድ ነገር ልንገርህ፤ እኔ ወደ ኢህአዴግ ስቀላቀል ምክንያቴ የነበረው በዋናነት ዲሞክራሲ …አልነበረም፤ በዋናነት አብሬ እንድሰለፍ ያደረገኝ የኢህአዴግ የፀረ ድህነት አቋም ነው። የታገልኩት ድህነትን ለማስወገድ ነው። ልክ ነው ብዙ ነገሮች ተሠርተዋል፤ የሀገራችንን ገጽታ የሚቀይሩ ነገሮች ተሠርተዋል፤ ድህነት እና ጉስቁልና ስር የሰደደ የህዝባችን ችግር ነው። እኔ በምመራው ክልል ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ነበር። ይህ ሁኔታ ተለውጧል። የተሠሩ የሚያኮሩ ስራዎች አሉ፤ አሁንም ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ድህንት ውስጥ ነው። ላለፉት አስር ዓመታት ያህል በክልሉ ቁልፍ ኃላፊነት ይዤ ሰርቻለሁ። ድህነትን ለመቀነስ ብዙ ለፍተናል፤ ብዙ ውጤትም አምጥተናል። አሁንም ግን አምስት ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ በድህነት ውስጥ ነው ያለው። ስለዚህ መጀመሪያ ኢህአዴግን ለመቀላቀል ምክንያት የሆነኝ ጸረ ድህነት ትግሉ ነው ካልኩት አኳያ ስመዝነው የሄድንበት ርቀት ብዙ የሚቀረው አድርጌ እወስደዋለሁ፤ አሁንም በቁጭት የምመለከተው ነው።

ዘመን፦ብዙዎችከክልልፕሬዚዳንትነቱሲለቁአምባሳደርሊሆኑነው፤ውጪጉዳይሚኒስትርሊሆኑነው፤አማካሪሊሆኑነው፤ወዘተእያሉየተለያየግምታቸውንእየገለጹነው፤የእርስዎምርጫምንድነው?

አቶገዱ፦መንግሥት ሰዎችን ለአንድ ኃላፊነት ሲመድብ ከተለያዩ ነገሮች አንጻር መዝኖ ነው፤ ይኸ ይሁን ብሎ ግፊት መፍጠር ተገቢነት አለው ብዬ አላምንም፤ ለሀገርም አይጠቅምም። እኔ ግን ምረጥ ብባል የምመርጠው ለተወሰነ ጊዜ ቀለል ባለ ቦታ ብቆይ ነው። አሁን በፖለቲካ መስኩ ሀገራችን ብዙ ታጋዮችን የምትፈልግበት ጊዜ ነው፤ ስለዚህ ከፖለቲካ መስኩ ወደ ኋላ አልልም። ነገር ግን የተወሰነ ጊዜ አርፌ ራሴን ማዘጋጀት እፈልጋለሁ። ስለዚህ ቀለል ያለ ቦታ ላይ ብመደብ እመርጣለሁ። ግን እዚህ ልመደብ ብዬ ምክረ ሀሳብ አላቀርብም፤ መንግሥት ‹‹እዚህ ቦታ ቢመደብ ውጤት ያመጣል›› የሚለውን ቦታ ይመዝናል። ስለዚህ በየትኛውም ቦታ ብመደብ ችግር የለብኝም። አስተዋጽኦ ለማበርክት እስከፈለግህ ድረስ፣ ማእከልህ ሀገር፣ ሕዝብ፣ የህብረተስብ የለውጥ አንቅስቃሴን ማገዝ እስከሆነ ድረስ የትም ሆነህ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላለህ። ስለዚህ ፍላጎቴ በአገር ውስጥ በየትኛውም ቦታ በማንኛውም ደረጃ ቢሆን ችግር የለብኝም።

ዘመን፦ ‹‹መነሳትነበረበት›› የሚሉትጉዳይይኖራል?

አቶገዱ፦በአገራችን በተጀመረው ለውጥ ህብረተሰቡ የተጎናጸፋቸው ውጤቶች አሉ፤ አንዱ ነጻነት ነው። አሁን ህብረተሰቡ የፈለገውን መናገር ይችላል፤ የሚጽፉ ሚዲያዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ የተሰደዱ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፤ በፖለቲካ አመለካከት ምክንያት የታሠሩ እንዲፈቱ ተደርጓል። በጠቅላላ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉበት መልካም ሁኔታ ተፈጥሯል። ይኸንን በአግባቡ የመጠቀም ጉዳይ የሚመለከታቸው አካለት ጉዳይ ነው፤ እንደ አገር የፖለቲካ ምህዳሩ የተመቻቸ ሆኗል።

በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች አሉ። ሥር ሰዶ የቆየው የጥላቻ ፖለቲካ አለ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩ የሚያደርጉ ሰፊ እንቅስቃሴዎች አሉ። ይህን ተግዳሮት ተቋቁሞ ሕዝብ ወደሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ብልጽግና፣ እንዲሸጋገር ማድረግ ያስፈልጋል። ይኸንን ለማሰናከል ሁሉም ወደየብሔሩ የመጎተት ችግር አለ። ይኸ የጥፋት መንገድ ነው የትም ሊያደርስ አይችልም። የጀመርነው የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይጨናግፍ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ቢያንስ በሚያግባቡ ጉዳዮች በአንድ ላይ መቆም አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። የሰላም፣ የዜጎችን ደኅንነት የማረጋገጥ፣ ሰብአዊ መብታቸውን የማስከበር ጉዳይ፣ የሕግ የበላይነትን የማስከበር አጀንዳዎች ቢያንስ ፓርቲዎች በነጻነት ለመንቀሳቀስ የሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው፤ ስለዚህ በእነዚህ ላይ በጋራ መሰለፍ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ።

ዘመን መጸሄት ሚያዚያ 2011

ዘመን መጸሄት ሚያዚያ 2011

በዝግጅት ክፍሉ