ሐራ ዘተዋሕዶ

May 25, 2019

his-grace-abune-elsa

*** ከየዋሃትና ከደግነት ጋራ በተሟላ የአገልግሎት ሕይወታቸው የታወቁት፣ አንጋፋው የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ዐረፉ፡፡   የ84 ዓመቱ አረጋዊ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ዛሬ ቅዳሜ፣ ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ 11፡30 ላይ፣ ከስኳር እና ከልብ ሕመም ጋራ በተያያዘ የኩላሊት መድከም፣ በሕክምና ሲረዱ በቆዩበት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ዐርፈዋል፡፡   በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ፣ በ1971 ዓ.ም. ለጅማ ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፡-   • ከ1971 እስከ 1976 ዓ.ም. የጅማ፣ • ከ1976 እስከ 1978 ዓ.ም. የካፋ፣ • ከ1978 እስከ 1981 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ • ከ1981 እስከ 2001 ዓ.ም. የደቡብ ጎንደር፣ • ከ2001 እስከ 2011 ዓ.ም. የሰሜን ጎንደር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመኾን፣ ቤተ ክርስቲያንን ለ41 ዓመታት በትጋት አገልግለዋል፡፡   ጥንቱንም ለሢመተ ጵጵስና ለመመረጥ ያበቃቸው፣ ከማሕሌት ቁመት እስከ ዐውደ ምሕረት ስብከት የዘለቀው ሙሉ አገልግሎታቸው ሲኾን፣ በሕመም ምክንያት እስከተወሰኑበት ጊዜ ድረስ፣ ከተማና ገጠር ሳይመረጡ በትጋት፣ በደግነትና በሰላማዊነት አባታዊ ሓላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡  

his-grace-abune-elsa-on-apostolic-duty

በፊት ስማቸው መሪጌታ አባ ኅሩይ ይባሉ የነበሩት ብፁዕነታቸው፣ ለሢመት ተጠርተው ሲመረጡ፣ በደብረ ጽጌ ገዳም፣ የድጓ እና የዝማሬ መዋስዕት መምህር ነበሩ፡፡ መጻሕፍተ ሐዲሳትንና ፍትሐ ነገሥትን በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተምረዋል፤ የቅኔና የአቋቋም ዐዋቂም ነበሩ፡፡   በአራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እና በስድስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ምርጫ ወቅት፣ በዕጩነት ከቀረቡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አንዱም ነበሩ፡፡   በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት፣ አፈርዋናት ወረዳ፣ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዴዎስ ደብር፣ በ1927 ዓ.ም. የተወለዱት የአንጋፋው አባት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ሥርዐተ ቀብር፣ በኑዛዜያቸው መሠረት በዚያው ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡  

his-grace-abune-elsa-on-32-sgga

በመጪው ሰኞ፣ በጎንደር መስቀል ዐደባባይ የስንብት መርሐ ግብር መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፤ የሥርዐተ ቀብራቸውን ዕለትና ሰዓት፣ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ስብሰባውን በማካሔድ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖ እንደሚያስታውቅ ይጠበቃል፡፡   የብፀዕነታቸው በረከት ይድረሰን፤ አሜን፡፡