26 ሜይ 2019

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትልፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳና የገቢዎች ሚንስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት የሰላሌ ኦሮሞ ባህል ማዕከልና የብ/ጀኔራል ታደሰ ብሩ ሐውልት በፍቼ ከተማ ዛሬ ተመርቋል።
የሰላሌ ኦሮሞ ባህል ማዕከል በ91.5 ሚሊየን ብር የተገነባ ሲሆን የመሠረት ድንጋዩ የተቀመጠው በ2005 ዓ.ም ነበር።
የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ካበቃ በኋላ በተጠናቀቀው የባህል ማዕከል አዳራሽ ውስጥ ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በዕለቱም “ብ/ጀኔራል ታደሰ ብሩ ተማሩ አለ፤ ዶ/ር ኃይሌ ፊዳ የምንማርበትን መሣሪያ ፈጠሩልን” ሲሉ ዶክተር ዐብይ የተናገሩ ሲሆን ብ/ጀኔራል ታደሰ የኦሮሞ ትግል እንዲቀጥል መሠረት የጣሉ ናቸውም ብለዋል።
“ብ/ጀኔራል ታደሰ ብሩ ጀግንነትን በጣሊያን ጦርነት ላይ ከተሰውቱ አባታቸው ነው የወረሱት” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ጀግንነትን ከአባታቸው ከወረሱት ብ/ጀኔራል ታደሰ አዲሱ አመራርም ተምሮ ጀግና እንዲሆን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
• ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ማዕድ የቀረቡት ምን ይላሉ?
በንግግራቸው ጣልቃም “ብዙ ሰዎች ‘አብቹ’ እያሉ ይጠሩኛል፤ እስከዛሬ ግን ምክንያቱን አላውቅም” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአራት ዓመታት በፊት የፃፉት ‘ሰተቴ’ መፅሃፍ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ተናግረዋል።
መፅሃፉን የፃፉበት ጊዜ አመቺ ስላልነበር ስማቸውን ቀይረው እንደፃፉት ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለዋል።
እርሳቸው መፅሃፉን በሚፅፉበት ጊዜ እራሳቸውን ሆነው ለመናገር ጊዜው ስላልፈቀደላቸው ‘ሰተቴን’ ሆነው እንደ እብድ የውስጣቸውን መተንፈሳቸውን ገልፀዋል።
ይህንን መፅሃፋቸውን አንብበው አሊያም ደግሞ ዐብይ ለሚለው ስማቸው ለ ‘አብቹ’ ስለሚቀርብ ሰዎች እንደዛ ብለው እንደሚጠሯቸው ግምታቸውን ተናግረዋል።
“በመፅሃፉ ውስጥ ‘አብቹ’ ስለሚባል ሰው ፅፌ ነበር፤ ምክንያቱ ለዚህ ይሆናል” ብለዋል። አብቹ የዚያ አካባቢ ጀግና እንደነበር ይነገራል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ “እንደ ‘አብቹ’ ጀግና ለመሆን ግን ለወደፊት ትልቅ የቤት ሥራ ይጠበቅብኛል” ሲሉም ተደምጠዋል።