Source: https://www.zehabesha.com/amharic/archives/95506
May 27, 2019
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ብአዴን የሚባል የምሳር እጀታ ህወሀት በሚባለው ምዕራባውያንና አረቦች በቀጠቀጡት ምሳር ገብቶ አማራን ከሰላሳ ዓመታት በላይ አስጨፍጪፏል፡፡ ብአዴን በሰማእታት መሰዋእትነት ህወሀት ተሚባለው ምሳር በግድ ሲላቀቅ ደሞ ወነግ ተሚባለው ምሳር እንደ አመንዝራ ተሰክቷል፡፡ ትናንት በህወሀት የምሳር ቀለበት ሰተት ብሎ ገብቶ አማራን ሲያስገድል፣ ሲያሳር፣ ሲያስገርፍ፣ ሲያሰልብ፣ ሲያሰድድ፣ ሲያደኸይ፣ ሲያሳምምና አንገት ሲያስደፋ ኖሯል፡፡ እንደ አለመታደል ዛሬ ደግም ያለወላጅ ፈቃድና ያለሰርግ ራሱን ለወነግ ምሳር ድሮና በቀለበቱ እንደ ቅርቃር ተቸክሎ ከሌላው ቀርቶ ከቤጌምድር፣ ከወሎ፣ ከሸዋና ከጎጃምም አማራን ሲያስጨፈጭፍና እንደ ዘፀዐቱ ዘመን ሲያሰድድ ይውላል፡፡ እንግዲህ አማራ ይኸንን እንደ ደን የሚያስጨፈጪፈውን እጀታ እስከመቼ በትከሻው ይሸከማል?
በአምስቱ ዘመን የአማራ ተጋድሎ በባንዳነት ያገለገሉ እርጉሞች ከነፃነት በኋላ ተሸማቀው አካካባቢያቸውን እየለቀቁ ከማይታወቁበት አገር ጅራታቸውን እንደ ውሻ ወትፈው ይኖሩ ነበር፡፡ ዓይን አውጣ ብአዴናዊ ባንዳዎች ግን የሰማእታትን ድል ቀምተው የባርነት ወንበራቸውን ለመጠበቅ ለነፃነት የሚታገሉትን ወጣቶች ህወሀት ባሰለጠናቸው የክፍልፋይ ስልጠና ሲከፋፍሉ ይታያል፡፡ ሕዝቡን በአዴፓነት እንደታደሱና ብአዴን ከድሮ ገራፊ አለቃቸው በረከት ጋር ወህኒ የገባ አስመስለው ያታልሉታል፡፡ አንዳንዱ ዘልዛላም አዴፓ ብአዴን ጋሰለም አረሩ መሆኑን ዘንግቷል፡፡
ባደኩበት ሰፈር አቶ አረሩና አያ አዳነ የሚባሉ ሰዎች ይኖሩ ነበር፡፡ አቶ አረሩን ኮስማናዋ እናቱ እማማ ሐብትሽ ምን እያበሉ እንዳሳደጉት አላውቅም ቁመናው የገደል ግማሽ ያኻክል ነበር፡፡ ጥምቡልዝ መልኩም የተወቀጠ ኑግ ይመስል ነበር፡፡ አቶ አረሩ የገደል ግማሽ እንደሚያህል ለመግለጥ የሰፈሩ ሕዝብ ” አረሩ ብቻውን የቤት ጣራ ተሸክሞ መሄድ ይችላል” ይለው ነበር፡፡ አያ አዳነ በተቃራኒው ቁመናዋ እንደ ስንበሌጥ የሰነነች መልኳም በቀይና በቀይዳማ መካከል ያለች ቆፍጣና ጎበዝ ነበረች፡፡ አቶ አዳነ በሰንጢ ንግግሯ እንደ አለቃ ገብረ ሃና የምትታወቅ ጠቢብ ነበረች፡፡ የአያ አዳነን የንግግር ሥስለትነት ለመግለፅ ማህበረሰቡ “የአዳነ ንግግር ያልጋለ ብረት ከመቅፅበት ይቆርጣል” ይላት ነበር፡፡
በዚሁ ሰፈር ካቶ አረሩ በተጨማሪ አረሩ የሚባል ጠብደል ጥቁር አለሌ ይኖር ነበር፡፡ አቶ አረሩ ከአለሌው ለመለየትና አረሩ የተባለውም የተቀቀጠ ኑግ በመሰለው ቆዳው ምክንያት ስለመሰለው ባካባቢው ባልተለመደ መንገድ ስሙን ጋሰለ ወደ እሚባል ስም ቀየረና አረፈው፡፡ ይኸንን በአካባቢው ያልተለመደ የሥም ለውጥ የተረዳ አብዛኛው የአቶ አረሩን ሥም በየቤቱ እያነሳ እየጣለ ሌላውም “ሥሙን መለወጥ መብቱ ነው!” እያለ የአንድ ሰሞን የቡና ቴራቲም ወሬ አደረገው፡፡
ብዙውን ጊዜ ተመንጋው ጋር የማትነዳዋ አያ አዳነ ግን የአቶ አረሩ ድንገተኛ ሥም ቅየራ የአንድ ሰሞን የቡና ወሬ አድርጋው ማለፍ አልፈቀደችም፡፡ አብዛኛው ሰው አቶ አረሩን በአዲሱ ስሙ ጋሰለ እያለ ሲጠራው አያ አዳነ ግን በሥሙ አፍሮና በማንነቱ ተሸማቆ ስም በቀየረው አቶ አረሩ በሽቃ በማያስፈልገው ቦታ ሁሉ “አረሩ” ብላ እየተጣራች አስቸገረችው፡፡ ይኸንን የአያ አዳነን ጥኑ አቋም የተመለከቱ ሽማግሌዎችም አረሩን በፈለገው ስም ጋሰለ ብላ እንድትጠራው አያ አዳነን ቢለምኗትም “ሥምን የሚያወጣው ወላጅና እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ እናቱ እማማ ሐብትሽ ባወጡለት ሥም ነው የምጠራው” ስትል በአቋሟ ጠናች፡፡
ባያ አዳነ እምቢተኝነት ያልተደሰተው የድሮው አረሩ ያሁኑ አቶ ጋሰለ በበኩሉ “አዳነ ጋሰለ ብሎ ታልጠራኝ ምላሱን እቆርጠዋለሁ” እያለ በሰፈሩ ማስወራቱን ቀጠለ፡፡ ዳሩ ግን ጋሰለ የሚባል ሥም ከአያ አዳነ አንደበት እንኳን በውኑ በህልሙና በቅዠቱም አልወጣ አለ፡፡ እንዲያውም አያ አዳነ በበነነ በተነነው “አረሩ….” የሚለውን ቃል ከወትሮውም በበለጠ እያነሳች አቶ ጋሰለን ማሳቀቁንና እንደዚህ ዓይነት በራስ ተሸማቆ ሥምን የመቀየር ባህል እዳይለመድ ማስተማሩን ቀጠለች፡፡
አቶ ጋሰለና አያ አዳነ በእንዲህ ዓይነት ውጥረት ውስጥ ሳሉ በአንድ የሰንበት ቀን አያ አዳነ አቶ ጋሰለ ጋቢውን ተከናንቦ ድንኳን መስሎ አህያው አረሩ ሳር ከሚግበት መስክ ተቀምጦ አየችው፡፡ አያ አዳነም በአቶ ጋሰለ አጠገብ ስታልፍ “ደህና አደርክ አረሩ” የሚል ሰላምታ አቀረበች፡፡ አቶ ጋሰለ ሰላምታውን እንዳልሰማ ሁሉ “ምን አልክ?” ሲል በንዴት ጠየቀ፡፡ አያ አዳነም በሽመሉ አለሌውን አረሩን እየጠቆመች “ያኛውን አረሩ ነው!” ስትል መለሰች፡፡
እናቱ እማማ ሐብትሽ ያወጡለትን ስም በማንነቱ አፍሮ እንደቀየረው አቶ አረሩ ብአዴንም እናቱ ህወሀት ያወጣችለትን ሥም በማንነቱ አፍሮ በድንገት ቀየረው፡፡ በአለሌው አረሩ ሥም እንደተሰየመው አቶ አረሩ ሁሉ ብአዴንም እናቱ ህወሀት ባወጣችለት ሥምና በባርነት ግብሩ ተሸማቀቀ፡፡ ይህ የተሸማቀቀ ውርጃ ድርጅትም ሥሙን ወደ አዴፓ ቀየረና አረፈ፡፡
ዳሩ ግን ጋሰለ የሚለው ስም የአቶ አረሩን መልክና ምንነት እንዳልቀየረው ሁሉ አዴፓ የሚለው ሥም የብአዴንን መልክና ምንነት አይቀይረውም፡፡ አዴፓ የሚለው ስም ብአዴን ለሰላሳ አመታት በአማራ ሕዝብ የፈጠመውን ወንጀልና ክህደት እንደ እንዶድ አያፀዳውም፡፡ አዴፓ የሚለው ሥም ብአዴን የህወሀት አጋሰስ ሆኖ እየተጫነ ያዘረፈውን ሐብት አያስመልሰውም፡፡ አዴፓ የሚለው ሥም ብአዴን የአማራን ዓይን ጨፍኖ ለህወሀት ያስረከባቸውን ራያን፣ ሁመራና ወልቃይትን አይመልስም፡፡
አዴፓ የሚለው ማታለያ ብአዴን ከቢሮው ጣራ አልሞ ተኳሽ አንጠልጥሎ ባህርዳር ያሰዋቸውን ወጣቶች ነፍስ አይመልስም፡፡ አዴፓ የሚለው ጅል ስም ብአዴን በህወሀት አሽከርነት በድብቅ ስፍራዎች ያስቀበራቸውን፣ ያሰለባቸውን፣ ያስገረፋቸውን፣ ያስጠለፋቸውና አካለ ጎደሎ ያስደረጋቸውን ዜጎች አይታደግም፡፡ አዴፓ የሚለው ሥም ብአዴን በአምባ ጊዮርጊስ፣ በጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ዳንግላ፣ ቡሬ፣ ወልዲያ፣ ማጀቴና ሌሎችም ቦታዎች ያስፈጃቸውን ዜጎች አያስረሳንም፡፡
አዴፓ የሚለው ማታለያ ብአዴን “አያገባኝም” እያለ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በጉራፈርዳ፣ በጎሬ፣ በወለጋ፣ በመተከል፣ በሀገረ ማርያምና ሌሎችም ሥፍራዎች ያስፈጃቸውንና ያሰደዳቸውን አማሮች ታሪክ አይፍቀውም፡፡
ስለዚህ አቶ ጋሰለ አረሩ ነው፡፡ አዴፓም ብአዴን ነው፡፡ እማማ ሐብትሽ ለልጃቸው ያወጡለት ሥም አረሩ ነው፡፡ ከአማራ መቃብር ሪፐብሊኳን ለመመስረት አጋዥ ልጆች የወለደችው ሕወሀትም ለበኩር ልጇ የሰጠችው ሥም ብአዴን ነው፡፡
አረሩም ሆነ ብአዴን ካለ እናቶቻቸው ፈቃድ ሥማቸውን መቀየር ክህደት ነው፡፡ አረሩ ሺ ጊዜ ሥም ቢቀይር እናቱም ሺ ጊዜ እማማ ሐብትሽ ናት፡፡ ብአዴንም ሺ ጊዜ ሥም ቢቀይር እናቱ ሺ ጊዜ ህወሀት ናት፡፡ በአፈጣጠራቸው አፍረው አረሩም ሆነ ብአዴን ሥማቸውን ቢቀይሩም እናታቸው፣ መልካቸው፣ ግብራቸውንና ታሪካቸው ዘላለማዊ ናቸው፡፡ ስለዚህ መልካቸውን፣ ግብራቸውንና ታሪካቸውን በሚገልጡትና እናቶቻቸው ባወጡላቸው ሥሞች አረሩና ብአዴን ተብለው ቢጠሩ መልካም ነው፡፡ ጋሰለ አረሩ አዴፓም ብአዴን ነው፡፡
ብአዴን ዛሬም የድሮ ጌታው ህወሀት ያወጣለትን የእጅታ ስም የቀየረው የዛሬውን ጌታውን ወነግ ቁጥር-2ን ተከትሎ ነው፡፡ ወነግ ቁጥር-2ን እንደ ዓይነ-ሥውር እየተከተለ የብአዴን ሥራ ግን ዛሬም አማራን እንደ አልተፈለገ ጫካ ማስጨፍጨፍ ነው፡፡ ይህ የማያቋርጥ የብአዴን የሎሌነት ባህሪ የሚያመለክተው የብአዴን “መሪዎች” የባርነት ጅን ተሸካሚዎች መሆናቸውን ነው፡፡ የምርምር ሥነ-ምግባር ቢፈቅድና እነዚህ እጀታዎች የዘር ሰንሰለታቸው (ክሮሞዞማቸው) ቢጠና እንደ ጠማማው እንጨት የሎሌነት ጂን ተሸካሚዎች ሆነው እንደሚገኙ እሙን ነው፡፡ እንደ ጠማማው እንጨት የሎሌት ጅን ተሸካሚ በሆነው እርጉሙ ብአዴን አማራ እስከ መቼ አንገቱን ይድፋ? አማራ እንደ ጫካ የሚያስጨፈጪፈውን የምሳር እጀታ እስከ መቼ በትከሻው ይሸከም?
ግንቦት ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም. Sponsored by Revcontent