ሐራ ዘተዋሕዶ
May 31, 2019

- ብፁዕ አቡነ አብርሃም ራብዕ፣ የመካከለኛው ካናዳ እና አካባቢው ጳጳስ ኾኑ፤
- ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ በገዳማት መምሪያ የበላይ ሓላፊነት ተወስነው ይሠራሉ፤
- የአድባራት የበላይ ጠባቂ ጳጳሳትን ሓላፊነት እና ተግባር ዝርዝር ይወስናል፤
- በሀገር ውስጥ ተመድቦ ላለመሥራት፣ የጤና እክልን በመከላከያ ያቀረቡ አሉ፤
- በቋሚ ሲኖዶስ በሚታዩ አቤቱታዎች እና በሥልጣኑ ጉዳይ መመሪያን ሰጠ፤
***
- የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውዝግብ፣ በአስቸኳይ ተጣርቶ እንዲቀርብ አዘዘ፤
- በአትላንታው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ያዕቆብ ላይ በቀረበ ሪፖርት መነጋገር ጀመረ፤
- በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸምና ዘረኝነት ችግር እንዳለባቸው አረጋገጠ፤
- በሊቀ ጳጳሱ ምክንያት ከ4ሺሕ በላይ ምእመናን ሳይበተኑ እንዲነሡ ተጠየቀ፤
- ውዝግቡ ወደ ፍ/ቤት አምርቶ ምእመኑን ከ700ሺ ዶላር በላይ ወጪ ዳርጓል፤
***
ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በዛሬ ረቡዕ፣ ግንቦት 22 ቀን የቀትር በፊት ስብሰባው፣ አምስት የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ያቀረቡትን የድልድል ማስተካከያ ጥያቄ መርምሮ ውሳኔ አሳለፈ፤ በቋሚ ሲኖዶስ የሚታዩ አቤቱታዎችን አግባብነትና ሥልጣኑን በተመለከተ ደግሞ መመሪያ ሰጠ፡፡
የአባቶች ዕርቀ ሰላምን ተከትሎ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድነት ባካሔደው ያለፈው ጥቅምት ምልአተ ጉባኤው፣ አዲስ የአህጉረ ስብከት ድልድልና የ34 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምደባ ያደረገ ሲኾን፣ በካናዳ እና በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት የተመደቡ አምስት አባቶች፣ ይስተካከልልን የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በዋሽንግተን ዲሲ የደብረ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል እና ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፤ የፔንሲልቫኒያ ስቴት ሊቀ ጳጳስ እና በባልቲሞር የመካነ ሰላም ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የገዳማት መምሪያ የበላይ ሓላፊ እና በዋሽንግተን ሲያትል የመካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፤ የዋሽንግተን ስቴትና አካባቢው ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አባ ማርቆስ እንዲሁም በካናዳ የኤድመንተን ከተማ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡
የድልድል ማስተካከያ ጥያቄአቸው፥ ከአገልግሎት አፈጻጸም፣ የአገልግሎት ቅድምናን ከመጠበቅና ከጤና እክል ጋራ የተያያዘ እንደኾነ ተገልጿል፡፡ የአድባራት የበላይ ጠባቂነት የተመደቡት፣ በድልደላው የአገልግሎት ቅድምና እንዳልታየላቸው ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ከእነርሱም፣ አድባራቱ ካሉበት ሀገረ ስብከት ተከፍሎ እንዲሰጣቸው የጠየቁ መኖራቸው ተመልክቷል፡፡ ወደ ሀገር ውስጥ ተዛውረው እንዲሠሩ ሲጠየቁ፣ በጤና እክል ሳቢያ እንደማይችሉ የገለጹም አሉበት፡፡
ኾኖም ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በኹለት ምደባዎች ብቻ መለስተኛ ለውጦች በማድረግ ብዙዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት ባሉበት እንዲጸኑ ነው የወሰነው፡፡ ከሀገር ውስጥም ከውጭም በተውጣጡ ስድስት ብፁዓን አባቶች ጥምር ኮሚቴ በጥናት የተሠራ ድልደላ እንደኾነና መሠረታዊ ማስተካከያ እንደማያስፈልገው በውሳኔው አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት፡- ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የገዳማት መምሪያ የበላይ ሓላፊነቱን ብቻ እንዲይዙና ከዋሽንግተን ሲያትል መካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂነት እንዲነሡ ወስኗል፡፡ የኤድመንተን ከተማ ጳጳስ

ብፁዕ አቡነ አብርሃም ራብዕ፣ በከተማው የሚገኘውንና ቀድሞም መቀመጫቸው የኾነውን የመድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እንደያዙ፣ ወደ መካከለኛው ካናዳና አካባቢው ሀገረ ስብከት እንዲዛወሩ ወስኗል፡፡ የኤድመንተን ከተማም እንደ ቀድሞው፣ የምዕራብ ካናዳና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በኾኑት ብፁዕ አቡነ ማትያስ ሥር(ብሪቲሽ ኮሎምቢያ፣ አልበርታና ኤድመንተን) እንዲኾን ወስኗል፡፡ መካከለኛው ካናዳና አካባቢው ሀገረ ስብከት፣ በጥቅምቱ ድልድል፣ ለሶማሌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ተደርቦ የተሰጠ እንደነበርና ብፁዕነታቸው እንደማይፈልጉ ባመለከቱት መሠረት ያለምደባ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የዋሽንግተን ዲሲ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና የባልቲሞር መካነ ኢየሱስ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ(የፔንሲልቫኒያ ስቴት ሊቀ ጳጳስ)፣ ባሉበት ሓላፊነት ይቀጥላሉ፡፡ ከአምስቱ ቅሬታ አቅራቢዎች ውስጥ፣ የአድባራት የበላይ ጠባቂ ለኾኑት ሦስቱ ብፁዓን አባቶች፣ ሓላፊነታቸውና ተግባራቸው በውሳኔው ቃለ ጉባኤው በዝርዝር ተገልጾ እንዲሰጣቸው ቅዱስ ሲኖዶሱ አዟል፡፡
በተ.ቁ.(7) የሰፈረውን፣ የሀገረ ስብከት ድልድልና ምደባ ይስተካከልን ጥያቄ በዚህ መልኩ ያጠቃለለው ምልአተ ጉባኤው፣ ከቀትር በኋላ በነበረው ውሎ፣ በተ.ቁ(8) ወደያዘው አጀንዳ ተሸጋግሯል፡፡ በአጥኚ ልኡካን ማጣራት የተካሔደባቸውንና በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በኩል የቀረቡ የአምስት አህጉረ ስብከት (በሰሜን አሜሪካ የአትላንታ ሰዓሊተ ምሕረት፣ በፊላዴልፊያ የቅዱስ ዐማኑኤል፣ የደቡብ አፍሪቃ፣ የካፋ እና የኢየሩሳሌም ገዳማት) ሪፖርቶችን በአጀንዳው መርምሮ ውሳኔ ይሰጥባቸዋል፡፡
በመጀመሪያ የተመለከተውና የቀትር በኋላውን ሙሉ ክፍለ ጊዜ የወሰደው፣ በአትላንታ የሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አባ ያዕቆብ እና በምእመናን መካከል ስለተፈጠረው አለመግባባት የቀረበው ሪፖርት ነው፡፡ የአጣሪ ልኡኩ አባልና የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ባልደረባ ቀሲስ በላይ ጸጋዬ፣ ሪፖርቱን ለምልአተ ጉባኤው በንባብ አሰምተው መነጋገር የጀመረ ሲኾን፣ ሳይቋጭ በይደር ተነሥቷል፡፡
በ26 ገጾች የተጠናቀረው የልኡኩ ሪፖርት፣ ሊቀ ጳጳሱን በመቃወምና በመደገፍ የተሰለፉ ካህናትንና ምእመናንን አቤቱታዎች በንጽጽር በመጥቀስና የደረሰበትን ግንዛቤ በማስፈር ውሳኔውን ለቅዱስ ሲኖዶስ የሚተው ነው፡፡ ከሪፖርቱ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ብዙኀኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናትና ምእመናን፣ ሊቀ ጳጳሱን የሚቃወሙና እንዲነሡላቸው የሚጠይቁ ናቸው፤ በአንጻሩ ለተቃውሞው ማኅበረ ቅዱሳንን በመክሠሥና ሊቀ ጳጳሱን ንጹሕ በማድረግ እንዲቆዩላቸው የሚፈልጉ ጥቂቶች ናቸው፡፡

በሊቀ ጳጳሱ ላይ ከተሰሙት አቤቱታዎች ከአንዱ በቀር ከፊሎቹን፣ በማስረጃም በትዝብትም ማረጋገጡን ልኡኩ በሪፖርቱ አስፍሯል፡፡ ሊቀ ጳጳሱ፥ የዘረኝነትና ወገንተኝነት ችግር እንደተስዋለባቸው፣ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸም ስሕተት መፈጸማቸውንና “ተኣምረ ማርያም አይነበብም” ለተባለውም ማረጋገጫ ማግኘቱን ገልጿል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ከተወገዘውና ዛሬም በኑፋቄው ከቀጠለው ልዑለ ቃል አካሉና ሌላው መናፍቅ መላኩ ባወቀ፣ ከቴክሳሱ ትዝታው ሳሙኤል እና ከመሳሰሉት ግብረ አበሮቻቸው ጋራ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከባድ ፈተና ላይ እንደጣሏት ነው ብዙኀኑ ያስረዱት፡፡
አሁን፣ ካህናቱና ምእመናኑ በኹለት ወገን ተከፍለው እየተፈራረቁ ቤተ ክርስቲያኑን እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡ ይህም በተለይ ለተተኪው ትውልድ ከሚያስተላልፈው መጥፎ ጫና አንጻር መቀጠል እንደሌለበት ነው የሚታመነው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ከሚበዛው ወገን ጋራ ከፈጠሩት አለመግባባትና በማጣራቱ ከተረጋገጠባቸው ድክመት አንጻር፣ ምልአተ ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያን ያደላ ውሳኔ ሊያሳልፍ ይገባል፡፡ ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት አምርቶ ከ700ሺሕ ዶላር በላይ ወጪ ከኾነ በኋላ ሊቀ ጳጳሱ ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ ባለፈው ግንቦት 10 ቀን 2011 ዓ.ም(May 18, 2019) ፍርድ ቤቱ ምዕመኑን ስብስቦ ድምፅ አሰጥቶአል፡፡ ቁጥሩ ከ400 በላይ የኾነው ምእመን፣ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አባ ያዕቆብ፣ ከአትላንታና አካባቢዋ እንዲነሡ ድምፅ ሲሰጥ፣ አይነሡ በማለት ድጋፍ የሰጧቸው 100 እንኳን አይሞሉም፡፡
ምእመናኑ፣ ይህን ተጨባጭ ኹኔታ በመጥቀስ ለቅዱስ ሲኖዶስ ባስተላለፉት መልእክት የሚከተለውን ተማኅፅኖ አቅርበዋል፡- “አቡነ ያዕቆብ ወደዱም ጠሉም፣ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከዚህ አካባቢ መባረራቸው አይቀርም፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶስ በዚሁ ምልዓተ ጉባኤው፣ በአንድ ጳጳስ ምክንያት ከ4,000 ቁጥር በላይ ያለው በ7 ስቴት ውስጥ የሚገኘውና የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕዳ እየከፈለ ያለው ምስኪን ምእመን እንዳይበተን ያስብለት፤ በአቡነ ያዕቆብ ተነሥተው በምትካቸው የምእመናን አንድነትና ፍቅር የሚገደው መልካም እረኛ የሚኾነን እንዲመድብልን፣ የተበተነው እንዲሰበሰብ፣ የተከፋፈለው አንድ እንዲኾን እንዲያደርግልን አጥብቀን እንማፀናለን፤” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ከእኒህ ኹለት አጀንዳዎች ቀደም ሲል ሲያከራክር በቆየውና በተ.ቁ.(6) በሰፈረው፣ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጉዳይ ትእዛዝ የሰጠው፣ ከትላንት በስቲያ ከቀትር በኋላ ነበር፡፡ የካቴድራሉ ሦስት የአስተዳደር ሓላፊዎች ከቦታው ተነሥተው እንዲዛወሩ ቋሚ ሲኖዶስ ያስተላለፈውንና ከፓትርያርኩ ጋራ አለመግባባት ያስከተለውን ውሳኔ አሰጣጥ መርምሯል፡፡ በአስተዳዳሪው፣ ዋና ጸሐፊው እና ሒሳብ ሹሟ ላይ አቤቱታ ያቀረቡት ሠራተኞችና ምእመናን ጥያቄ፦ የቅርስ ማውደሙ፣ ምዝበራው፣ አድልዎው፣ የአሠራር ጥሰቱ ይጣራልን፤ የሚል እንደኾነና ሓላፊዎቹ እንዲዛወሩ መወሰን ጊዜውን ያልጠበቀ በመኾኑ ማጣራቱ መቅደም እንደነበረበት አስገንዝቧል፡፡
በመኾኑም፣ በኹሉም ወገን የቀረቡ አቤቱታዎችን አጣርቶ በአስቸኳይ የሚያቀርብ፣ ከሀገረ ስብከትና ከጠቅላይ ጽ/ቤት የተውጣጣ ሦስት አባላት ያሉት ልኡክ ሠይሟል፡፡ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዋና ሓላፊ አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሐና እንዲሁም፣ የስብከተ ወንጌል ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ ኅሩያን ሠርጸ አበበ የልኡኩ አባላት ሲኾኑ፣ በተቻለ መጠን እስከ ስብሰባው ፍጻሜ ሪፖርታቸውን አጠናቀው እንዲያደርሱ፣ ካልተቻለ በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ እልባት እንዲሰጠው ነው ያዘዘው፡፡
ከዚሁ ጋራ በተያያዘ ምልአተ ጉባኤው፣ በአጀንዳ ተ.ቁ.(7) በሰፈረው፣ የቋሚ ሲኖዶስ ሥልጣንና የሥራ አፈጻጸም ከተነጋገረ በኋላ መመሪያ ሰጥቷል፡፡ ቋሚ ሲኖዶሱ የተመለከታቸው አቤቱታዎች(ቅሬታዎች)፣ የውሳኔዎች አሰጣጥና አፈጻጸማቸው፣ እያጋጠማቸው የሚገኘው አክል በመነሻነት ቀርበው ተወያይቶባቸዋል፡፡ ቋሚ ሲኖዶሱ፣ የምልአተ ጉባኤው መመሪያዎችና ውሳኔዎች በሥራ መተርጎማቸውን የሚከታተል ተቆጣጣሪ አካል እንደመኾኑ፣ በይግባኝ የሚመለከታቸው አቤቱታዎች፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ መታየታቸውንና ደረጃቸውን ጠብቀው መቅረባቸውን አስቀድሞ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልገው ተጠቅሷል፡፡
እንደ ጉዳዩ ኹኔታ ተመልክቶ በአግባቡ ያሳለፈው ውሳኔም በሚመለከታቸው አካላት ተፈጻሚ ሊኾን እንደሚገባ ምልዓተ ጉባኤው አሳስቧል፡፡ ፓትርያርኩ በሰብሳቢነት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በቋሚ አባልነት የሚገኙበት ቋሚ ሲኖዶሱ፣ በየሦስት ወራቱ የሚቀያየሩና በምልአተ ጉባኤው የሚሠየሙ አራት፣ አራት ብፁዓን አባቶችን በተለዋጭ አባልነት የያዘ የቅዱስ ሲኖዶሱ አካል ነው፡፡