አዲስ ዘመን

“የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ለ27 ዓመታት ስልጣን ላይ ቆይቶ ከህዝብ ጋር የተለያየው መዋቅራዊ ችግሮች ስለነበሩ ነው፡፡ እነዚህ መዋቅራዊ ችግሮች በዋናነት የተያያዙት ከህገመንግስቱ እና ከፌዴራል አደረጃጀቱ ጋር ናቸው፡፡ በእነዚህ ዙሪያ በቂ ውይይት አድርጎ አስታራቂ ሃሳብ እና ብሔራዊ መግባባት ማምጣት ሳይቻል ሌሎች ችግሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህን መዋቅራዊ ችግር ለመፍታት የሃሳብ ነፃነትን በማክበር፣ ከውጪ ያሉትን ፓርቲዎች በማስገባት፣ እስረኛን በመፍታት ብቻ ሊፈታ አይችልም፤ መዋቅራዊ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ወደ በጎ አቅጣጫም አይወስደንም፡፡ ስለዚህ ከቅደም ተከተል አንፃር መንግስት ትክክለኛው አቅጣጫ ላይ ነው ብዬ አላምንም” ያሉት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች አነጋግረን ሀሳባቸው እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
አዲስ ዘመን፡– በአገሪቷ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ ምን ይላሉ?
አቶ ልደቱ፡- አሁን ላይ ብዙ ተስፋዎች እና ብዙ ስጋቶች አሉ፡፡ ለውጡ ከመጣ አንድ ዓመት ሆኗል፡፡ በዚህ ዓመት ውስጥ ብዙ የተገኙ ውጤቶች እንዳሉ ሁሉ አዳዲስ የተፈጠሩ ችግሮችም አሉ፡፡ ስለዚህ ከአሁን በኋላ ያለንን ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመን ጉድለ ቶቹን በደንብ ለይተን አውቀን እንዲሟሉ ካደረግን ተስፋዎቹ የበለጠ እየጠነከሩ አገሪቷም ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ትገባለች፡፡
ነገር ግን በደንብ መመርመር አቅቶን ሁሉም ነገር በተገቢው ሁኔታ እየሄደ ነው ብለን ካመንን እና እየታዩ ያሉት ስጋቶች በጊዜያቸው እንዲፈቱ ካላደረግን ስጋቱ የበለጠ እየሰፋና እየጠነከረ ሄዶ የአገሪቷንም ህልውና አሳሳቢ የሚያደርግበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ እንደገና አዲስ የለውጥ ፍላጎት ህዝቡ ውስጥ ተፈጥሮ ወደ ሌላ ቅራኔና ግጭት ያድጋል፡፡ አሁን ተስፋውም ስጋቱም በእጃችን ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡– የትኛው ተስፋ፤ የትኛው ደግሞ ስጋት ነው በደንብ አብራሩልኝ?
አቶ ልደቱ፡– ከተስፋው ቢጀመር እንደሚታወቀው ባለፈው አንድ ዓመት ብዙ ነገር ተሰርቷል፡፡ የፖለቲካ እስረኛ አለ ተብሎ አይታመንም ነበር፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸው ታምኖ መፈታታቸው ትልቅ ውጤት ነው፡፡ በአዋጅ እና በህግ ነፃ ፕሬስ ቢኖርም በተግባር ግን ብዙ ጫናና አፈና ነበር፡፡ በዚህ በኩልም ቀላል የማይባል ለውጥ መጥቷል፡፡ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣ ሀሳብ በነፃነት ለህዝብ የሚደርስበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች አገር ውስጥ እና ውጭ ተከፋፍለው የተለያየ ጎራ ውስጥ ነበሩ፡፡ አሁን ውጭ አገር በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ እነዚህ ተስፋዎች ናቸው፡፡ የበለጠ እየጠነከሩ እየሰፉ ከሄዱ አገሪቷን ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሷታል፡፡
እንደስጋት ሊገለፁ የሚችሉት ደግሞ በብዙ የአገሪቷ አካባቢዎች ግጭቶች መታየታቸው ነው፡፡ በሺዎች ሳይሆን በሚሊዮኖች የሚጠጉ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ ተሰደዋል፤ የሞት እና የመ ቁሰል አደጋ የደረሰባቸውም ብዙ ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ማንነት እና በንዑስ ብሔር ማንነት ዙሪያ መግባባት ላይ አልተደረሰም፡፡
ስለዚህ መሰረታዊ የሚባሉ መዋቅራዊ ቅራኔዎች ላይ ቁጭ ብሎ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ በአንድ በኩል ቀደም ሲል የነበሩት ችግሮች አሁን እየተፈቱ መሆኑ ተስፋ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ ቅራኔዎችም እየተፈጠሩ እና እየተጠናከሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ አገሪቷ አሁንም ወደ ሌላ ጥያቄ እና ቀውስ ትገባ ይሆናል የሚል ስጋት አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡– ይህ የጠቀሱት ስጋት እያለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻ ላል?
አቶ ልደቱ፡– የእኔ አመለካከት አይቻ ልም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– በቃ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም?
አቶ ልደቱ፡– አይቻልም፤ ቢቻልም ኖሮ የህዝብ እና ቤት ቆጠራውን ማራዘም ባላስፈለገ ነበር፡፡ የህዝብ እና ቤት ቆጠራው በህግ የተቀመጠ ነው፡፡ እንደውም የህዝብ ቆጠራ ምርጫ ከማካሄድ ይቀላል፤ በተጨማሪ ፖለቲካው ላይ እንደምርጫ የህዝብ ቆጠራው የሚያስፈልግ አይደለም፡፡ በህዝብ ቆጠራ ከስልጣን የሚወርድም ሆነ ወደ ስልጣን የሚወጣ የፖለቲካ ሃይል የለም፡፡ ስለዚህ የአገሩ የፖለቲካ ሁኔታ የህዝብ ቆጠራ ለማ ካሄድ የማያስችል ከሆነ በምን መንገድ ለስል ጣን የሚያበቃ ምርጫን ማካሄድ ይቻላል?
አዲስ ዘመን፡– ሰላምን ለማረጋገጥ እስከምን መዝለቅ ያስፈልጋል?
አቶ ልደቱ፡– አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩት ችግሮች በሙሉ አሁን የተፈጠሩ አይደሉም፡፡ ለ27 ዓመታት ሲንከባለሉ እየተጠራቀሙ የመጡ ናቸው፡፡ አሁን አመራር ላይ ያለውን ሃይል ለእነዚህ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም፡፡ ቁም ነገሩ አሁን ስልጣን ላይ ያለው ለለውጥ እታገላለሁ የሚለው አመራር ይህን ተገንዝቦ ሲንከባለሉ ሲጠራቀሙ የነበሩትን ችግሮች ተገንዝቦ በአግባቡ መፍታቱ ላይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የለውጡ ኃይል ዘገምተኝነት እየታየበት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
በተለይ ከቅደም ተከተል አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ትልቁ እና ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የህግ የበላይነት፣ የሰላም እና የመረጋጋት ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የአንድ መንግስት የመጀመሪያው ኃላፊነት የዜጎቹን ደህንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ ይህ ሳይጠበቅ የሰብአዊ መብት፣ የዴሞክራሲ፣ የምርጫ ጉዳይ ፋይዳ የለውም፡፡ ሌሎቹ የፖለቲካ ጥያቄዎች በመሰረታዊነት መመለስ የሚችሉት ሰላም እና መረጋጋት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ከቅደም ተከተል አንፃር ይህ መንግስት ተገቢውን ትኩረት ለሰላም እና መረጋጋት አልሰጠም፡፡
ትኩረት የተሰጠው በአዲስ አበባ የወንዞች ልማት ላይ ነው፡፡ በየመገናኛ ብዙሃኑ የሚደ መጠው ይህ ነው፡፡ ምርጫ ይካሄድ አይካሄድ የሚል ክርክርም አለ፡፡ መንግስት ኮሚቴ እና ካቢኔ የማቋቋም የመሾም እና የመሻር ስራ ላይ ተጠምዷል፡፡ ዋናውን የህግ የበላይነት፣ የሰላም እና የመረጋጋት ጉዳይ ሁለተኛ እና ሶስተኛ እያደረገው ነው፡፡
ያለውን ጊዜ ያለውን ጉልበት እና አቅሙን ሁሉ አሟጦ መጠቀም ያለበት የህግ የበላይነት እንዲኖር ማድረግ ላይ ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ ወደ ሌላው መመጣት ያለበት ሰላም እና መረጋጋት ከሰፈነ በኋላ ሊሆን ይገባል፡፡ ሆኖም ግን ትኩረት የተሰጠባቸው ጉዳዮች መዋቅራዊ የሆኑ ችግሮች ላይ ያነጣጠሩ አይደሉም፡፡
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ቅራኔ የመነጨው ከፌዴራል አደረጃጀቱ እና ከህገመንግስቱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለብንን ችግር በበሰለ ሁኔታ ተወያይተን መፍትሔ ሳናስቀምጥ ሌሎች ይህን ችግር ተከትለው የመጡ ችግሮችን ብቻ በመፍታት መፍትሄ ማምጣት አይቻልም፡፡ ችግሩ መዋቅራዊ ስለሆነ መጀመሪያ ለእዚህ ችግር የዳረገን ምንድን ነው? የሚለው ላይ ቁጭ ብሎ ተመካክሮ መሰረታዊ የሆነ መፍትሔ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡
መዋቅራዊ ችግሩን ተከትለው የመጡ ችግሮች ከላይ በተስፋ መልክ እንደተገለጹት ተፈ ተዋል፡፡ ነገር ግን ዋናው መሰረቱ ኢህአዴግ ለ27 ዓመታት ስልጣን ላይ ቆይቶ ከህዝብ ጋር የተለያየው መዋቅራዊ ችግሮች ስለነበሩ ነው፡፡ እነዚህ መዋቅራዊ ችግሮች ከህገመንግስቱ እና ከፌዴራል አደረጃጀቱ ጋር በዋናነት የተያያዙ ናቸው፡፡
በእነዚህ ዙሪያ ላይ በቂ ውይይት አድርጎ በቂ አስታራቂ ሃሳብ እና ብሔራዊ መግባባት ማምጣት ሳይቻል ሌሎች ችግሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ ወደ በጎ አቅጣጫም አይወስደንም፡፡ ስለዚህ ከቅደም ተከተል አንፃር መንግስት ትክክለኛው አቅጣጫ ላይ ነው ብዬ አላምንም፡፡
አዲስ ዘመን፡– አሁን መንግስት ህግ እያስከበረ አይደለም ማለት ይቻላል? እንደተለመደው በኃይል ያለመረጃ አፍሶ ከማስገባት ቀስ በቀስ መረጃ ላይ ተመስርቶ ህግ የማስከበር ስራ መስራት አይሻልም? በእርግጥ ለህግ ማስከበር ትኩረት አልተሰጠም?
አቶ ልደቱ፡– እኔ በሃይል የሚል ቃል አልወጣኝም፡፡ ተወደደም ተጠላ በምርጫም ባይሆን የመጣ መንግስት አለ፡፡ ህዝብም የአሁኑ መንግስት ወደ በጎ አቅጣጫ ያሸጋግረናል በሚል ዕወቅና ሰጥቷል፤ ሊደግፈውም ተዘጋጅቷል፡፡ መንግስትና ህዝብ ተባብረው ሰላም እና መረጋጋትን ማምጣት አለባቸው፡፡ መንግስት ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አሳምኖ ህዝቡን በዙሪያው አሰባስቦ እና ህዝቡን የለውጡ ባለቤት አድርጎ ህግ እና ስርዓት እንዲሰፍን ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህን በህዝብ እንቅስቃሴ በሰላማዊ መንገድ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በኃይል የሚለው አማራጭ እዚህ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡
ሌላው ህግ እና ሥርዓት ጭራሽ ትኩረት አላገኘም ወይ ለተባለው፤ እኔ እንደሚገባኝ ህግና ሥርአት ትኩረት አላገኙም፡፡ አዲስ አበባ የሚኖር ሰው ላያውቅ ይችላል:: ነገር ግን ወጣ ተብሎ በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ህግ እና ሥርዓት አለ ማለት አይቻልም፡፡ አንድ ዜጋ አንድ ችግር ቢደርስበት ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ ቢያመለክት የሚደርስለት የለም፡፡
‹‹እኛ ምንም ልንረዳህ አንችልም ራስህን ጠብቅ›› እየተባለ ነው፡፡ እዚህ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ኢንደስትሪዎችን የሚያስተዳድራቸው ማን ነው? ቢባል የኢንደስትሪ ባለቤቶች ኢንደስት ሪያቸውን በፈለጉበት ሁኔታ ማስተዳደር የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል፡፡ የፈለጉትን ነገር የሚያዙት እና የሚወስኑት የአካባቢው ወጣቶች ናቸው፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር መንግስት ጣልቃ ገብቶ መፍትሔ እያመጣ አይደለም፡፡ ችግራችሁን ራሳችሁ ፍቱ እያለ ነው፡፡
ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ዜጎች መስራት ማልማት የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥ ሯል፡፡ በአገሪቷ ታይቶ የማይታወቅ አሰቃቂ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች ሳይቀሩ በህግ ተጠያቂ መሆናቸው እየታየ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ የህግ የበላይነት አለመኖሩ አጠያያቂ አይደለም፡፡ መንግስት ያለው አሁን በፌዴራል ደረጃ ነው፡፡ እርሱም ደካማ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ጠንካራ እንዲሆን አይጠበቅም፡፡
ወደ ታች ሲኬድ በፓርቲም ሆነ በመንግስት መዋቅር መንግስት አለ የሚባልበት ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡ ከአዲስ አበባ ወጥቶ መመለስ በፀሎት ሆኗል፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ስለምርጫ፣ ስለዴሞክራሲ፣ ስለሰብዓዊ መብት መነጋገር ቅንጦት ነው፡፡ መጀመሪያ ሰላም እና መረጋጋት መስፈን አለበት፡፡ ለአንድ አገር መሰረታዊ ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ አንድ መንግስት መንግስት የሚባለው ይህን ማድረግ ሲችል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– የፖለቲካ ቅራኔ የመነጨው ከፌዴራል አደረጃጀቱ እና ከህገመንግስቱ ነው ብለዋል፡፡ በፌዴራል አወቃቀሩ ላይ ያለዎት ሃሳብስ ምንድን ነው?
አቶ ልደቱ፡– ህገመንግስቱም ሆነ ስራ ላይ ያለው የፌዴራል አደረጃጀት መጀመሪያውኑ በህዝብ ይሁንታ እና በብሔራዊ መግባባት የመጡ መፍትሔዎች አይደሉም፡፡ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ የተፃፈውን የፖለቲካ አጀንዳ በህገመንግስት እና በመዋቅር ስም ወደ ተግባር የለወጠበት ነው፡፡ በአገር ደረጃ ሰፊና ሃቀኛ ውይይት ተካሂዶ እና አንፃራዊ መግባባት ተፈጥሮ አግባብ ባለው ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ የተዋቀረ የፌዴራል አደረጃጀት አይ ደለም፡፡
አንድ ፓርቲ የራሱን እምነት እና ፍላጎት በህዝብ እና በአገር ላይ የጫነበት መንገድ ነው፡፡ 27 ዓመት ሙሉ መንግስት እና ህዝብ መታረቅ ያልቻሉበት እና እንደዚህ አይነት የፖለቲካ ቅራኔ ውስጥ የኖሩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ችግሩ መዋቅራዊ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ መዋቅራዊ ችግር የሃሳብ ነፃነትን በማክበር፣ ከውጪ ያሉትን ፓርቲዎች በማስገባትና እስረኛን በመፍታት ብቻ ሊፈታ አይችልም፤ መዋቅራዊ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል፡፡
እነዚህ አጀንዳዎች ከህዝብ ፍላጎት ውጪ ብሔራዊ መግባባት ሳይፈጠር በአንድ ፓርቲ ፍላጎት ተግባር ላይ የዋሉ በመሆናቸው እንደገና ወደ ውይይት መቅረብ አለባቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ሃይሎች መደራደር እና መወያየት አለብን፤ ከዛ በኋላ አንፃራዊ የሆነ መግባባት ከተፈጠረ በኋላ ህገመንግስቱን የጋራ ማድረግ ይቻላል፡፡
ይህ ሲሆን የፌዴራል አደረጃጀቱም የጋራ ይሆናል፡፡ የጋራ መግባባት ከተፈጠረ ነፃ ምርጫ ተደርጎ የህዝብ መንግስት መቋቋም ይቻላል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ወደ ምርጫ መሄድ አስቸጋሪ ነው፡፡ መሰረታዊ የሚባሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ሳይፈቱ ወደ ምርጫ መሄድ የሚፈለገውን ውጤት አያስገኝም፡፡ እንደውም የበለጠ ያባብሰው እና ከቁጥጥር ውጪ እንዲሄድ ያስገድደዋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር መታየት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡– ስለዚህ ህገመንግስቱ ተቀይሮ?
አቶ ልደቱ፡– ተቀይሮ አይደለም፤ ተሻሽሎ! ህገመንግስቱ በሙሉ መጥፎ ነው ማለት አይደለም፡፡ በህገመንግስቱ ውስጥ ዓለም የተቀበለው ኢትዮጵያም የተቀበለቻቸው ብዙ የሰብአዊ መብት የዴሞክራሲ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ እነርሱን መለወጥ አያስፈልግም፤ ይዘናቸው እንቀጥላለን፡፡ ነገር ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት፣ አብሮነት እና የኢኮኖሚ ዕድገት የማይጠቅሙ አንቀፆች አሉ፡፡ እነዚህን አንቀፆች በህዝብ ውይይት ጤናማ በሆነ እና በሰለጠነ መልኩ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወያይቶ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡
ህገመንግስቱን ማሻሻል በኛ የተጀመረ አይደለም፡፡የተለያዩ አገሮች ህገ መንግስ ታቸውን ብዙ ጊዜ አሻሽ ለዋል፡፡ እኛ ወደ ፖለቲካዊ ቀውስ ከገባን በኋላ እንኳን ህገ መንግስታቸውን ያሻሻሉ አገሮች አሉ። እኛ ይህንን ጉዳይ አንለቅም ብለን አገርን ማተረማመስ ተገቢ አይደለም፤ የፖለቲካ ሰነድ አስከ ሆነ ድረስ በፖለቲካ አንቅስቃሴና ውይይት ሊሻሻል ይችላል። ሆኖም ህገ መንግስቱን የሞት የሽረት ጉዳይ አደርጎ በዚህ ጉዳይ ላይ አንነጋገርም ማለት አነጋገሩ ራሱ ዴሞክራሲያዊ አይደለም።
በሌላ በኩልም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ ሊፈታ የሚችል መፍትሄም አይደለም። ስለዚህ ‹‹ህገ መንግስቱ ተቀዶ ይጣል›› የሚሉ ሰዎች አሉ:: እኔ ይህንን አልቀበልም፤ ምክንያቱም ህገ መንግስቱ ውሰጥ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች አሉ። ጉድለቶቹ ግን መሻሻል መለወጥ ደግሞ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፤ የፌደራል አወቃቀሩ በተለይ ደግሞ ቋንቋና ብሔርን ማዕከል አድርጎ መዋቀሩ ላይ የአርስዎ ሀሳብ ምንድን ነው?
አቶ ልደቱ፡– እኔ አመለካከቴን ላለፉት 26 ዓመታት ስገለጽ ነበር፡፡ ቋንቋን መሰረት ያደረገ አወቃቀር ለአገራችን አይጠቅምም ጠቅሞም አያውቅም፤ ስለዚህ ቋንቋ እንደ አንድ መመዘኛ ተደርጎ ሊታይ ቢችልም ብቸኛ መመዘኛ ግን መሆን የለበትም። ለምሳሌ የአስተዳደር የኢኮኖሚ አመቺነት መልከዓ ምድር፣ የህዝብ ብዛት፣ የመሬት ቆዳ ስፋት ከግምት ውስጥ ገብተው የፌደራል አደረጃጀቱ እንደገና መደራጀት ይኖርበታል።
ቋንቋ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የምንጠቀምበት መሆን እንጂ ያለበት የአገሪቱን ፌደራሊዝም ለማደራጀት ብቸኛ መመዘኛ ሆኖ ጥቅም ላይ መዋል አልነበረበትም፡፡ አንዱ ቀውስ የፈጠረበን ይህም ነው:: ስለዚህ በዚህ ደረጃ እኛ አሁን የምናቀርበው መፍትሔ አይደለም::
እኛ የምንናገረው የራሳችንን ሀሳብ ነው፤ ለችግሩ መፍትሔ መስጠት ከተፈለገ ደግሞ ዝም ብለን የእኛን ሀሳብ መግለጽ ሳይሆን ቁጭ ብለን መነጋገር ያስፈልገናል፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ የአንዳችን ሀሳብ አሸናፊ አንዲሆን ሳይሆን የሁላችንም ሀሳብ አሸንፎ በማቻቻል ተማምነን የእኔ የእኔ የምንለውን ትተን ለሁላችንም የሚበጅ እና ሊያስማማን የሚችል ማዕከላዊ መፍትሔ መፍጠር አለብን።
እኔ አሁን የማወራው መፍትሔ የእኔ አውነት ነው ወይም አቋም ነው አንጂ ብቻውን ለአገር መፍትሔ ይሆናል ማለት አይደለም። ከሌሎች ሀሳቦች ጋር መደመር አለበት፤ ለዚህ ደግሞ የሌሎችን ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብኝ፤ አንዲሁ ሌሎቹም የእኔን ሀሳብ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆን አለባቸው፤ በዚህ ዓይነት የመከባበር ፖለቲካ ውስጥ ስንገባ ነው ይህችን አገር ማሸጋገር የምንችለው።
አዲስ ዘመን፤ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከብሔርተኝነት ነጻ ማድረግ ይቻላል ወይ?
አቶ ልደቱ፡- ይህ እንግዲህ በሂደት ይቻላል ብዬ አስባለሁ። አሁን ግን አንዳንዶቹ አንደሚሉት በህግ በማገድ ወይንም ደግሞ በማራከስና በማንቋሸሽ የሚሆን ነው ብዬ አላስብም። አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ሲታይ ወደድንም ጠላንም ጽንፍ ይዟል:: ስለዚህ በብሔር እራሳችውን አደራጅተው ያሉ የፖለቲካ ሀይሎች አሉ::
ስለዚህ የእነዚህ ሰዎች መብትም ደግሞ ሜዳ ሊጣል ስለማይቻል መከበር አለበት። በእኔ እምነት ሰዎች መደራጀት ያለባቸው በዜግነታቸው፣ በአስተሳሰብ እና ለአገር ባላቸው አጀንዳ ነው ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን እኔ እንዲህ ስላመንኩ ሌሎችም በዚህ ሀሳብ ማመን አለባቸው ማለት አልችልም። ምክንያቱም ምርጫቸው ከዚህ የተለየ የሆኑ አሉ፡፡
የሁለታችንንም ሀሳብ ሊያስታርቅ የሚችል ምንድን ነው? ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው አንዱ ችግር በዜግነት በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ የሚደረግ መደራጀት እያጥላሉ ቦታ እያሳጡ በብሔር መደራጀትን ቦታ እየሰጡ እንዲፋፋ የማድረግ ሁኔታ ነበር። አሁንም ደግሞ ሌላውን ማጥላላት የለብንም፤ ሁለቱም ቦታ አግኝተው ጤናማ በሆነ መልኩ ለህዝብ ምርጫ እየቀረቡ የሚፎካከሩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።
ይህ ሲሆን በሂደት አንዱ አሸናፊ እየሆነ ይሄዳል። ይህ ደግሞ ጤናማ አካሄድ ነው። አሁን በህግ በማገድ በተጽዕኖ አንዱን አሸናፊ ለማድረግ መሞከር ግን የበለጠ የቅራኔ አዙሪት ውስጥ ያስገባል። ስለዚህ እኔ የብሔር ድርጅቶች መኖራቸውን ባልደግፍም ቢኖሩ ደግሞ ማክበር አለብኝ፤ በሀሳብ የተደራጁ ፓርቲዎችም መኖር አለባቸው፡፡ ሁለቱን እኩል ትኩረት ማግኘት ያለባቸው ከመሆኑም በላይ ማንም ህዝብ በነጻነት መደራጀት መቻል አለበት።
እንደዚህ ማድረግ ከቻልን አንደኛው እያሸነፈ ይመጣል። ኢኮኖሚያችን እያደገ አስተሳሰባችን እየተቀየረ ለአለም ያለን እይታ እየተቀየረ ሲሄድ ዞሮ ዞሮ ወደ አንድነት መምጣታችን አይቀርም። የሀሳብ ፖለቲካም የበለጠ ቦታ እያገኘ መምጣቱም አይ ቀርም፡፡ ስለዚህ በዚህ መልኩ አንዱ አሸናፊ የሚሆንበትን አድል መፍጠር ይቻላል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሁለቱንም ተቀብሎ መሄድ ግዴታ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– ኢዴፓ ፈርሷል አልፈረሰም የሚሉ ክርክሮች አሉ?
አቶ ልደቱ፡– ምንም ክርክር የለም፡፡ ለኢዴፓ ህጋዊ ዕውቅና የሚሰጠው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ኢዴፓ አለመፍረሱን ገልጿል፡፡ ከዛ በኋላ የኛ መልስ አያስፈልግም፡፡ ፈርሷል የተባለው በውሸት ነው፡፡ ሊያፈርሰው የሚችለው አካል ጭራሽ አልተሰበሰበም፡፡ ሊያፈርሰው የሚችለውን አካል ደግሞ ምርጫ ቦርድ ዕገዳ ጥሎ በታል፡፡ ያ ዕገዳ ባልተነሳበት ሁኔታ ከሌላ ጋር መዋሃድም ውሳኔ መስጠት አይቻ ልም፡፡ ዝም ብሎ ወሬ ነበር ወሬ መሆኑም በሂደት ታይቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ፍርድ ቤት አልወሰነም?
አቶ ልደቱ፡– በዚህ ጉዳይ ላይ የተካሄደ ክርክርም የለም፡፡ ክስም አልነበረም፡፡
አዲስ ዘመን፡– መጋቢት 1 ጉባኤ መካሄዱ እና መፍረሱም ሲጠቀስ ነበር?
አቶ ልደቱ፡- በመተዳደሪያ ደንባችን መሰረት ጠቅላላ ጉባኤውን የሚጠራው በአንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ13 ነጥብ 4 መሰረት ብሔራዊ ምክር ቤቱ ነው፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ብዙሃኑ ያለው ደግሞ እኛ ጋር ነው፡፡ እኛ ያልጠራነው ጠቅላላ ጉባኤ ማንም ሊጠራው አይችልም፡፡ በዛ ላይ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ላይ ምርጫ ቦርድ ዕገዳ ጥሏል፡፡ ያ ዕገዳ ሳይነሳ ማፍረስም ሆነ ማዋሃድ አይቻ ልም፡፡
አዲስ ዘመን፡– በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ልደቱ ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2011