Source: https://mereja.com/amharic/v2/121331
አዲስ ዘመን

ሰውየው ሲያዩዋቸው ሩህሩህና ለስላሳ ይመስላሉ፡፡ መስሪያ ቤቶች በሚያባክኑት ገንዘብና የአሰራርና የሕግ ጥሰት አንጀታቸው ብግን ብሎ ሪፖርት ሲያቀርቡና ሲማጸኑ የብዙዎችን አንጀት ይበላሉ፤ አንዳንዴም ህግ ይከበር ሲሉ ኮሰተር ብለው ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ! ይሁን እንጂ ተማፅኖአቸውንም ሆነ ማስፈራሪያቸውን የሚሰማና የሚታረም ተቋምም ሆነ ኃላፊ ያለ አይመስልም፡፡
እርሳቸው ሪፖርት ሲያቀርቡ ጆሮውን የማይሰጣቸው የለም፡፡ በተለይ መገናኛ ብዙሃን በየመስሪያቤቶቹ ላይ የሚቀርቡትን የበጀት ጉድለትና ብክነት ለመስማት ሁሌም አይናቸው እንደበራና ጆሯቸው እንደተቀሰረ ነው። ተደጋጋሚ ኦዲት ግኝቶችን ሲያቀርቡ ሲሰማ መንግሥት እንደመንግሥት ቆሞ መሄዱ ሲያስገርም፤ የመንግሥት በጀት ተዝቆና ባክኖ አያልቅምን? የሚል አመለካከትን ይፈጥራል፡፡
ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፌዴራል ዋና ኦዲተር የቀረበው በፌዴራል ዋና ኦዲተር የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የ2010 ዓ.ም የፋይናንስ ህጋዊነት ኦዲትና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት እንደቀደሙት ዓመታት የሚያስደነግጥና መፍትሄ የታጣለትን ችግር ይዞ ነበር።
በጥሬ ገንዘብ ጉድለት፡- በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 810 ሺህ 060.38 ብር፣ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ 123 ሺህ 599.00 ብር፣ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ 271 ሺህ 73.28 ብር፣ በሁለት የገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች 102 ሺህ 532.99 ብር ፡፡
ውዝፍ ያልተሰበሰበ ሂሳብ፡- በብሔራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ብር 608,731,337.69፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብር 441,828,292.09፣ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ብር 322,520,418.09፣ በቀድሞው ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ብር 282,965,014.42፣ በቀድሞው መገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ብር 256,674,976.65፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ብር 250,218,048.94፣ በትምህርት ሚኒስቴር ብር 232,084,916.72፣በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ብር 169,647,495.93፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ብር 160,457,088.68፣ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ብር 153,255,211.99፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብር 108,079,052.31፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብር 114,611,493.86፣ በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ብር 111,362,647.02፣ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ብር 102,777,501.69 ያሉ ሲሆን፤ እነዚህ ያልተሰበሰቡ ውዝፍ የአገሪቱ አንጡራ ሀብቶች ከአንድ ዓመት ጀምሮ ከአስር ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ መሆናቸው፣ ከመቼ ጀምሮ በተሰብሳቢነት እንደተመዘገቡ የማይታወቁና ከእነማን እንደሚሰበሰቡ በቂ ማስረጃ ሊቀርብባቸው ያልቻሉ በመሆናቸው ለቁጥጥር እንኳ አመቺ እንዳልሆነ በሪፖርቱ በግልፅ ተቀምጧል፡፡
ዋናው ኦዲተር ከገንዘብ ጉድለቱ ባሻገር የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ ተመዝግቦ የተገኘ ሂሳብ፣ ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ ካለአግባብ የተፈፀሙ ክፍያዎች፣ በብልጫ የተከፈሉ ሂሳቦች፣ የግዢ አዋጅ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ የተፈፀሙ ግዢዎች፣ ንብረቱ ገቢ ስለመሆኑ የዕቃ ገቢ ደረሰኝ ሳይቀርብለት በወጪ የተመዘገበ ሂሳብ፣ በተሰብሳቢ ሂሳብ መመዝገብ ሲገባው በወጪ የተመዘገበ የቅድሚያ ክፍያ ሂሳብ፣ ማስረጃ ሳይኖር በወጪ የተመዘገበና ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ወጪ ሂሳብ ወዘተ…መገኘታቸው ምን ያህል የአሰራር ዝርክርክነት መኖሩን አመላክቷል። ዓመታትን የተሻገረና መታረም ያልቻለ ጉዳይ መሆኑን ስናስብ ደግሞ ከማስገረም አልፎ ያሳዝናል።
ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ በምክር ቤቱ ተገኝተው ሪፖርት ባቀረቡ ቁጥር ብዛት ያላቸው የመንግሥት ተቋማት በተደጋጋሚ በየዓመቱ የሚሰጣቸውን አስተያየት ተግባራዊ በማድረግ ከማሻሻል ይልቅ ወደባሰ ጥፋት እየገቡ መሆናቸውንና ለዚህም ዋና ምክንያቱ ተጠያቂ ያለመደረጋቸው መሆኑን ቢያስረዱም፤ የእርሳቸውን አቤቱታ ተከትሎ መንግሥት የወሰደው እዚህ ግባ የሚባል ርምጃ ባለመኖሩ በየዓመቱ የምናደምጠው እጅግ ግዙፍ የገንዘብ ብክነት መንግሥትን የተሰማው አይመስልም፡፡
እስከዛሬ ድረስ በቀረቡ የዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርቶች ተለይተው በወጡ ጉልህ ግድፈቶች በቂ የሕግ እርምጃ አለመወሰዱ ተቋማቱን በየጊዜው በችግር ውስጥ እንዲዳክሩ አስተዋፅዎ እንዳበረከተና ከስህተታቸው መማሪያ እንዳላገኙ ቢያሳይም በዚህ ሁኔታ እስከመቼ ይዘለቃል የሚለው የሁሉም ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
አዲስ ዘመን
► መረጃ ፎረም – JOIN US