Source: https://mereja.com/amharic/v2/121510

የአማራ ክልል መስተዳደር ምክር ቤት የዳግማዊ ዓጼ ምኒሊክ መታሰቢያ ሙዚዬም ማቋቋሚያ ደንብን አጸደቀ፡፡መስተዳደር ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ ላይ እንደተመለከተው ደንቡን ማውጣት ያስፈለገው ለኢትዮጵያ አንድነት ጉልህ ሚና ላበረከቱት ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ መታሰቢያ እንዲሆን በሰሜን ሸዋ ዞን አንኮበር የተቋቋመው ሙዚዬም በአጠባበቅና አያያዝ ጉድለት ለአደጋ እየተጋለጠ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ነው፡፡
የደንቡ መጽደቅ ለመስህብ ሀብቱ ተገቢ ጥበቃ በማካሄድ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታዎችን ለማስፋት ያስችላል ተብሏል፡፡በደንቡ እንደተመለከተው በክልሉ ካቢኔ የሚሾሙ ዋና እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች የሚኖሩት ይሆናል፤ ገቢውም በክልሉ የፋይናንስ ሕግ መሠረት እንደሚመራ ተጠቅሷል፡፡የሕዝቡ ታሪክ ባግባቡ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ በአካባቢው ያሉ ለሀብቱ ተቆርቋሪ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ሥራውን በባለቤትነት በማስተዳደር አጋዥ እንዲሆኑ ለማስቻል የሙዚዬሙ አማካሪ ቦርድ አባላት እንዲሆኑ በደንቡ ላይ ተገልጿል፡፡
ሙዚዬሙ በደንብ እንደገና መቋቋሙ በየቦታው ያሉ ቅርሶችን በማሰባሰብ፣ ተዘርፈውና በሌላም አጋጣሚ ተወስደው በውጭ አገሮች የሚገኙ ቅርሶችን ሕግን መሠረት በማድረግ ለማስመለስ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት እንደሚያስችልም ታውቋል፡፡
ምንጭ፡- የርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት
► መረጃ ፎረም – JOIN US
