June 1, 2019

Source: https://mereja.com/amharic/v2/121513

“ኢዴፓ ፈርሷል የተባለው በውሸት ነው” – አቶ ልደቱ አያሌው

“ኢዴፓ መጋቢት 1 ቀን በጠራነው ጉባኤ ፈርሷል” – ዶ/ር ጫኔ ከበደ – የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር

(ኢ.ፕ.ድ) – ኢዴፓ ፈርሷል የተባለው ውሸት መሆኑንና ለኢዴፓ ህጋዊ ዕውቅና የሚሰጠው ምርጫ ቦርድም ኢዴፓ አለመፍረሱን እንደገለጸ አቶ ልደቱ አያሌው ተናገሩ፡፡

አቶ ልደቱ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት በኢዴፓ መፍረስ አለመፍረስ ላይ ምንም ክርክር እንደሌለና ለኢዴፓ ህጋዊ ዕውቅና የሚሰጠው ምርጫ ቦርድም ኢዴፓ አለመፍረሱን እንደገለፀ ተናግረዋል፡፡

ከምርጫ ቦርዱ ምላሽ በኋላ የኛ መልስ አያስፈልግም ያሉት አቶ ልደቱ ፈርሷል የተባለው በውሸት ነው፤ ሊያፈርሰው የሚችለው አካል ጭራሽ አልተሰበሰበም ብለዋል፡፡

ሊያፈርሰው የሚችለውን አካል ምርጫ ቦርድ ዕገዳ ጥሎበታል፤ ያ ዕገዳ ባልተነሳበት ሁኔታ ከሌላ ጋር መዋሃድም ውሳኔ መስጠት አይቻ ልም፤ ዝም ብሎ ወሬ ነበር፤ ወሬ መሆኑም በሂደት ታይቷልም ነው ያሉት፡፡

እንደ አቶ ልደቱ ገለፃ በዚህ ጉዳይ ላይ የተካሄደ ክርክርም ይሁን ክስም አልነበረም፡፡

መጋቢት 1 ጉባኤ መካሄዱ እና መፍረሱም ሲጠቀስ እንደነበርና ይህ ምን ያህል እውነት እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ልደቱ በመተዳደሪያ ደንባችን መሰረት ጠቅላላ ጉባኤውን የሚጠራው በአንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ13 ነጥብ 4 መሰረት ብሔራዊ ምክር ቤቱ ነው ያሉ ሲሆን ብሔራዊ ምክር ቤቱ ብዙሃኑ ያለው ደግሞ እኛ ጋር ነው፤ እኛ ያልጠራነው ጠቅላላ ጉባኤ ማንም ሊጠራው አይችልም ነው ያሉት፡፡

ብሔራዊ ምክር ቤቱ ላይ ምርጫ ቦርድ ዕገዳ እንደጣለ የጠቀሱት አቶ ልደቱ ያ ዕገዳ ሳይነሳ ማፍረስም ሆነ ማዋሃድ አይቻልም ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከሳምንት በፊት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዝዳንት የአሁኑ ኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ “ኢዴፓ መጋቢት 1 ቀን በጠራነው ጉባኤ ፈርሷል” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል። (ሙሉ ቃለ ምልልሱን በዚህ ሊንክ ያገኛሉ https://www.press.et/Ama/?p=11334#)

እንደ ዶክተር ጫኔ ገለጻም፤ ኢዴፓ ከመጋቢት 1 በኋላ ያሉትን ንብረቶች የሂሳብ ሪፖርቶችን አጣርቶ ለአዲሱ ፓርቲ ሀብት ሆነው እንዲዘዋወሩ ወስኖ ያንንም የሚያደርግ ሦስት አባላት ያሉት ኮሚቴ መርጦ ወደ አዲሱ እንዲዘዋወር ወስ ኗል። ይህን ሃሳብ ያቀረበው ደግሞ ራሱ ጉባኤው ነው።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ