June 1, 2019
Source: https://haratewahido.wordpress.com
https://haratewahido.files.wordpress.com/2019/06/his-grace-abune-yacob-archbishop-of-all-african-diosces0
ሐራ ዘተዋሕዶ

- እስከ ቀጣዩ የጥቅምት ምልአተ ጉባኤ ወደ ደቡብ አፍሪቃ እንዳይሔዱ አገዳቸው፤
- አንድም የሚጠቀስ በጎ ሥራ ያጣላቸው አጣሪ ኮሚቴ፣ እንዲዛወሩ ሐሳብ አቀረበ፤
- ሊቀ ጳጳሱ የሪፖርቱን ግኝቶች በመካዳቸው ለተጨማሪ ማጣራት አባቶች ተመደቡ፤
- ማጣራት ሲካሔድባቸው የአኹኑ 3ኛ ጊዜ በመኾኑ፣ ውሳኔው ምእመናንን አስቆጣ፤
- ሲኖዶሱ፥ የሊቀ ጳጳሱን ያህል ለእኛ ደኅንነት አልተጨነቀልንም፤ በማለት አማረሩ፤
***
- መዋቅር ፈርሷል፤ አስተዳዳሪዎች፣ ሠራተኞች፣ አገልጋዮችና መምህራን የሉም፤
- በሊቀ ጳጳሱ ብቻና በዘፈቀደ ነው እየተሠራ ያለው፤ ችግሮችም በወቅቱ አይፈቱም፤
- መደበኛም ይኹን የዕቅበተ እምነት ትምህርት ባለመኖሩ፣ ብዙዎችን እያጣን ነው፤
- ሲኖዶሳዊ አንድነቱ ቢመለስም፣ በሊቀ ጳጳሱ ጥላቻ የማገናኘቱ ሥራ አልተሠራም፤
- የተመደቡት 2 ብፁዓን አባቶች፥ ሕዝቡን ያገናኛሉ፤ደ/አፍሪቃውያኑን ያስተምራሉ፤
***
በደቡብ አፍሪቃ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር መፈራረስ፣ ለምእመናን መከፋፈልና ነፍስ መጥፋት፣ ለሀብት ብክነትና ምዝበራ ተጠያቂ የኾኑት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አባ ያዕቆብ፣ እስከ መጪው ጥቅምት ምልአተ ጉባኤ ወደ ሀገረ ስብከቱ እንዳይሔዱ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ አገደ፡፡
እገዳው በሊቀ ጳጳሱ ላይ የተላለፈው፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በዛሬ ቅዳሜ፣ ግንቦት 24 ቀን የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ የቀትር በፊት ውሎው፣ በአጣሪ ኮሚቴው በቀረበለት ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኋላ ነው፡፡
ከአራት ዓመት በፊት ከሀገረ ስብከቱ ታግደው የተመለሱት ሊቀ ጳጳሱ፣ የቀደመ ጥፋታቸውን ከማረም ይልቅ ብልሽታቸው እየተባባሰ መሔዱንና ይቀጥሉ ቢባል፥ የምእመናኑ መከፋፈል፤ የሰርጎ ገቦች ጣልቃ ገብነት እየከፋ የሚሔድ ከመኾኑም በላይ በደቡብ አፍሪካ የቤተ ክርስቲያን ሰላምና የምእመናን አንድነት አስከፊ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ሪፖርቱ በውሳኔ ሐሳብ ያቀረበውን ማሳሰቢያ በመቀበል፣ እስከ መጪው ጥቅምት ምልአተ ጉባኤ እንዳይሔዱና በአገር ቤት እንዲቆዩ ቅዱስ ሲኖዶሱ አግዷቸዋል፡፡
ሊቀ ጳጳሱ፣ ለምልአተ ጉባኤው አባላት ባሠራጩትና በንባብ ባሰሙት ምላሽ፣ የሪፖርቱን ግኝቶች በሙሉ አስተባብለዋል፤ በቃል በሰጡትም ማብራሪያ፣ ቀደም ሲል በድረ ገጽ ከተብጠለጠሉበት ያልተለየ ሪፖርት እንደኾነ በመጥቀስ አጣጥለዋል፤ “በጎ ሥራዬ አልታየልኝም፤” በማለት አከናወንኩ ያሏቸውን ተግባራት ዘርዝረዋል፤ “በኀጢዓት ከማንም አልበልጥም፤ በጽድቅም ከማንም አልበልጥም” በማለት ጉዳያቸው ከታየላቸው አባቶች ተለይተው፣ ከሀገረ ስብከቱ መዛወር እንደማይፈልጉ መልእክት ያስተላለፉበትን የሚመስል አስተያየት አክለዋል፡፡
በስብሰባው ሥነ ሥርዓት መሠረት፣ የልኡካኑን ሪፖርትና የሊቀ ጳጳሱን አስተያየት በቅደም ተከተል ያደመጠው ጉባኤው፣ ብፁዕ አባ ያዕቆብ፣ በውጭ እንዲቆዩ በማድረግ ሲወያይ፣ የተለያዩ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ በአሉታዊ ነገሮች ላይ ያተኮረና የተሠሩ ሥራዎችን ያላካተተ ሪፖርት ነው፤ በሚል ሊቀ ጳጳሱን ደግፈው በረጅሙ የተናገሩ እንዳሉ ኹሉ፣ “ሀገረ ስብከቱ በኹሉም ነገር ተጎድቷል፤ በአግባቡ አልተዋቀረም፤ ሕጉ ተጠብቆ ሳይኾን በዘፈቀደና በሊቀ ጳጳሱ ውሳኔ ብቻ ነው እየተሠራ ያለው፤ ምንም ነገር የለም፤” በማለት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲሰሙት የቆዩትን እውነታ ማንጸባረቁን የተናገሩ ብፁዓን አባቶችም አሉ፡፡
ሊቀ ጳጳሱ፣ የሀገረ ስብከትና የአድባራት ሓላፊዎችን ምደባ በማሰናከላቸው፣ ካህናትንና መምህራንን ቀጥረው ለማሠራት አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያን ምእመናን የተሟላ አገልግሎት እንደማያገኙ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በአግባቡ እንደማይማሩ፣ከኹሉም በላይ ብፁዕ አባ ያዕቆብ ገንዘብ ካልተከፈላቸው እንደማይጎበኟቸው፣ ከጥቂቶች ጋራ በጥቅም ከመቆራኘት በቀር ለብዙኀኑ ደቡብ አፍሪቃውያን ትኩረት እንደነፈጓቸው፣ በዚህም ሳቢያ እየኮበለሉ የፕሮቴስታንትን ቸርች የሚያባዙና በቤታቸው መቅረትን የመረጡ እንደተበራከቱ፣ ሪፖርቱ በስፋት ያተተው በእጅጉ እንደነካቸው ገልጸዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ፥ በጠንካራ፣ ትጉህና ኹሉንም በእኩል ዓይን በሚያይ መንፈሳዊ አባት ቢመራ፣ ምእመናኑ ለቤተ ክርስቲያናቸው ያላቸው ፍቅርና ትብብር እጅግ የሚያስቀና እንደኾነና ከራሱ አልፎ በአገር ውስጥ ላለችው ቤተ ክርስቲያን እገዛ ሊያደርግ የሚችል ሀብትና ሕዝብ ያለበት እንደኾነ የተገለጸውም እንዳስቆጫቸው አልሸሸጉም፡፡
በዐቢይ ጾም እና በጾመ ፍልሰታ መምህራን ከአዲስ አበባ መጋበዛቸውን ብቻ በመልካምነት ያነሣው ልኡኩ፣ እርሱም በአመራረጥ ረገድ ውስንነት ያለበት በመኾኑ፣ ለሊቀ ጳጳሱ አንድም እንኳ ጥሩ ነገር ሊጠቅስላቸው ተቸግሮ ታይቷል፡፡ በመኾኑም፣ ሊቀ ጳጳሱ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረው በምትኩ፣ ምእመናኑን በአንድነት ለመምራት ችሎታውና ትጋቱ ያለው መንፈሳዊ አባት እንዲመደብ ቅዱስ ሲኖዶሱን ጠይቋል፡፡ ሀገረ ስብከቱንና አብያተ ክርስቲያናቱን ከማዋቀርና ከማደራጀት፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በአግባቡ ከማስጨበጥና በተለይም የዕቅበተ እምነት እንቅስቃሴውን ከማጠናከር፣ የሕገ ወጥ ቡድኖችን ሁከት በመግታት አኳያ ሊሠሩ የሚገባቸውን ተግባራትንም ጠቁሟል፡፡
ከሪፖርቱና ውይይቱ በመነሣት፣ ሊቀ ጳጳሱ በሀገረ ስብከቱ መቀጠል እንደሌለባቸው አጠቃላይ መግባባቱ አለ፤ የሚበዙትም አባቶች አስተያየት፣ “ከጅምሩ ያጠፉት ነገር ስላለ የሚያስቀጥላቸው አይደለም፤ መዳን አይችሉም፤” የሚል ነው፡፡ ኾኖም፣ አሉታዊው ነገር አመዝኗል፤ አንድ አቅጣጫ ብቻ ነው፤ እዚያው ተመልሰው እየሠሩ ይጠየቁ፤ ጉዳያቸውን ይከታተሉ፤ በሚሉ አባቶች ግፊት ውሳኔው ለጊዜው ወደ እግድ ተለውጧል፡፡ እስከ መጪው ጥቅምት ምልአተ ጉባኤ ወደ ሀገረ ስብከቱ እንዳይሔዱ የታገዱ ሲኾን፣ በጽሑፍና በቃል ከሰጡት ምላሽና ማብራሪያ አኳያ፣ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ተጉዘው ተጨማሪ ማጣራት እንዲያደርጉ፣ ኹለት ብፁዓን አባቶች በምልአተ ጉባኤው ተመድበዋል፡፡ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የተመደቡ ሲኾን፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ባልደረባው ቀሲስ በላይ ጸጋዬ በጸሐፊነት እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ፣ በጉጉት ሲጠባበቁ የቆዩትን የሀገረ ስብከቱን ምእመናን አላስደሰተም፤ በእጅጉ አስቆጥቷቸዋል፤ ብፁዕ አባ ያዕቆብ አይኹኑ እንጂ አንድ አድርጎ በፍቅር የሚመራንንና የሚባርከንን ሌላ አባት እንቀበላለን፤ በማለት በምልአተ ጉባኤው ላይ ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ የአኹኑን ጨምሮ ለኹለት ጊዜያት የተደረጉ ማጣራቶች፣ ሊቀ ጳጳሱ ለደቡብ አፍሪቃ ሀገረ ስብከት አባት መኾን እንደማይችሉ እያረጋገጡ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ይጣራ ማለት ከቧልት እንደማይተናነስ አስረድተዋል፡፡
ሊቀ ጳጳሱ፣ ለጊዜውም ቢኾን በእግድ መቆየታቸው፣ የበለጠ ሊጎዳቸው እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡ ጉልበተኞችን እየቀጠሩ የተቃወሟቸውን በማስደብደብ ካላቸው ልምድ አኳያ፣ በተለይ ስማቸው በሪፖርቱ ለተጠቀሱት ካህናትና ምእመናን ደኅንነት አስጊ እንደኾነ አስታውቀዋል፡፡ “ሲኖዶሱ ለሊቀ ጳጳሱ ቅሬታ የተጨነቀውን ያህል ለእኛም ሕይወት ማሰብ ነበረበት፤” ያሉት ምእመናኑ፣ ቢያንስ የሀገረ ስብከቱንና የአብያተ ክርስቲያናቱን ሒሳብ እንዳያንቀሳቅሱ ጨምሮ ሊያግዳቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
የተመደቡት ብፁዓን አባቶች፣ በብፁዕ አባ ያዕቆብ ጥላቻ፣ እንዲርቁ የተደረጉትንና ቀደም ሲል በውጭው ሲኖዶስ ሥር የነበሩትን ካህናትና ምእመናን ጨምሮ ሕዝብን የማገናኘት ሓላፊነት ተሰጥቷቸዋል፤ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ረስታናለች፤ ልጆቻችንንም ኾነ እኛን የሚያስተምረን የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንንና ኢትዮጵያን እንወዳታለን፣ አባቶቻችን ግን ረሱን፤” እያሉ በአገልጋይና መምህራን ዕጦት የሚያማርሩ ደቡ አፍሪቃውያንን አግኝተው ተስፋቸውን ያጠናክራሉ፤ ተብሏል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶሱ አጀንዳ ተ.ቁ(9) ላይ እየተካሔደ ያለው፣ ማጣራት የተካሔደባቸው አህጉረ ስብከት ሪፖርት ውይይት፣ በመጪው ሰኞ፣ የካፋ ሀገረ ስብከትንና የኢየሩሳሌም ገዳማትን በመመልከት ይቀጥላል፡፡
