
የሱዳን ወታደራዊ ኃይል እስካሁን ከተቃዋሚዎች ጋር የተደረጉ ስምምነቶችን ወደ ጎን በመተው በዘጠኝ ወር ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አቀረበ።
ይህ ጥሪ የተደረገው ወታደራዊ ኃይሉ በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ እየወሰደ ያለው ኃይል የተቀላቀለበት እርምጃ ከዓለም አቀፍ መንግሥታት ተቃውሞ ከደረሰበት በኋላ ነው። በሱዳን ካርቱም ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የተጋጩት ሰልፈኞች ላይ በተወሰደ እርምጃ እስካሁን 30 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
አሜሪካ ድርጊቱን “ጨካኝ እርምጃ” ስትል ኮንናዋለች።
ወታደሩ እርምጃውን የወሰደው ተቃዋሚዎች ጋር ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመሄድ የሶስት አመት የሽግግር ጊዜ ከተስማማ በኋላ ነው።
• አሜሪካ የቪዛ አመልካቾችን የማህበራዊ ሚዲያ ዝርዝር ልትጠይቅ ነው
• የቦይንግ 737 ማክስ ደህንነት ስለ ማሻሻል ያለው እሰጣ ገባ ቀጥሏል
ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሺር ከስልጣን ከተወገዱ ጀምሮ ሀገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘው የወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤቱ ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር በመደራደር አዲስ አስተዳደር በሚመሰረትበት ጉዳይ ላይ መግገባባት ላይ ደርሰው ነበር።
ነገር ግን የሽግግር መንግሥቱ መሪ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡራሀን ለሀገሪቱ ቴሌቪዥን በላኩት መግለጫ ” ከተቃዋሚዎች ጋር የምናደርገውን ድርድርም ሆነ እስካሁን ስምምነት የደረስንባቸውን አቋርጠናል” ብለዋል።
አክለውም በዘጠን ወራት ውስጥ “አለም አቀፍና አህጉራዊ” ታዛቢዎች በተገኙበት ምርጫ ይካሄዳል ብለዋል።
ይህ መግለጫ የመጣው የሲቪል አስተዳደር እንዲመሰረት የሚደራደሩት ተቃዋሚዎች ሀገሪቱን መምራት ያለበት ሲቪሉ ነው በማለት የሚደረገውን ድርድር በማቋረጥ ሀገር አቀፍ አድማ ከጠሩ በኋላ ነው።