June 4, 2019

Source: https://haratewahido.wordpress.com

61862933_2277933202271688_7119126344314650624_n

***

በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትን በአድማና በፀብ እያወኩ ሊቀ ጳጳሱንና አባቶችን በመደብደብ ጉዳት ያደረሱ መነኰሳት፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲቀጡ ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፤ በዚኹ ሳቢያ ተፈጥረዋል የተባሉ አጠቃላይ ማኅበረሰባዊ ቅራኔዎችንም በማስወገድ የሚያስተራርቁና ቀኖናዊ ውሳኔውን የሚያስፈጽሙ ሦስት ብፁዓን አባቶችን መደበ፡፡

ምልአተ ጉባኤው በዛሬ ማክሰኞ፣ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. የቀትር በፊት ውሳኔው፣ ባለፈው ታኅሣሥ 9 ቀን ቄሰ ገበዝ ለመምረጥ በዴር ሡልጣን ገዳም በተደረገው የማኅበሩ አጠቃላይ ስብሰባ ላይ፣ እኛ ያልነው ካልኾነ በማለት ከመነኰስ አባት በማይጠበቅ የሥነ ምግባር ጉድለት፣ ሁከትና ፀብ በማነሣሣትና በመፈጸም እንዲሁም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በመናቅና በማቃለል የተሳተፉት ሦስት መነኰሳት፥ በተመደቡት ብፁዓን አባቶች ቀኖና እንዲሰጣቸው ወስኗል፡፡

ድርጊቱን የፈጸሙት መነኰሳት፥ አባ ተስፋ ማርያም ይኅደጎ፣ አባ ገብረ እግዚአብሔር ተስፋይ እና አባ ወልደ ሩፋኤል ገብረ ጻድቅ የሚባሉ ሲኾኑ፣ ሦስቱም በገዳማቱ ማኅበር አጠቃላይ ስብሰባ ውሳኔ፣ ካለፈው ታኅሣሥ 17 ቀን ጀምሮ ከአገልግሎትና ከአንድነት ተሰናብተው ቆይተዋል፡፡ መነኰሳቱ በበኩላቸው፣ ርምጃውን ተቃውመው ለቅዱስ ፓትርያርኩ በጻፉት አቤቱታ፣ በውጭ ፖሊቲከኞች ጣልቃ ገብነትና በወገንተኝነት የተላለፈብን ውሳኔ ነው፤ በማለት ድርጊቱን መፈጸማቸውን ክደዋል፤ በማኅበሩ የተፈጠረው መከፋፈል ወደ ሕዝብ እንደወረደና ይህም እርስ በርስ እንዳያበጣብጥ ስለሚያሰጋ በቅዱስነታቸውና በቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት ተሰጥቶት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የገዳሙን አስተዳደራዊ ርምጃና የመነኰሳቱን አቤቱታ የሚመረምር የቋሚ ሲኖዶስ ልኡክ፣ በጥር ወር መጀመሪያ በስፍራው ተገኝቶ ያደረጉትን የማጣራትና ለማኅበሩ አንድነትና አገልግሎት መቃናት የሚበጅ አጠቃላይ መፍትሔ የሚዳስስ ሪፖርት፣ ትላንት ከቀትር በፊት ለምልአተ ጉባኤው አቅርበዋል፡፡

his-grace-abune-enbakom-bishop-of-the-holy-land-jerusalem

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ረዳት ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊ መልአከ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎሬዎስ በአባልነት የሚገኙበት ይኸው የቋሚ ሲኖዶሱ ልኡክ፣ በስም ተጠቃሾቹ መነኰሳት ድርጊቱን ስለ መፈጸማቸው በማጣራቱ አረጋግጧል፤ እንደ ጥፋታቸው መጠንም ከጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ ሊወሰድ የሚገባውን ቀኖናዊ ቅጣት አስቀምጧል፤ ኾኖም ጉዳዩ ወደ አስራኤል ፍ/ቤት በማምራቱና አለመግባባቱ ወደ ኢትዮጵያዊው ማኅበረሰብ ዘልቆ የእርስ በርስ መከፋፈል በመፍጠሩ፣ ችግሩ በዕርቅ ሊፈታ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡

ከሪፖርቱ በኋላ፣ መነኰሳቱ ወደ ኢትዮጵያ ተጠርተው ቀኖና ይሰጣቸው፤ እዚኹ ቀኖናቸውን ይፈጽሙ፤ በሚሉና ዕርቁ ይቅደም፤ መነኰሳቱም ቀኖናቸውን እዚያው ፈጽመው ወደ ገዳሙ ይመለሱ፤ በሚሉ አባቶች መካከል መካረር የታየበትና አንድ የጉባኤው አባል እንደተቹት፣ “በጎሠኝነት የመደጋገፍ ዝንባሌ” የተስተዋለበት ክርክር ተካሒዷል፤ ትላንት ከቀትር በኋላ የነበረው የስብሰባው ጊዜ ባለመብቃቱም አድሯል፡፡

ዛሬ ከቀትር በፊት፣ ምልአተ ጉባኤው በቀጠለው ውይይት፣ መነኰሳቱ በፈጸሙት ድርጊት፥ ሥርዓተ ገዳሙን እንደጣሱና ሊቀ ጳጳሱን ብፁዕ አቡነ ዕንባቆምን እንደበደሉ መግባባት ተደርሶ ቀኖና እንዲሰጣቸው ወስኗል፤ ይህን ቀኖናዊ ውሳኔ ከማስፈጸም ጋራ ማኅበሩንና ሕዝቡን በማነጋገር አንድ እንዲያደርጉና ዕርቀ ሰላም እንዲያወርዱ ሦስት ብፁዓን አባቶችን ማለትም የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን፤ የአሶሳ፣ የምዕራብ ወለጋና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤልን፤ የምሥራቅ አውስትራልያ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን መድቧል፡፡


ከዚህ ቀደም ሲል ምልአተ ጉባኤው፣ በካፋ ሀገረ ስብከት፣ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ሕዝኤል እንዲነሡ ማኅበረ ማእመናን ሲያቀርቡት ከቆዩት ጥያቄ ጋራ በተያያዘ፣ የአጣሪ ልኡካኑን ሪፖርት በመስማት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ እና ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ዋናው ችግር በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሓላፊዎች የተፈጠረ መኾኑን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡በመኾኑም፣ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በቦታቸው ቆይተው፣ ካለው ተጨባጭ ኹኔታ አኳያ፣ ጽ/ቤቱን በጠንካራ ሥራ አስኪያጅና ሌሎች ሓላፊዎች ለማጠናከር እንዲሁም የአሠራር ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚያስችሉ ርምጃዎች እንዲወሰዱ ውሳኔና ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

በዚኹ ወደ ተ.ቁ(10) አጀንዳው የተሸጋገረው ምልአተ ጉባኤው፣ በጦርነትና በአክራሪ ጎሠኛ ኀይሎች የተቃጠሉ፣ በአገልጋይና አቅም ማጣት የተዘጉና በግንባታ ላይ ያሉ አብያተ ክርስቲያንና የአብነት ት/ቤቶች፤ የተፈናቀሉ ምእመናን ድጋፍና ድጎማ በተመለከተ አህጉረ ስብከቱ ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች ተመልክቷል፤ የድጋፍና ድጎማ ጥያቄአቸውን አጣርቶ ለቀትር በኋላ ክፍለ ጊዜ የሚያቀርብ ኮሚቴም ሠይሟል፡፡

የርዳታ ጥያቄውን ያቀረቡት፡- በባድመ ጦርነት የፈራረሱ 11 የዛል አንበሳ አብያተ ክርስቲያን የሚገኙበት የዓዲ ግራት ሀገረ ስብከት፣ በጎሠኞች ጥቃት የተፈናቀሉና የተጎዱ አብያተ ክርስቲያንና ምእመናን የሚገኙባቸው የቤንሻንጉል ጉምዝ፣ የምሥራቅ ወለጋ፣ የሰሜን ሸዋ እና የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ አህጉረ ስብከት ናቸው፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በግንባታ ላይ ለሚገኘው የመርጡለ ማርያም ካቴድራል፣ የታእካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም ሕንፃ እድሳት፣ ለደብረ ሊባኖስ ገዳም የአባቶች ማረፊያ፣ ለባሌ እና ኢሉ አባቦር አህጉረ ስብከት የአብነት መምህራንና ተማሪዎች ደግሞ የድጎማ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ቀጥሎ በተመለከታቸው አጀንዳ ተ.ቁ(11)፥ በውጭው ዓለም በነበረው ሲኖዶስ፣ በዋሽንግተን ዲሲ ስለሚገኘው የአራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ማረፊያ ቤት ሽያጭ ጉዳይና በአጀንዳ ተ.ቁ(12)፥ በአዲስ አበባ እና በአሥመራ፣ የኹለቱ አኀት አብያተ ክርስቲያን የቤቶች ይመልስልኝ ጥያቄዎች ተወያይቶ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

የቅዱስነታቸው ማረፊያ የነበረው ቤት፣ ቀደም ሲል በውጭው ሲኖዶሱ ውሳኔ ተሽጦ የተገኘው 460ሺሕ ያህል ዶላር በባንክ እንደተቀመጠ ተገልጿል፡፡ በተካበተው በዚኹ ገንዘብ፣ ማረፊያ ቤቱን፥ የማሠልጠኛ፣ የስብሰባ፣ የአበው ማረፊያ በአጠቃላይ ለቤተ ክርስቲያን መገለጫ የኾነ ሥራ እንዲሠራበት ነው የወሰነው፡፡ ይህንም እንዲያስፈጽሙ፣ ለአራት የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት(ለኒው ዮርኩ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ለዋሽንግተን ሲያትሉ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ለዋሽንግተን ዲሲው ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል እና ለሰሜን ካሊፎርኒያና አካባቢው ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ) ሓላፊነት የሰጠ ሲኾን፤ የሪል ስቴት እና የሕግ ባለሞያዎችን ጨምረው ሥራውን እንዲያከናውኑ አዟቸዋል፡፡

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ የነበሩትና ትውልደ ኤርትራዊው ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ በአዲስ አበባ ያሠሩትን ቤት፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በኪራይ እየተጠቀመበት ሲኾን፣ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለስላት ጠይቃለች፤ በተመሳሳይ አኳኋን፣ በአሥመራ ላይ ደግሞ፣ የደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ገዳም ቤት ያለው በመኾኑ፣ እንዲመለስ በእኛ በኩል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ኹለቱም በጥናት መመለስ ይኖርበታል፤ ያለው ምልአተ ጉባኤው፣ በቋሚ ሲኖዶስ አጥኚ ቡድን ተዋቅሮ ውጤቱን ለቀጣዩ የጥቅምት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡