June 4, 2019
Source: https://www.zehabesha.com/amharic/archives/95598
ላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
እንደምናቀውና በቅርቡም ሎስ አንጀለስ ታይምስ እንደዘገበው ሶሶት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተሰደው መኝታቸው ጪንጫ መሬት ትራሳቸው ድንጋይ ሆኗል*፡፡ የእነዚህ ስደተኛ በጎች እረኛ መሆን የሚገባቸው የክርስትናና የእስልምና መሪዎች ግን አንድም በግ እንዳልጠፋባቸው ሁሉ ሆዳቸውን ሲሞሉ ውለው ከአየር ፍራሽ ተንፈላሶ ማደሩን ቀጥለውበታል፡፡ ምዕመናን በገጀራ ሲከተፉ፣ በጦር ሲወጉ፣ በባሩድ ሲረግፉና መጤ እየተባሉ በላያቸው ቤታቸው ሲፈርስ አፋቸውን በምዕመናን አስራት ጠቅጥቀው ጪጭ ብለዋል፡፡
መጽሐፉ እስተንፋስ ያለው ሁሉ እንዲተነፍስ ያዝዛል፡፡ ዳሩ ግን ካህናት ይህንን የመጽሐፍ ቃል በመሻር በጎንደር አንድ ሚሎዮን የሚጠጋ ሕዝብ ሜዳ ሲያደር፣ በመተከል ሲታረድ፣ በሸዋ ሕዝብ በገጀራ ሲቀላና ቤት በገላው ሲፈርስ፣ በጌዲዮ ሕዝቡ ስደተኛ ሆኖ በርሃብና በበሽታ ሊያልቅ ካህናት የምዕመራንን አስራት እየጠቀጠቁ ያላዩ ያልሰሙ መስለው ጪጭ ብለዋል፡፡
ሰይጣን እንደ እግዚአብሔር በአካል ባይታይም በጭራቅነቱ፣ በውሸታምነቱ፣ በከሐዲነቱ፣ በአታላይነቱ፣ በሌባነቱ፣ በስግብግብነቱ፣ በእስስትነቱ፣ በእባብነቱና በክብርየለሽነቱ ይታወቃል፡፡ እነዚህ የሰይጣን ባህሪያት በባዕዳን ከወንበር የተጎለቱትን ባንዳ ገዥዎች ይገልጧቸዋል፡፡ ካህናት በተለይም አቡኖችና አቡኖችን እንደ መጋዣ የተሸከሙት ጳጳሳት ለዚቺ በጉንፋን ትተዋት ለሚሄዷት ዓለም፣ ለገንዘብና ለስልጣን ሳስተው አምላካቸውንና አገራቸውን ክደው የምዕመናን ሰቆቃ ችላ ሲሉ፤ የባንዳዎች ተላላኪ ሆነው የሕዝብን ልሳን ሲዘጉ ኖረዋል፤ አሁንም ቀጥለዋል
ኢትዮጵያ ሆይ! እነዚህ ጳጳሳት ልጆችሽ ሲታረዱ፣ ሲገረፉ፣ ሲታሰሩ፣ ሲሰደዱና ሲራቡ አብረዋቸው ቆመው አያውቁም፡፡ እነዚህ ቆብ ደፊ፣ ሸማ ጠምጣሚ፣ ዘንግ ሰባቂ፣ ጸናጽል አፋጪና ከበሮ ደላቂ ካህናት ከፎቃቸውና ከሉመዚናቸው እየወጡ የቁርጥ መቁረጫ መስቀላቸውን አንጠልጥለው የልጆችሽን ጆሮ እየጠባ ሲያሳስርና ሲያስገርፍ የኖረ ፓስተር ተከታዮች ሆነው በእርሱ አገዛዝ የሚረግፉትን ምዕመናን ረስተዋል፡፡ አንቺም ይህን በሰይጣንና በሰይጣን ተላላኪዎች የሚፈጸም ከራስ ዳሽን የረዘመ ግፍ ችለሽ ተቀምጠሻል፡፡ እባክሽ እማማ እነዚህን የሰይጣን ተላላኪ ካህናት “ልጆቼ ሲገደሉ አትግደል አላላችሁም፤ ሲገረፉ አትግረፍ አላላችሁም፤ ሲራቡ አላበላችሁም! ሲሸጡኝ አልከለከላችሁም” ብለሽ ደጀ ሰላም እንደ ገባ ውሻ አብከንክነሽ አባሪያቸው፡፡
ኢትዮጵያ ሆይ! እግዚአብሔር ለልጆችሽ ክፉና ደጉን እንዲለዩበት አእምሮ፣ ሃይማኖትና ጥበብ ከዓለም በፊት ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ቅዱሱ መጽሐፍም ነጣቂዎችንና ተኩላዎችን ከፍሪያቸው ታውቃላችሁ ሲልም አስተምሯቸው ነበር፡፡ ምነዋ ዛሬ የተማሩት ልጆችሽ የተማሩትን ረስተው ካህናትን በስራቸው ከፍሪያቸው መለየት አቃታቸው? በየትኛው የቅድስና ሥራቸው የነፍሰ-ገዳይ ተላላኪ አቡንና ጳጳሳትን ብፁዓንና ቅዱሳን እያሉ ጠሯቸው? እባክሽን ኢትዮጵያ ልጆችሽ ቆብ የደፋውን ተላላኪ ካድሬ አባ እያሉ እንዳይጠሩ፤ መስቀል የጨበጠውን የሰይጣን ተከታይ ይፍቱኝ እንዳይሉ፤ ካባ የደረበውን ከርሳም አቡንና ጳጳስ ብፁዕና ቅዱስ እያሉ ከመለኮት እንዳይጣሉ ምከሪያቸው!
ኢትዮጵያ ሆይ! እንደ ዛሬው በባዕዳን ሴራ የደም አበላ ስትሆኝ ልጆችሽ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል እንደ እንደተሰውልሽ ታስታውሻለሽ! ፋሽሽት ገብቶ ሲያምስሽ መላከ ብርሃን አድማሱና አባ ገብረየሱስ ከፋኖች ጋር እንደተዋጉልሽ ታውቂያለሽ! ምነዋ ዛሬ በስንት ለጋ ልጆች ሰማእታት ተንበሽብሸሽ የካህን ሰማእት መካን ሆንሽ? ምነዋ ጅብ ሲበላ ጅብ ተከትለው የፍታትና የተዝካር ልፋጭ በሚጎትቱ የካህን ውሾች ተሞላሽ?
ኢትዮጵያ ሆይ! የባዕዳን ጉዳይ አስፈፃሚ ባንዳዎች እየገዙሽና ባንዳዎችን እሹሩሩ የሚሉ ጳጳሳት እየመጠመጡሽ ምን ያህል ጊዜ ትኖሪያለሽ? ምዕመናን ልጆችሽን ድንጋይ እያንተራስሽና ጳጳሳትን በትንቡክ ፍራሽ እያስተኛሽስ ስንት ዘመን ትቀጥያለሽ?
ኢትዮጵያ ሆይ! ልጆችሽን ለእባብ ተሚገብሩ ጳጳሳት እንዲገላግልሽ እጆችሽን ዛሬም ወደ ሰማይ ትዘረጊያለሽ!
ሰኔ ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.
*Ethnic violence in Ethiopia has forced nearly 3 million people from their homes https://www.latimes.com/world/la-fg-ethiopia-ethnic-violence-millions-displaced-20190530-story.html