ሐራ ዘተዋሕዶ
June 4, 2019

- የባሌና የኢሉባቦር አህጉረ ስብከት የአብነት መምህራንና ተማሪዎች 400ሺሕ ድጎማ ቋሚ በጀት ነው፤
- ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ: የቅርስ ጥበቃና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ የበላይ ሓላፊነት ተመደቡ፤
- በደቡብ ትግራይ -ማይጨው እና ደቡባዊ ምሥራቅ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንደ ኾኑ ይቀጥላሉ፤
- ምልኣተ ጉባኤው፣ በ4ኛው ዙር የሕዝብና ቤት ቆጠራ አቋም ቅድመ ዝግጅት መነጋገር ጀምሯል፤
***
በአክራሪ ጎሠኞች ጥቃትና በእርስ በርስ ግጭት ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ምእመናንና ለተጎዱ አብያተ ክርስቲያን ርዳታ እንዲሁም ለአብነት ት/ቤቶችና ለገዳማት ድጎማ የሚውል የ17.9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፡፡
የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው፣ በዛሬ ማክሰኞ፣ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. የቀትር በፊት ስብሰባው፣ ከየአህጉረ ስብከቱ የቀረቡ የርዳታ እና ድጎማ ጥያቄዎችን አድምጦ፣ የጉዳት መጠኑንና የሚያስፈልገውን ርዳታ ለውሳኔ በሚያመች መልኩ መዝነው የሚያቀርቡ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ኮሚቴ ሠይሞ የነበረ ሲኾን፣ ከቀትር በኋላ ኮሚቴው ባቀረበው መሠረት፣ በድምሩ የ17 ሚሊዮን 900 ሺሕ ብር ርዳታና ድጎማ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲሰጥ ወስኗል፡፡
የርዳታ ጥያቄውን ላቀረቡት፡- በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት የፈራረሱ 11 የዛል አንበሳ አብያተ ክርስቲያን የሚገኙበት የዓዲ ግራት ሀገረ ስብከት አንድ ሚሊዮን ብር፤ በጎሠኞች ጥቃት የተፈናቀሉና የተጎዱ አብያተ ክርስቲያንና ምእመናን ለሚገኙባቸው የቤንሻንጉል ጉምዝ አንድ ሚሊዮን ብር፣ የምሥራቅ ወለጋ አንድ ሚሊዮን ብር፣ የሰሜን ሸዋ 300ሺሕ ብር እና የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ 200ሺሕ ብር እንዲሰጥ ወስኗል፡፡
ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለጠየቁት፡- በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በግንባታ ላይ ለሚገኘው የመርጡለ ማርያም ካቴድራል 5 ሚሊዮን ብር፣ ለደብረ ሊባኖስ ገዳም የአባቶች ማረፊያ 2 ሚሊዮን ብር፣ ለባሌ ሀገረ ስብከት የአብነት ት/ቤት ቋሚ በጀት 200 ሺሕ ብር እና ለኢሉ አባቦር ሀገረ ስብከት የአብነት መምህራንና ተማሪዎች 200ሺሕ ብር ቋሚ በጀት እንዲመደብ ወስኗል፡፡

በሌላ በኩል ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በዚኹ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ፣ የሦስት ዓመት የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት ዘመናቸውን በውጤታማነት ያጠናቀቁት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የቅርስ ጥበቃ እና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ እንዲኾኑ መድቧቸዋል፡፡
ምልአተ ጉባኤው ምደባውን ያደረገው፣ ብፁዕነታቸው ከጤና እክል ጋራ በተያያዘ ለክትትል እንዲመች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት እንደ ኾነ ተገልጿል፡፡ ብፁዕነታቸው፣ ላለፉት 15 ዓመታት፣ የደቡብ ትግራይ – ማይጨው እና ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
ከገቢ አኳያ፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ባስመዘገቡት 729 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ፣ ምልአተ ጉባኤው ከፍተኛ አድናቆትና ምስጋና የቸራቸው ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ በሀገረ ስብከታቸው መቐለ ዙሪያ፣ ከክልሉ መንግሥት በሊዝ መነሻ ዋጋ በወሰዱት 2070 ካሬ ይዞታ ላይ የሚያስገነቡት ለመንበረ ጵጵስና፣ ለካህናት ማሠልጠኛ እና ለቢሮ የሚያገለግል ኹለገብ ሕንፃ ተጠቃሽ ወቅታዊ ሥራቸው ነው፡፡
ዛሬ የተመደቡበትን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የቅርስ ጥበቃ እና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ የበላይ ሓላፊነታቸውን የሚወጡት፣ አህጉረ ስብከታቸውን እንደ ያዙ ነው፡፡
የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባው፣ በአጀንዳ ተ.ቁ(14) በተያዘው፣ አራተኛው ዙር የሕዝብና ቤት ቆጠራ በተመለከተ፣ የቤተ ክርስቲያን አቋም እና ቅድመ ዝግጅት ላይ መወያየት ጀምሯል፡፡
ባለፉት ቆጠራዎች የተፈጸሙትን ግድፈቶች በማረም፣ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮቿንና ምእመናኗን በትክክል ለማስቆጠርና የውጤቱም ተጠቃሚ ለመኾን፣ በአፈጻጸሙ ዙሪያ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በየአህጉረ ስብከታቸውና በማእከልም ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋራ መከናወን ስለሚገባቸው የጥንቃቄና የቅሰቀሳ ተግባራት አቅጣጫና መመሪያ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
