June 2, 2019
ምንት ውእቱ ረባሁ ለበግዕ ዘይትዐቀብ
ከመበላት ለማያመልጥ በግ መጠበቅ ምን ይጠቅመዋል?
ይህች ጦማር ለኢትዮጵያውያን ትድረስ
ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
nigatuasteraye@gmail.com
ግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ/ም
ከ40 ዘመን በውጭ ቆይታየ በኋላ ወደ ውድ አገራችን ኢትዮጵያ ሄጄ ከታህሳስ 13 እስከ ሚያዝያ 25 ቀን ቆየሁ። 4 ወራት ከ12 ቀናት ማለት ነው። የተማርኩባቸውን በገጠር ያሉትን አድባራትና ገዳማት ለማየት ከተለየሁባቸው ጥቂት ቀናት በቀር፤ የቀረውን ብዙውን ጊዜ ካሳለፍኩባቸው ቦታወች አንዷ የነስክንድር ቢሮ ናት።
ያዲስ አበባ ወጣቶች የሚገቡባትና የሚወጡባት ያች ቢሮ ስለ ኢትዮጵያና በውስጧ ስለሚኖሩ ዜጎች ብቻ የሚወያዩባት፤ ብር የማይቆጠሩባት፤ በህይወት ያሉና የሌሉ የጀግኖች አበው ስንክሳር በተግባር የሚያነቡባት፤ የእርስ በርስ ፍቅር የሚመነጭባት በከተማ ያለች ገዳም ናት። አራት ኪሎ ላይ ባለችው በዚህች ገዳም፡ የገደሙ ወጣቶችም ፤ ባለቤቱ ቢፈልግ አርዶ በሚበላው፤ ወይም ባለቤቱ ለሌላ በይ በሚሸጠው በግ የሚገለጹ ናቸው።
ከነሱ ጋራ ተቀምጨ የሚናበቡትን በሰማሁባት ቅጽበት ሁሉ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አባት ሆይ የሰማይና የምድር ጌታ ይህንን ከጥበበኞችና ካስተዋዮች ሰውረህ
ለሕጻናት ስለ ገለጽክላቸው አመሰግንሀለሁ”(ማቴ 11።25)ብሎ በአንክሮ ያቀረባት ምስግና ትዝ ትለኝ ነበር። በየአድባራቱ ካሉት ሁሉ ሰዎች ይህችን ጥበብ ሰውረህ፤ በዚህች ቢሮ ለሚሰበሰቡት ወጣቶች ይህችን ጥበብ የገለጽክላቸው አምላክ ተመስገን እል ነበር።
ካስተዋዮቾ ከጥበበኞች ተሰውራ ለህጻናት የተገለጸችው ይህች ጥበብ ምን ትሆን? ምናልባትም፡ ደመወዝ የምንጠይቅባቸው ቅዳሴ፡ ማህሌትና ስብከት የሚመስለን እንኖር ይሆናል። “በብዙ መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል“(የሐ 14፡ 22 )እያሉ ሐዋርያት ደጋግመው የተናገሩት፤ ለህዝብ ደህነት ሲባል እነ እስክንድር እንደሚያርጉት ከግዥወች ጋራ በእምነትና በቆራጥነት የሚደረገውን ትግል ነው እንጅ፤ ለደመወዝ ቅጥረኛ ሆኖ የሚቀደሰውን፤ የሚዘመረውንና የሚሰበከውን መከራ ብለው ሐዋርያት እንደማይተረጉሙት ግልጽ ነው።
ቅዱስ ጴጥሮስ “ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችኋል ያበረታችኋላ”(1ኛ ጴ 5፡10)ያለውም፡ “መጥፎ ረብ በመመኘት የእግዚአብሔርን መንጋ በግድ አትግዙ” እያለ በመገሰጹ ቁልቁል እስከመሰቀል ድረስ የደረሰበትን መከራና ግፍ
1
በእምነትና በቆራጥነት እንዲወጣው ስላደረገችው ጽናት እንጅ፤ እኛ ከምንቀድሰው ቅዳሴ ከምንዘምረውና ከምንሰብከው ጋራ የሚገናኝ አይመስለኝም። ቅዳሴው፡ ማኅሌቱ፡ ስብከቱ ምግብ ልብስ መጠጥና ሌላም ከምእመናን ኑሮ እጅግ የላቀ የተትረፈረፍ ንብረትና ጥሪት ከሚያተርፉልን ባሻገር ለመከራና ለስቃይ አይዳርጉንምና።
የነጴጥሮስን ፈለግ ይከተል የነበረው ዮሐንስ አፈወርቅም በድርሳኑ “እስመ ቦ እምሰብእ እለ
ይቤሉ ከመ መከራ ትወስድ ኀበ አዕምሮ ። ወታጠብብ ፈድፋደ እማካልኣኒሃ”(5፡ቁ180)ብሏል። የአረፍተ ነገሯ ጽንሰ ሀሳብ እንደሚከተለው ነው። ገዥወች በህዝብ ላይ የሚፈጽሙትን ግፍና መከራ እንዲያቆሙ የሚቃወሟቸውን ለማፈን፤ እየደበደቡ እያሰሩ እንደገና ደግመን አናደርገውም እያሰኙ ከፈቷቸው በኋላ፤ መከራውና ግርፋቱ እንደገና እንዳይደርስባቸው ከቀደመ አቋማቸው የሚያፈገፍጉ ብዙ ናቸው። በደረሰባቸው መከራ ካቋማቸው የማያፈገፍጉት ከቀድሞው ይልቅ እጅግ በላቀ ሁኔታ እንደ ብር ተሰንግለው፤ እንደወርቅ ነጥረው በህብረተ ሰባቸው መካከል ብቅ ይላሉ።
ዮሐንስ አፈወርቅ ሌላም በተግሳጹ የተናገረው አለ። “ኢንበል የአክለነ ዘገበርነ በውርዝውና።
አላ ንወስክ ገድልነ በዲበ ገድል በከመ ይደሉ። “ይደልወነ ንትጋደል በጻሕቅ በከመ ይቤ ጳውሎስ ሐዋርያ ሩጹ ወብድሩ። ወዘሰ ይረውጽ ወይበድር ኢይኔጽር ኀበ መኑሂ እምእለ ተዳደቅዎ በፍኖት። እመኒ ማእከለ ገነታት አው መእከለ ገራውህ። ዘሰ ይረውጽ ኢይኔጽር ኀበ ምስጋሪሁ። ዘእንበለ ዳእሙ ኀበ እሤቱ። እመኒ ርዕይወ ብኡላን አው ነዳያን። ኢይትመየጥ ድኅሬሁ ። ወኢኀዝኖ ምንትኒ ኢውዳሴ ወኢሀሜት ወኢውግረተ ዕብን። ወኢይዜከር ውሉዶ ወኢብእሲቶ ወኢጥሪቶ። አላ ይከውን መፍቅዱ ከመ ይብጻሕ ወይንሣእ አስቦ” ምዕ 7)ብሎ ነበር።
ሲተረጎም፦“በጎልማሳ ዘመናችን የሰራነው ትሩፋት ይበቃናል አንበል። ነገር ግን የቀደመ ተጋድሎአችንን ሳናቆም እንቀጥል እንጅ። ጳውሎስ እንዳለው፦ በውድድር ተሰልፎ የሚሮጥ ማንንም አይመለከትም። የሚሮጥ እንቅፋት በበዛበት ሜዳ ቢሆን፤ በፊቱ ያለውን እንቅፋት ተመልክቶ አይበግረውም፤ የሚመለከተው አሸንፎ የሚቀዳጀውን የድል አክሊል ብቻ ነው። ባለጸጋ አይቶት በማድነቅ እንዲሸልመው፤ ጥረት ከሚጠይቀው ብዙ ላብ ከሚይስልበው ሥቃይ ይልቅ በድህነቴ ተገንዠ ወደ መቃብር ብሸኝ ይሻለኛል እንደሚል ፈሪና መንፈሰ ደሀም ሳይሆን። ከየትኛውም አቅጣጫ በሚመጣለት ውዳሴ አድናቆት ዝናና ሽልማት ሳይማረክ፤ በሚሰነዘርበትም ትችትና ነቀፋ ሳይበገር፤ የባለ ሥልጣን ውግረት ህሊናውን ሳይሰብረው፤ ልጆቹን ሚስቱን ንብረቱን የራሱን ጤና ሰውቶ ዘላለመዊውን የድል አክሊል ይቀዳጃል” የሐዋርያትንና ዮሐንስ አፈወርቅን ተግሳጻዊ መስፈርት በመላ ኢትዮጵያ ስዘረጋው በመስፈርቱ የሞሉልኝ እስክንድርና ባልደረቦቹ ናቸው ብል ተሳሳትኩ?
ባዲስ አበባ ቆይታየ እንደተረዳሁት፤ መንፈሳውያን ነን፤ የሰው ህይወት ያሳስበናል ብለው በአውደ ምህረት ላይ ህዝብ የሚያደነቁሩ፤ ነፍሳቸውንና ሥጋቸውን ለህዝብ ሊሰው ይቅርና፦ የጻፉትን ኩርባብች የጠለሰሙትን ጠልሰም በሳንቲም በሚቸረችሩበት ወቅት እነእስክንድር ከመከተል ማንን ልከተል? ከማንስ ጋር ልዋል? ፍረዱኝ? በእመቤታችን በጻድቃን በመላእክት ስእሎችና ከቅዱስ መጻሕፍት በተመዘዙ ጥቅሶች ባጃጃቸውንና ታክሲወቻቸውን ወደ ተንቀሳቃሽ ቤተ መቅደስ ቀይረው በሕሊና መሳጭ እንጉርጉሮ እያጀቡ የአዲስ አበባን ህዝብ የሚያገለግሉትን የአዲስ አበባን ወጣቶች በዚህ አጋጣም ሳልጠቅሳቸው
2
አላልፍም። የአዲስ አበባን አካባቢ ለማየት ከነሱ ጋር ስዞር ከሰጡኝ አገልግሎት ጋራ ብዙ አስተምረውኛልና።
እነእስክንድር አሁን ያሉበት ህይወት ከመላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬና በበጉ አጠናቅረው ከቀመሯት አስገራሚ ቅኔያቸው ጋራ አገናኘኝ። ከ82 ዓመት በፊት በታላቁ ደብር በዲማ ቅዱስ ጊርጊስ የቀመሯት ብዙ ምሥጢር አጠናቅራ የያዘችው የመላከ ብርሃን አድማሱ ቅኔ ከነ ማብራሪያዋ እነሆ!
እም አፈ አርዌ በግዐ ለእመ ዐቀበ፦ ኖላዌ አባግዕ አዕላፍ ምንት ኂርውናሁ።
ወምንት ውእቱ ለዘይትአቀብ ረባሁ።
እምአፈአርዌ እመአቀቦ፡ ውእቱ እስመ ይበልዖ ለአርዌ ከማሁ።
ወእመ ለሊሁ ኢይበልዖ፦ እስመ ይሰይጦ በወርቅ ለዘይበልዕ ኪያሁ።
ኂሩትሰ ወረባሕ ለኖላዊነ ትጋሁ።
በበትረ መስቀል ድህረ ዐቀበ እምአፈ አርዌ አባግኢሁ።
አምጣነ ደሞ ያሰቲ እንዘ ያበልዕ ሥጋሁ።
ወአፍአ ኢያወጽኦ ለዘመጽአ መንገሌሁ።
የበግ ባለቤት በጉን ከበላተኛ አውሬ ይጠብቀዋል። ሥጋ ሲያምረው አርዶ ይበላዋል። እራሱ ባይበላውም ለሌላ በላተኛ በብዙ ወርቅ አትርፎ ይሸጠዋል። ታዲያ በጉን ከአውሬ የጠበቀው ሲሰባለት አርዶ ሊበላው፤ ወይም ብዙ ብር አትርፎ ለበላተኛ ሊሸጠው ከሆነ ለበጉ ምንይጠቅመዋል?በጉ ምንጊዜም ቢሆን ከመበላት ስለማይድን፤ በጉን አውሬ እንዳይበላበት ባለቤቱ ለራሱ ጠበቀው እንጅ ለበጉ ያደረገው ችርነቱ ምንድነው?ምን ያስደንቃል?በቸርነት መደነቅና መመስገን የሚገባው እረኛስ፦ በጎቹን አቅጣጫና ዘዴ እየቀያየረ ከሚበላ አውሬ እየተከላከለ በበጉ ፈንታ ህይወቱን የሚሰዋ ነው”
እነ እስክንድር በሚቀኙት ቅኔ፤ ስለ ኢትዮጵያ እየተቀኙ ያለፉትን መላከ ብርሃን አድማሱን እንዳየሁበት፤ በመላከ ብርሃን አድማሱ ቅኔም አሁን በመቀኘት ላይ ያሉትን እነ እስክንድርን አያቸዋለሁ። መላከ ብርሃን በበጉ አጠናቀረው ባቀረቡት ሰማሰም ቅኔ እነ እስክንድርን እና አሁን የሚደረገውን ተመለከተኩ። ካሁን በፊት የነበሩት ገዥዎች ሲያስሩት የነበረውን እስክንድርን፤ የዛሬዎቹ የሚያስሩት ከሆነ፤ የቀደሙት መሪወች ኢትዮጵያን ካንድ ጎሳ አገዛዝ ፈልቅቀው ለሌላ ጎሳ አገዛዝ የሚዳርጓት ከሆነ፤ የቀደሞቹ ከቤተ መንግስት ተወግደው፤ የዛሬወቹ ወደ ቤተ መንግሥት መምጣት ለኢትዮጵያ ህብረተ ሰብ ጥቅሙ ምንድነው? እጅግ ሚያስደንቀውስ የነዮሐንስ አፈወርቅን ምሳሌ በመከተል፤ የራሱን ህይወት ቤተ ሰብና ጥቅም ሰውቶ በማይለወጥ አቋሙ ጸንቶ ከዚህ ቀደም የተፈጸመበት እስርና እንግልት ሳይበግረው፤ በህዝብ ላይ ያንዣበበውን መከራ ለመሸከም አሁንም ድምጹን የሚያሰማው የእስክንድና የመሰሎቹ አቋም ይመስለኛል ብል ተሳሳትኩ?
እዚህ ላይ “በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ በደረቀውስ እንዴት ይሆን? አለ (ሉቃ 23፡31)። ብሎ ክርስቶስ የተናገረውን ልጥቀስ። በደል ባልተገኘበት፤ የበደል
3
ንክኪ በሌለበት፤ ዓለም ባወቀው በእስክንድር ላይ፤ ይህ ዛቻና የማሰር ሙከራ ከተቃጣ፤ ዓለም በማያያቸው በገጠር ባሉት ሁሉ የሚደርሰው መከራ ምን ያህል ይከብድ ይሆን?
ይህን ስል፦ አባቶቻችን የሚጠቅሷትን ረስቼ አይደለም። እንዲህ ይላሉ። “የሰይጣን ባለሟሎች አገር የምታፈርስ የህብረተሰብ ኑሮ የምታቃውሰውን ታላቅ ነገር፤ ትንሽ በጣም ትንሽና ረቂቅ አርገው፤ ጎልተው በሚታዩ በብዙ ማጭበርበሪያ ንግግሮች ጠቅልለውና ሸፋፍነው ለህብረተ ሰብ ያቀርቧታል። ከተሸፋፈነችባቸው ሸፍጦች ፈልፍለው በማውጣት ለህዝብ ማሳየት የሚችሉት እንደ እነ ስክንድር ያሉት የሚያሰሙትን የተቃውሞ ድምጽ ያፍናሉ። ፤ አቅማቸው ፈቅዶላቸው አስቀድመው በማየታቸው ገልጸው የሚናገሩትን የሚተቹና የሚነቅፉ ፍልፍሎ የማየት አቅም የሚያጥራቸው ወገኖች ይበዛሉ። ፍርድ የሚያስከትለው ከአቅም ፈቃድ ከፍና ዝቅ እያልን በምንናገረው ሸፍጥ በምንሰራው በደል ስለሆነ፤ ባአዝጋሚ እይታቸው መጠን የሚተቹትና የሚነቅፉት የማየት አቅማችሁን አዳብሩ ብሎ ከመምከር በቀር ሊፈረድባቸው አይገባም” ይላሉ አባቶች።
ያም ሆነ ይህ፦ድንገት እየሄዱ ቤት በማፍረስ ላይ ያሉትን ከማፍረሳችሁ በፊት የሚጠለሉበትን ቦታ ሳታዘጋጁላቸው፤ ወልዳ የተኛችውን ያራሷን ቤት አታፍርሱ፤ ደሀውን ህዝብ አታፈናቅሉ እያሉ የሚያሰሙትን ድምጽ ለማፈን የሚሰነዘረው የማስፈራሪያ ዛቻ መገሰጽና መቆም ያለበት ተግባር ነው።
ይህ ማለትም፦ባፍራሾች ላይ ሊሰነዘር የሚገባውን ተግሳጽና ዛች አቅጣጫ አስታችሁ፤ አታፍርሱ ባሉት በእነ እስክንድር ላይ አትሰንዝሩ ለማለት እንጅ፤ የተመረጡለትን ስራ ባገባቡ በመወጣት ባሉት በመልካም መሪወች ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩት ህገ ወጦች መረን ይለቀቁ ማለት አይደለም። ወቅት እያነበቡ አጋጣሚ እየጠበቁ በጎውን ነገር ሁሉ እየመረዙ ለህዝብ የሚያቀርቡ ብዙ ሸፍጠኞች እንዳሉ ይታወቃልና።
በተረፈ በመላዋ ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሆይ! በጉን ከአውሬ የጠበቀው የበግ ባለቤት ሲሰባለት አርዶ ሊበላው፤ ወይም በብዙ ብር አትርፎ ለበላተኛ ሊሸጠው ከሆነ ለበጉ ምንይጠቅመዋል?የሻጭውና የገዥው በበጉ ላይ መፈራረቃቸውስ እንዴት ያስመሰግናቸዋል? መደነቅና መመስገን የሚገባውስ አቅጣጫና ዘዴ እየቀያየረ በጉን ከሚበላ አውሬ እየተከላከለ በበጉ ፈንታ ህይወቱን የሚሰዋው ነው።
በመላከ ብርሃን አድማሱ ቅኔ የነ እስክንድርን ህይወት በንቃትና በማስተዋል ተመልክታችሁ፤ እነ እስክንድርን በመሳሰሉ ሰዎች ላይ የሚሰነዘረው የማስፈራሪያ ዛቻ እንደገና እንዳይደገም፤ ተግሳጽና ድጋፍ ትሰነዝሩ ዘንድ በንጽጽር ያዘጋጀኋት ይህች ጦማር ትድረሳችሁ።
4

