ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በካርቱም አየር ማረፊያ ደርሰው አቀባበል ሲደረግላቸው

PM office

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ፍጥጫ ላይ ያሉትን የሱዳን መንግሥት ወታደራዊ መሪዎችና ሕዝባዊ ተቃውሞውን የሚመሩትን ተቃዋሚዎች ለማነጋገር ዛሬ ጠዋት ሱዳን መዲና ካርቱም መግባታቸውን ኤ ኤፍፒ ዘገበ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የኢታማዦር ሹሙ ጄነራል ሰዓረ መኮንን፣ አምባሳደር ሙሐመድ ድሪር ከልኡካን ቡድኑ አባላት መካከል ይገኙበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ካርቱም ያቀኑት ሰሞኑን የተከሰተውን ደማፋሳሽ ግጭት ተከትሎ ነው። በጉዟቸውም በሃገሪቱ የነገሰውን ውጥረት ለማብረድ አልበሸርን ከስልጣን አንስተው ጊዜያዊውን አስተዳደር የሚመሩትን ወታደራዊ ባለስልጣናት በቀዳሚነት እንደሚያናግሩ ተገልጿል።

ለሰዓት በኋላ ደግሞ ወታደራዊው አስተዳደር ስልጣኑን በቶሎ ለሲቪሎች እንዲያስረክብ ግፊት እያደረጉ ያሉትና በርካታ ደጋፊዎቻቸው እንደተገደሉባቸው የሚናገሩትን የተቃዋሚውን ቡድን መሪዎች ያናግራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር የግብፅ መንግሥት ተወካዮችም ውጥሩቱን ለማርገብ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ሱዳን ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት ሰላምና ደህንነት ኮሚሸነር ስማሊ ቼሩጉኢ አብረው እንደሚሆኑም ተነግሯል።

የአክሱም ሙስሊሞች ጥይቄ መቼ ምላሽ ያገኝ ይሆን?

አፍሪካውያን ስደተኞች በአሜሪካ ድንበር ደጅ እየጠኑ ነው

ካፍ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ድጋሚ እንዲካሄድ አዘዘ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጉዞ 108 ተቃዋሚ ሰልፈኞች መሞታቸው ከተነገረና ትናንት አፍሪካ ህብረትም ይህንን ተከትሎ ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር እስክትመለስ ድረስ ከየትኛውም የህብረቱ እንቅስቃሴ እንዳገዳት ካስታወቀ በኋላ ነው።

ሰሞኑን በተካሄደው ደም አፋሳሽ ተቃውሞ ውስጥ የሀገሪቱ ልዩ ኃይል በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ እርምጃ መውሰዱ የተነገረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሱዳን ከተሞች በስፋት ተሰማርተው ይገኛሉ ተብሏል።

የሱዳን ጤና ጥበቃ ሚኒስትር የተገደሉት ተቃዋሚ ሰልፈኞች 61 ብቻ ናቸው ያሉ ሲሆን፤ ከተቃዋሚ ሰልፈኞች ጋር ግንኙነት ያላቸው የሐኪሞች ቡድን ግን ሟቾቹ 100 እንደሆኑ መግለፃቸው ይታወሳል።

ለወራት የዘለቀው ተቃውሞ ወደ ብጥብጥ ያደገው ሰኞ ዕለት የደህንነት ኃይሎች ለወራት ከመከላከያ ኃይሉ ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት በመቀመጥ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ሰልፈኞችን ማዋከብ ከጀመሩ በኋላ ነው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሺር ከስልጣን ከወረዱ ኋላ ይህ ወታደሩ የወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ሟቾች የተመዘገበበት ነው።

ከሰኞ ጀምሮ በተቃዋሚዎች እና በወታደራዊ ምክር ቤቱ መካከል ሲደረግ የነበረው ንግግር የተቋረጠ ሲሆን የእንግሊዝ መንግሥት ያለውን ስጋት በተወካዩ በኩል ገልጧል።

ተያያዥ ርዕሶች