June 8, 2019
Source:https://1.gravatar.com/avatar/7f09202441ad3b4b636e88820d6a7061?s=96&d=identicon&r=G

- ፕሬዝዳንቷ በጉባኤው ተገኝተው፣ ብፁዓን አባቶች አቋማቸውን እንዲያጠናክሩ ተማፀኑ፤
- ከውግዘቱ ባሻገር ተጠቂን ለመታደግ፣ቤተሰብን ለማዳንና ትውልድን ለማስቀጠል እንሥራ፤
- እንደ IPPF AR ያሉቱ፣ በሥነ ፆታ እና ጤናማ ተዋልዶ ሽፋን ድርጊቱን እያስፋፉ ነው፤
- በኀያላን መንግሥታትና ሰዶማውያን ማኅበራት እስከ 250 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦለታል፤
- 42 የአፍሪቃ አገሮች ተቋማትን በአባል ማኅበራቱ ተጣብቶ ዓላማውን በሽፋን ያራምዳል፤
- ከተመድ ጀምሮ፣ አህጉራዊ ተቋማትንና መንግሥታትን፣ ለፖሊሲ ድጋፍ ይወተውታል፤
- ፋሚሊ ዎች በአንጻሩ፣ ትውልዱ ከተጋላጭነት እንዲጠበቅ ከወላጆች ጋራ የሚሠራ ነው፤
- “አገርና ታሪክ አለን ካላችሁ ሰለባውን ነጥቃችሁ ቤተሰብን ታደጉ፤ትውልድን አስቀጥሉ፤”
- ሰኞ የሚጠናቀቀው ምልአተ ጉባኤ፣ በመግለጫ የሚያካትተው ጠንካራ አቋም ይጠበቃል፤
***
ለሰው ፍጹም ተፈጥሯዊ ያልኾነውን የግብረ ሰዶም ኀጢአት፣ ነውርና ወንጀል ማውገዝ፣ ቤተሰብን የማዳንና ትውልድን የማስቀጠል ጉዳይ እንደኾነ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ያስረዱት የፋሚሊ ዎች ኢንተርናሽናል ፕሬዝዳንት ሻሮን ስሌተር፣ ቤተ ክርስቲያን ችግሩን የመከላከል አቋሟን በማጠናከር ሰለባዎችን ነጥቆ የማዳን ሥራም እንድትሠራ ተማፀኑ፡፡
በቱሪዝም ሽፋን በተደራጀ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ድርጊቱን ለማስፋፋት ያቀዱ ግብረ ሰዶማውያንን ቅዱስ ሲኖዶስ ካወገዘበት ከረቡዕ ስብሰባ በኋላ፣ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን ጋራ ምሽቱ ላይ ተገናኝተው የተወያዩት ፕሬዝዳንቷ፣ በማግሥቱ ኀሙስ ጠዋት ከሦስት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋራ በምልአተ ጉባኤው ፊት ቀርበው፣ ለተወሰደው ጠንካራ አቋም የድርጅታቸውን ድጋፍና አድናቆት ገልጸዋል፡፡

መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የበጎ ፈቃድ ድርጅታቸው፥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በራሱ በአሜሪካ መንግሥትና በየአህጉሩ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ፣ ቤተሰብ ተኮር በኾኑ ጉዳዮች፦ ወላጆች ልጆችን በመልካም የሚያሳድጉበትን፣ ልጆችም በትምህርት ተቋማት ከሞራል እና ሠናይ ምግባር ተፃራሪዎች ተጋላጭነት የሚጠበቁበትን፣ በዋናነትም በሚመለከታቸው አካላት በጎ ፖሊሲዎች የሚታነፁበትን አዎንታዊ ተጽዕኖ በመፍጠር እየሠራ እንደኾነ ጠቅሰዋል፡፡
በአንጻሩ በሰብአዊ ረድኤትና ልማት ስም ወደ አፍሪቃ ከሚመጡ ድርጅቶች ጥቂት የማይባሉት፣ ለመንግሥታቱ በይፋ ከሚቀርቡት ማኒፌስቶ በተቃራኒ፣ ግብረ ሰዶምን የመሳሰሉ ነውረኛ ተግባራትን፣ በወጣቶች ፆታዊ መብቶችና ነፃነቶች ጥበቃ ሽፋን እያስፋፉ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
የሩካቤ ሥጋ ነፃነት እና ጤናማ ሥነ ተዋልዶ የሚሉት ዋነኛ እንደኾኑ አንሥተዋል፡፡ በሰዶማዊ ድርጊት፥ ወጣት ወንዶችን ለኤች.አይ.ቪ አትጋለጡም፤ ከበሽታውም ነፃ ትኾናላችኁ፤ በማለት ወጣት ሴቶችን ደግሞ፣ እርግዝና እና ውርጃ አያሰጋችኹም፤ እያሉ እየገፋፉ ለልቅነት እንደሚያበረታቷቸው አብራርተዋል፤ “በፊንጢጣ የሚደረግ ግንኙነት ከተፈጥሯዊው 17 እጥፍ ለኤች.አይ.ቪ ተጋላጭ እንደሚያደርግ በጥናት ተረጋግጧል፤” ብለዋል ፕሬዝዳንቷ፡፡ በማደጎ ስም የወሰዷቸውን ሕፃናት ተፈጥሯዊ የፆታ ማንነትና ሚና እያቃወሱ መልሰው ወደ ትውልድ አገራቸው በማምጣት ብዙዎችን በአስተሳሰቡና በድርጊቱ እየጎዱ እንዳሉ፤ ኢትዮጵያም ከዚሁ ስጋት ነፃ እንዳልኾነች አስታውቀዋል፡፡
በበጎ አድራጎት ሽፋን ድርጊቱን ያስፋፋሉ ካሏቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ፣ በናይሮቢ መቀመጫውን ያደረገውን IPPFAR የተባለውን እንግሊዛዊ ድርጅት በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በሰብአዊ መብቶችና ረድኤት ስም የሚያገኛቸውን በተለይ ከ25 ዓመት በታች የኾኑ ወጣቶች፣ በሩካቤ ሥጋና በሥነ ተዋልዶ ጤና መብቶች(sexual and reproductive health and rights – access to SRHR services) ምንም ዓይነት ገደብና ክልከላ ሊደረግ እንዳይገባ አድርጎ እየሰበከ እንደሚያበላሻቸው፥ Rights, Sexuality and Living with HIV/AIDS የተሰኘ ኅትመቱን በአስረጅነት ለምልአተ ጉባኤ እያሳዩ አስረድተዋል፡፡

በፕሮግራሙ የጋራ አቋም ለማስያዝና በፖሊሲ እነፃ ለማስደገፍ፥ ከተመድ ወኪል ድርጅቶች(UNAIDS, UNFPA, UNICEF) ከአፍሪቃ ኅብረት፣ ከክፍለ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች፣ ከ42 የአህጉሩ መንግሥታት፣ ከሲቪል ማኅበራት፣ ከአብያተ እምነት ተቋማትና ከግሉ ማኅበረሰብ ጋራ በአባል ማኅበራቱ አማካይነት እንደሚወተውት፣ የተጣባቸው መንግሥታዊ ተቋማትም ስለ መኖራቸው አትተዋል፡፡ ከኅብረቱ የአጀንዳ 2063 ጋራ በማጣመር እ.አ.አ በ2022 አሳካዋለኹ ለሚለው ስትራተጂ፣ በኀይለኛው ሀብት እያሰባሰበ ሲኾን፣ ለያዝነው ዓመት ብቻ ከዓላማው ደጋፊ ኀይሎች እስከ 250 ሚሊዮን ዶላር እንደተመደበለት ገልጸዋል፤ በግንባር ቀደምነት ይረዳሉ ያሏቸውን ኀያላን ምዕራባውያን መንግሥታት በስም ጠቅሰዋል፡፡
“አጀንዳቸውን በየጊዜው እየቀያየሩና የድኻ አገሮች መንግሥታትን እያሳሳቱ ስለሚገቡ መጠንቀቅና በንቃት መጠበቅ ይበጃል፤” ያሉት ፕሬዝዳንቷ፣ የአንጋፋዋ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ረገድ የወሰደው ጠንካራ አቋም፣ በቤተሰብ ደኅንነት መጠበቅ ዙሪያ የሚሠሩ እንደ ፋሚሊ ዎች ያሉ የበጎ ፈቃድ ተሟጋቾች፣ አዎንታዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር እንደሚያስላቸው አመልክተዋል፡፡
“ድርጊቱ ውስጥ ለውስጥ በአስጊ ኹኔታ እየተስፋፋ ነው፤ ቤተሰብን እያጣን ነው፤ ብዙ ሕፃናት፣ ብዙ ሰው እየተጎዳ ነው፤” ያሉት ወ/ሮ ሻሮን ስሌተር፣ ሰዶማውያንን ማውገዝ፣ ቤተሰብን የማዳንና ትውልድን የማስቀጠል ጉዳይ እንደኾነ አስገንዝበዋል፤ ከማውገዝ ባሻገርም፣ ሰለባዎቹን ከተወሰዱበት ነጥቆ ለማዳን፥ በማስተማር፣ ምክክርና ድጋፍ ቤተ ክርስቲያን ጠንክራ እንድትሠራ ተማፅነዋል፤ ድርጅታቸውም ጥረቱን እንደሚያግዝ አስታውቀዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ቅዱሳት መካናት ለመምጣት ሲፎክሩ የነበሩት የተደራጁ ግብረ ሰዶማውን፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ውግዘትና ሌሎች አካላት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ልዩ ልዩ የማዘናጊያ መልእክቶችን እያስተላለፉ እንዳሉ ቢገለጽም፣ አጀንዳቸውን በየጊዜው እየቀያየሩ ያለማስታወቂያም ሊመጡ ስለሚችሉ፣ ፕሬዝዳንቷ እንዳሉት ንቃትና ጥንቃቄ ከማድረግ መቦዘን የለብንም፡፡
የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው በውግዘቱ፦ ተቃውሞውን ገልጾ ለመንግሥት ደብዳቤ እንዲጻፍ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በየአህጉረ ስብከታቸው ጠንክረው እንዲያስተምሩ፣ ቤተሰብ ራሱንና ልጆቹን እንዲከታተልና እንዲጠብቅ፣ በቅዱሳት መካናት ትብብር እንዳይደረግላቸውና በንቃት እንዲጠበቁ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
የድርጁ ግብረ ሰዶማውያኑን የእንመጣለን ማስታወቂያ በግንባር ቀደምነት ከተቃወሙት አንዱ የኾኑት፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ፣ የፋሚሊ ዎች ኢንተርናሽናል ፕሬዝዳንትና የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ እንዲገናኙና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ ቀርበው ማስረዳት እንዲችሉ የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡