June 10, 2019

የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያጋራ ምክር ቤት የህዝብና ቤት ቆጠራው ለአንድ አመት እንዲራዘም ወሰነ።

5ኛው የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ አመት የስራ ዘመን 3ኛ ልዩ የጋራ ስብስባ ዛሬ ተካሂዷል።

በዚህም የህዝብና ቤት ቆጠራው ይራዘም አይራዘም በሚለው ጉዳይ ላይ ከተወያየ በኋላ ቆጠራው ለአንድ አመት እንዲራዘም ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ ውሳኔውን በ30 ተቃውሞ እና በ3 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ነው ያሳለፈው።

በጋራ ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ቆጠራው ከአንድ አመት በላይ ላልተወሰነ ጊዜ ይራዘም የሚልና አሁን ላይ ያለው የሰላም ሁኔታ መሻሻል በማሳየቱ ለ6 ወር ብቻ ይራዘም የሚል የመከራከሪያ ሃሳብ ቀርቧል።

ከጋራ ምክር ቤቱ ስብሰባ ቀደም ብሎ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የህብና ቤት ቆጠራው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ውሳኔ አሳልፈው ነበር።

በዚህም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብና የቤት ቆጠራው በ8 ተቃውሞ እና በ4 ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ሲወስን፥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በ24 ተቃውሞ እና በ2 ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ህዝብና የቤት ቆጠራው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ወስኗል።

በምክር ቤቶቹ በነበረው ውይይት ላይ አሁን ያለው የሰላም ሁኔታ መሻሻል ቢታይበትም ቆጠራውን ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩ በምክንያትነት ቀርቧል።

ከዚህ ባለፈም በርካታ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውና ለቆጠራው ባላቸው ዝግጁነት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑ፥ እንዲሁም ቆጠራውን የሚያደርጉ ሰራተኞች ከቦታ ቦታ መዘዋወር በማይችሉበት ሁኔታ ቆጠራው መካሄዱ አግባብ አለመሆኑ ተጠቅሷል።

ከዚህ አንጻርም አመቺ ሁኔታ በሌለበት አግባብ መካሄድ የለበትም በሚል ቆጠራው እንዲራዘም ተወስኗል።

FBC