June 12, 2019
ምንጭ : (ኢትዮ 360 )

በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ አርሶ አደሮች አላግባብ ከመሬታቸው እንዲነሱ መደረጋቸውን ገለጹ
(ኢትዮ 360 )
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ተለሁደሬ ወረዳ ለምድር ባቡር ግንባታ በሚል አላግባብ ከመሬታቸው እንዲነሱ መደረጋቸውን የአካባቢው አርሶ አደሮች ገለጹ።
እነሱ እንደሚሉት በ13 ቀበሌዎች ይካሄዳል የተባለው ግንባታ ከ1 ሺ በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን መሬት አልባ አድርጓል።
መሬታቸውን ከተነጠቁ አራት አመት እንደሆናቸው የሚገልጹት አርሶ አደሮች ለምድር ባቡር ግንባታ በሚል ለወደመባቸው ንብረት ካሳ ማግኘት አልቻሉም። ከዚህም አልፎ ይላሉ አርሶ አደሮቹ ለኢትዮ 360 በአካባቢው ውሃ እናወጣላችኋላን በሚል ተራራ እንዲናድ ተደርጎ ውሃው ቢገኝም አገልግሎት ላይ እንዳይውል በሚል እንዲዘጋ ተደርጓል ብለዋል።
ከአዋሽ ወልዲያ ሃራ ገበያ የተኮናተረው የቱርኩ ኩባንያ ያፒ መከርዚ ግንባታውን የሚያከናውን ቢሆንም የምድር ባቡርና የወረዳው አስተዳደር ስራውቸውን በትክክል ባለማከናወናቸው የተፈጠረ ችግር ነው ይላሉ።
መብታችን ካልተከበረ እንዴት ልማት ማከናወን ይቻላል በሚል ጥያቄ በማቅረባቸው የውሃ አገልግሎቱ እንደተቋረጠባቸው ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ በዚህም የተነሳ ያለሙት እርሻ ከጥቅም ውጪ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ጉዳያቸውን ከዞን እስከ ክልል አስተዳደር ለማሳወቅ ቢሞክሩም ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውን ይገልጻሉ።
በህግ ለመጠየቅ ያደረጉት ሙከራም እስካሁን እየተጓተተ ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ይናገራሉ።
ኢትዮ 360ም ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ደቡብ ወሎ ዞን ያደረገው የስልክ ጥሪ ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም።