
12 June 2019
አቶ ጌታቸው አሰፋን በሚመለከት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ድረስ ሊያስጠይቅ የሚችል ጉዳይ አለ ብለዋል
ሆን ተብሎ መንገድ በመዝጋት ሕዝብ ለማስራብና ለማስጠማት የተደረገው በመንግሥት ዕውቅና ነው ሲሉ ኮንነዋል
መንግሥት ስለአንድነት እየተናገረ ባለበት አገር ውስጥ አንድነትን የሚያሳጣ አዝማሚያ በመብዛቱና በትግራይ ሕዝብ ላይ ሆን ተብሎ በሚደረግ ‹‹የዘር ጥቃት ሕዝቡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ አብሮ እንዳይቀጥል የሚገፋፋና የሚበትን አዝማሚያ›› እየተበራከተ በመምጣቱ፣ ሕዝቡ ከሥርዓቱ ጋር አብሮ ከመቀጠል ይልቅ መገንጠል ስሜት ውስጥ መግባቱን የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ በተለይ ከሪፖርተር ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ሕዝቡ በሚደርስበት ዘር ተኮር ጥቃት ሳቢያ ከፌዴራልም ሆነ ከክልል መንግሥታት ጋር አብሮ በአንድነት መቆየት ላይ ተስፋ ቆርጧል፡፡ ‹‹እኛ ነን አብረን እንታገላለን፣ እናስተካክላለን እያልን ያረጋጋነው እንጂ ሕዝቡ የመገንጠል ስሜት አድሮበታል፡፡ እየተገፋና ሆን ተብሎ በሚፈጸም ጥቃት ሕዝቡ ከዚህ ሥርዓት ጋር አብሮ መቀጠል እንደማይቻል እየገለጸ ነው፡፡ በትግራይ ላይ የዘር ጥቃት በይፋ ታውጇል፡፡ ከራስህ መንግሥት የማትጠብቀው ዘመቻ ተከፍቷል፤›› ብለዋል፡፡
በዘርና በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በትግራይ ላይ እየተፈጸመ ለመሆኑ ማሳያ ካደረጓቸው ነጥቦች መካከል በመካከለኛና በታችኛው የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የተመደቡ ሁሉ፣ በአቅም ማነስ ሳይሆን የትግራይ ሰው ስለሆኑ ብቻ ከቦታቸው የተነሱ ኃላፊዎች በርካታ ናቸው ብለዋል፡፡
‹‹በአገር ደረጃ የዕብደት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ትግራይን ለማጥቃት ከማዶ አጀንዳ የሚሰጡ፣ የሕዝብ ጥያቄ አስመስለው የሚንቀሳቀሱ አሉ፤›› ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ‹‹ሰላም እንዲያስከብር በበላይነት ኃላፊነቱን የወሰደው አካል ሲያበላሽ እኛ እያስተካከልንለት ነው፡፡ የእኛ ሥራ ማቀጣጠል አይደለም፡፡ ከክልላችን በላይ ኃላፊነት ደጋግመን በመውሰድ ሰላም ለማስፈን ችለናል፡፡ ግን ለጥቃትና ለማበጣበጥ ኃይል እየተላከብን ነበር፡፡ ከሕግ ውጪ በሆነ መንገድ ወታደር እየተላከብን ለማበጣበጥ ተሞክሯል፤›› በማለት በፌዴራሉ መንግሥት ላይ ከባድ ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አጎራባች በሆነው የአማራ ክልል የመንግሥት ኃላፊዎችም ሆነ በፌዴራል መንግሥት ዕውቅና የተሰጠው በሚመስል አድራጎት፣ የፌዴራል መንግሥት ንብረት የሆነው አውራ መንገድ እየተዘጋ ጭምር ሕዝብ እንዲራብና እንዲጠማ ለማድረግ ተሞክሯል ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ብያኔ እየተካሄደ ነው፡፡ መንገድ እየተዘጋ ሕዝብ ሆን ተብሎ እንዲራብና እንዲጠማ ለማድረግ የሚፈጸም ወንጀልን የአማራ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ዝም ማለታቸው ሆን ተብሎ ጫና ለመፍጠር መንግሥት ፈቅዷል እንላለን፡፡ መኪና ማለፉ ወይም አለማለፉ አይደለም፡፡ ምግብ እንዳይበላ በሚመስል መንገድ የተደረገ ነው፡፡ ሕዝቡ መብላት ባያቅተውም እንዲህ የተደረገው ሆን ተብሎ ነው፡፡ ሕዝብ ላይ ጥቃት ሲፈጸም ዝም ያለው መንግሥት ተጠያቂ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር የአቶ ጌታቸው አሰፋን ጉዳይ በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ መጠየቅ ያለበት፣ ያጠፋ ይጠየቅ ካሉ በኋላ፣ ‹‹ደማቅ ፊርማ ያለው ቀላል ፊርማ ያለው የሚባል ነገር የለም፡፡ ብሔሩ ትግራይ ስለሆነ ብቻ ከእየ ኮሚቴው እየተመረጠ የሚታሰር ብዙ ነው፡፡ ሊገመት የማይችል ወደ ታች መውረድ እየታየ ነው፡፡ ይኼ የእኛ መንግሥት ነው እንዴ የሚያስብል ዝቅጠት እየታየ ነው፤›› ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ እንደ መንግሥትና እንደ ሕግ አግባብ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆኖ በግሉ ያጠፋ ካለ ‹‹ይንጠልጠል ብያለሁ›› በማለት በሕግ አግባብ የሚወሰድ ዕርምጃን እንደሚደግፉ፣ ሆኖም በአቶ ጌታቸው አሰፋ ላይም ሆነ ሌሎች ላይ እየቀረበ ያለው ክስ ግን ‹‹በዓለም ላይ አሳፋሪ የሚባል›› ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡
የደኅንነት ሠራተኞች ‹‹ኤርትራ ሄዳችሁ ሰለላችሁ ተብለው እየተጠየቁ ነው›› ያሉት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ እንዲህ ያለው አካሄድ እጅግ አሳፋሪ እንደሆነባቸው የገለጹት፣ ‹‹ፖለቲካዊ ብልሽት ተከስቷል›› በማለት ጭምር ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕጋዊና ትክክለኛ ዕርምጃ ቢሆን ኖሮ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጭምር የሚጠየቁበት አግባብ እንደሚኖር፣ ሆኖም በግላቸው አቶ ኃይለ ማርያምም ሆኑ አቶ ጌታቸው፣ እንዲሁም ሌሎች የታሰሩ ሰዎች ለመንግሥትና ለሕዝብ በማገልገላቸው መታሰር እንደማይገባቸው፣ በተጨማሪም ከደኅንነት ሥራ ጋር ከተያያዘ የታሰሩ ሰዎች እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡
አንባቢያን ሰፊውን ቃለ ምልልስ በቅዳሜው የእንግሊዝኛ ዘ ሪፖርተርና በእሑድ የአማርኛ ሪፖርተር ጋዜጦች እንዲያነቡ እናሳስባለን፡፡