Sheger FM : የመንግስት ድርጅቶች አትራፊና ቀጣይ እንዲሆኑ ለማብቃት ከስራ አስፈፃሚዎች በላይ የቦርድ አባላት ይሾማሉ፡፡ የቦርድ አባላት፣ በአብዛኛው የመንግስት የጊዜው ባለስልጣናት ይሆናሉ፡፡ በተለይም ገንዘብ አመንጪ በመሆናቸው በሚታወቁት ተቋማት የሚመደቡት ቢናገሩ የሚደመጡ ጎምቱ ባለስልጣናት ሲሆኑ ይታያል፡፡
እንዲያውም፣ ጠቀም ያለ የቦርድን ክፍያ ለማግኘት በሚያስችሉ ቦታዎች እንዲጠቀሙ የሚፈለጉ ሹማምንት ይመደባሉ የሚል ሐሜት በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ ይሁንና አሿሿማቸው ላይ የሚሰጠው አስተያየት ቢያከራክርም የተመደቡባቸው ተቋማት ሲዘበራረቁና ውድቀት ሲያሳዩ የቦርድ አባላት ተጠያቂ ሲሆኑ አይታይም፡፡
በሚሰጡት መመሪያ ለጠፋው ጥፋት ተጠያቂ መሆናቸው ተነግሮ አያውቅም፡፡
በቅርቡም 6 የልማት ድርጀቶች መክሰራቸው ተነግሯል፡፡ ነገር ግን የድርጅቶቹ የቦርድ አባላት የመሪነት ሀላፊነታቸው ምን ያህል እንደተወጡ አልተነገረም፡፡ ለመሆኑ የድርጅት የቦርድ አባላት የሚመረጡትና የስራ አፈፃፀማቸው የሚመዘነው እንዴት ነው?