June 16, 2019

Source: https://haratewahido.wordpress.com
https://haratewahido.files.wordpress.com/2019/06/sequence-05.00_34_06_28.still003.png

ssd 8th round

ከመላው አህጉረ ስብከት የተወከሉ ከ200 በላይ ልኡካን የተሳተፉበትና ከሰኔ 7 ቀን ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት አዳራሽ ሲካሔድ የቆየው፣ የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፍ አንድነት 8ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ፣ባለ27 ነጥቦች የጋራ አቋም መግለጫ በማውጣት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡

የጋራ መግለጫው ዐበይት ነጥቦች፡-

***

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት 8ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ የቃለ ጉባኤ ማጠቃለያ እና የጋራ የአቋም መግለጫ፤

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤

ብፁዕ አቡነ ያሬድ
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና
የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ
በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስና
የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
ጥሪ የተደረገላችኹ የክብር እንግዶች
ክቡራን ክብራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤

ssd 8th gen assembly2

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት 8ኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ከየአህጉረ ስብከቱ በተወከሉ የሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አጠቃላይ ጉባኤ አባላትና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊና ሥነ ሥርዓት ተካሒዷል፡፡

ጉባኤው፣ ሰኔ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ጸሎተ ቡራኬ ተከፍቷል፡፡ ቅዱስነታቸውም፣ ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ የኾነ ሥራ እንድትሠሩበት የምትዘጋጁበትና የምትመካከሩበት ጉባኤ እንዲኾን እግዚአብሔር ይባርካችኹ፤ ይቀድሳችኹ በማለት አባታዊ ቡራኬና መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

Sequence 07.00_17_28_44.Still003

በማስከተልም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በተለያዩ አርእስት ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ፣ በሰሜን አሜሪካ የሜኒሶታና አካባቢው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ የሰው ባሕርያት በሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት በተመለከተ፤ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ የደቡብ ኦሞ ሀ/ስብከት ጳጳስ፥ ለእግዚአብሔር መታዘዝን በተመለከተ፤ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ በዓለ ጰራቅሊጦስን በተመለከተ ትምህርት ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠልም በማደራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ፣ የዘመኑን የሥነ ምግባር ውድቀት አደጋ ባካተተው የ2011 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርት ጉባኤው ሥራውን ጀምሯል፡፡ ከየአህጉረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ተወክለው የመጡ ወጣቶችም በተያዘላቸው መርሐ ግብር መሠረት ዓመታዊ ሪፖርታቸውን በንባብ አሰምተዋል፡፡

በሪፖርቶቻቸውም፣ በየአህጉረ ስብከቱ የወረዳና የአጥቢያ መዋቅሮች፣ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ የተቋቋመባቸውንና ያልተቋቋመባቸውን በቁጥር ለይተው አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም፣ ጉባኤ የተካሔደባቸውንና ያልተካሔደባቸውን፣ ምርጫ የተካሔደባቸውንና ያልተካሔደባቸውን ለይተው አቅርበዋል፡፡

የበጀት እጥረትን፣ የመማሪያ ቦታና የጽ/ቤት ችግሮችን፣ የስልታዊ ዕቅዱ አፈጻጸምን ያካተቱ ሲኾን፣ በወረዳና በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያሉትን የአሠራር ችግሮች፣ የሥርዓተ ትምህርቱን መጽሐፍ፣ የመዝሙረ ማሕሌትና የቪሲዲውን ሥርጭት በተመለከተ ከማደራጃ መምሪያው በተሰጣቸው የሪፖርት ቅጽ መሠረት አቅርበዋል፡፡

ጉባኤው፣ በአለፉት ሦስት ቀናት ቆይታው የሚከተሉት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ተወያይቶባቸዋል፤

  1. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የቀጣይ አምስት ዓመት ስትራቴጂ አፈጻጸም ላይ ሰፊ የቡድንና የጋራ ውይይት አካሒዷል፤
  2. ሀገር አቀፍ የሥርዓተ ትምህርት ትግበራን በተመለከተ፣
  3. የአንድነቱ ጉዞ ከ2004 እስከ 2011 ዓ.ም. ስኬቶቹ፣ ተግዳሮቶቹና መጻኢ ዕድሉ በተመለከተ፣
  4. የሥነ ሕዝብ ቈጠራ ጥቅምና ጉዳቱ፣ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ፋይዳውን በተመለከተ፣ ከተወያየ በኋላ የጋራ ግንዛቤና አቋም ወስዷል፡፡

በመኾኑም፣ የጥናቶቹ ቁልፍ ሐሳቦች ከለዩዋቸው ጥንካሬዎችና ችግሮች በመነሣት፣ በዚህ ጉባኤ የተሳተፍን የሰንበት ት/ቤቶች ጠቅላላ ጉባኤ አባላት፣ የሰንበት ት/ቤቶች ለዘለቄታው በጋራ የምንሠራባቸውንና የምንጠይቃቸውን ነጥቦች ያካተተ የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

1. ለኹለተኛ ጊዜ የተዘጋጀውን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የ5 ዓመት መሪ ዕቅድ ማለትም /ከ2012 – 2016 ዓ.ም./ የታቀደውን መሪ ዕቅድ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ቃል እንገባለን፡፡

Sequence 05.00_03_00_48.Still001

2. የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የ5 ዓመት መሪ ዕቅድ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ማለትም በሀገረ ስብከት፣ በወረዳ ቤተ ክህነት እና በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ዕቅድ አካል እንዲሆንና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችና ኮሌጆችም የሰንበት ት/ቤቶች መሪ ዕቅድ ከዕቅዳቸው ጋር በማገናዘብ በዕቅዳችው እንዲያካትቱ እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡

3. በ8ኛው ጠቅላላ ጉባኤ የተወያየንበትን የ2012 ሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎት የትኩረት አቅጣጫዎች መነሻ በማድረግ እንደየሀገረ ስብከታችን ተጨባጭ ኹኔታዎች ዕቅዶቻችንን በማስተካከል ለመተግበር ቃል እንገባለን፡፡

4. አህጉረ ስብከትን፣ ወረዳዎችንና አጥቢያዎችን መሠረት ያደረገ የሰንበት ት/ቤቶችን ትስስር በማጠናከር ሰንበት ት/ቤቶች ባልተቋቋመባቸው እንዲቋቋምባቸው፤ በተቋቋመባቸውም ደግሞ የተጠናከረ አገልግሎት እንዲሰጥባቸው ለማድረግ ጠንክረን እንሠራለን፤ ባለድርሻ አካላትም ድጋፋቸውን እንዲያደርጉልን መመሪያ እንዲሠጥልን እንጠይቃለን፡፡

5. የሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎት ዕቅድ ተፈጻሚነት የተሳካ ይኾን ዘንድ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በጀት ተይዞለት እንዲፈጸም በታላቅ ትሕትና እንጠይቃለን፡፡

Sequence 05.00_34_06_28.Still003

6. በአጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶቻችን፣ የመማሪያ መጻሕፍትና መምህራን እንዲሟሉልንና እንዲመደቡልን እንዲሁም የመማሪያ አዳራሽ ለሌላቸው ሰንበት ት/ቤቶች እንዲዘጋጅላቸው እንጠይቃለን፡፡

7. ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አንሥቶ አሰከ አጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች የሚደርስ የፋይናንስ ትስስርና የንብረት አያያዝ ሥርዓት በመምሪያው አቅራቢነት ቀርቦ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲጸድቅልን እንጠይቃለን፡፡

8. በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያኒቷ መንፈሳዊ ተልእኮ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለው የአፅራረ ሃይማኖት/የአማሌቃውያንና የመናፍቃን ወረራ/ እንቅስቃሴ ለማስቆም፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን አካላት ውጤት ያለው የተናጠል ርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን፡፡

9. በየዓመቱ ለሀገር አቀፍ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ትኩረት ለማይሰጡ፤ ተወካዮቻቸውን ያልላኩ አህጉረ ስብከት ተለይተው/ታውቀው/ ተወካዮቻቸውን እንዲልኩ ደረጃውን የጠበቀ መመሪያና አስፈላጊውም ቅጣት እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን፡፡

10. በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ልማታዊ ጉዳዮች ከአባቶቻችን ጋር በመኾን ያለንን አቅም አሟጠን በመጠቀም ለቤተ ክርሰቲያናችን ዕድገትና ልዕልና የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፡፡

11. የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ኹለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት ከመንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን ማኅበራት ጋራ ተባብረን የምንሠራ መኾናችንን እንገልጻለን፡፡

12. በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች በተሳሳተ አመክንዮ በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና አባላት ላይ እየደረሰ ያለው እስር፣ እንግልትና ወከባ እንዲቆምልን በአጽንዖት እንጠይቃለን፡፡

13. ከዚህም ጋር ተያይዞ የመንግሥት የፍትሕ አካላትም ከአጥቢያዎች ጋር በመተባበር የሰንበት ት/ቤትን አባላት ከማሰር እና ከማንገላታት እንዲታቀቡ እንዲደረግ በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል መመሪያ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን፡፡

14. ግብረ ሰዶማዊነት እንደ ሕግ ያጸደቁ አገሮች ወጣቱን ሥነ ምግባር በማሳጣት ለዓላማቸው ሰለባ እንዲኾን የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅመው እየሠሩ ስለኾነ፣ ቅድስት ቤተ ክርሰቲያን ወጣቱን ትውልድ ከዚህ ወረርሽኝ ለመታደግ በቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈውን መልእክቷን ለሚመለከተው ኹሉ እንደምናሰማ በአጽንዖት ቃል እየገባን፣ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነትና ስርጭትንም እናወግዛለን፡፡

15. የሰንበት ት/ቤቶችን ለማጠናከር፣ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለውን አደረጃጀት የሚያሠራ የበጀት ድጋፍ እንዲደረግልን እንጠይቃለን፡፡

16. በጥምቀትና በተለያዩ በዓላት የሚያገለግሉ ነገር ግን በመዋቅር ያልታቀፉ ወጣቶችን፣ በሰንበት ት/ቤት መዋቅር በማቀፍና መምህረ ንሥሓ በመመደብ በኹሉም አጥቢያዎች እንዲሠራበት መመሪያ አንዲሰጥበት እንጠይቃለን፡፡

17. ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ አህጉረ ስብከት የሚገኙ ወጣቶች ከሚያቀርቡት ጥያቄ አንጻር፣ ሰንበት ት/ቤቶችን እንዲያደራጁና በማደራጃ መምሪያው አማካይነት የአንድነት ጉባኤያት እንዲያቋቁሙ በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን፡፡

18. በአጥቢያ ደረጃ የሚከሠቱ ችግሮች መፍትሔ እንዲሰጣቸውና በዚያ የሚገኙ ሊቃውንትም ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ተተኪዎችን እንዲያፈሩ መመሪያ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን፡፡

19. ወጣቱን ከአደገኛ የሕይወት አዝማሚያ ለመታደግ በየሀገረ ስብከታችን ጠንክረን በመሥራት ሓላፊነታችንን እንወጣለን፤ ለሰንበት ት/ቤቶች መምህራን ሥልጠና ተግባራዊነት ተገቢውን ጥረት እናደርጋለን፡፡

20. የአፅራረ ቤተ ክርስቲያንና ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴን ለማምከን፣ በመዋቅሮቻችን ጠንክረን እንሠራለን፡፡

21. በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው የሕዝብ ቆጠራ፣ እኛ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በየሀገረ ስብከታችን ምእመናንን በማስተባበር የሚጠበቅብንን ሁሉ እንወጣለን፡፡

22. የሃይማኖት አክራሪዎች፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን እንቅስቃሴ ለማዳከም የሚያደርጉት የተቀነባበረ ጥቃት እንቃወማለን፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወስደውን ማንኛውም ውሳኔ እንደግፋለን፡፡

23. በጥቅምቱ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ የሚመጡ በመዋቅር ላይ ያሉ የሰንበት ት/ቤት ክፍሎች ሓላፊዎችና የአንድነቱ ተወካዮች እያሉ የማይመለከታቸው ሓላፊዎች እየተላኩ ስለኾነ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰንበት ት/ቤቶች ውክልና በአግባቡ እንዲጠበቅ ጠበቅ ያለ መመሪያ ለኹሉም አህጉረ ስብከት እንዲያስተላልፍል እንጠይቃለን፡፡ በተደጋጋሚ ይህን ተግባር የሚፈጽሙትን ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያስታግሥልን እንጠይቃለን፡፡

24. ከቀረበው ሪፖርትና ከነባራዊው ኹኔታ አንጻር፣ ባለፈው ዓመትና በአሁኑ ሰዓት ወላጆች፣ ሕፃናትና አረጋውያን፣ ሰብአዊ ክብራቸው ተነክቶ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን አጥብቀን እናወግዛለን፡፡

25. ለሰንበት ት/ቤቶች ማጠናከርያ በጀት መድበው የሰጡ አህጉረ ስብከትን ጉባኤው እያመሰገነ ሌሎች አህጉረ ስብከትንም ማደራጃ መመሪያው ለይቶ በሚያቀርበው መሠረት የሥራ ማስኬጃ በጀት እንዲመድቡ እንጠይቃለን፡፡

26. የመማሪያ አዳራሾች የሌላቸው ሰንበት ት/ቤቶች የቤተ ክርስቲያን አካል እንደ መኾናቸው መጠን አህጉረ ስብከት አዳራሾችን እንዲያዘጋጁላቸው ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን፡፡

27. ከቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውጭ በቤተ ክርስቲያን ስም ከመንግሥት አካላት እውቅና ለማግኘት የሚደራጁ ማኅበራት እውቅና እንዳይሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን፡፡

የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰን፡፡

ሰኔ 9 ቀን 2011 ዓ.ም.
አዲስ አበባ