June 17, 2019

በቦሌ ቡልቡላ ወጣቶች የተሰሩ የመጠለያ ቤቶችን በሃይል ለመውረር ያደርጉት ሙከራ በፖሊስ ሃይል ከሸፈ — የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ወጣቶቹ በፖሊስ ሃይል እንዲመለሱ ይደረግ እንጂ የአካባቢው ነዋሪ አሁንም ስጋት ላይ ነው።

(ኢትዮ 360 )

በቦሌ ቡልቡላ ከ200 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች የተሰሩ የመጠለያ ቤቶችን በሃይል ለመውረር ያደርጉት ሙከራ በፖሊስ ሃይል መክሸፉ ታወቀ።
በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ አራት ኪሎና ፍልውሃ አካባቢ ቤታቸው ፈርሶ በላስቲክ ውስጥ የነበሩና ቁጥራቸው 113 የሚሆኑ ዜጎች በዚህ መጠለያ ውስጥ እንዲያርፉ ከተደረገ አራት ወራት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
አራት በአራት የሆነውና በቆርቆሮ የተገነቡት ከ450 በላይ ቤቶች ንብረትነታቸው የአራዳ ክፍለ ከተማ መሆናቸውንም ከስፍራው ለኢትዮ 360 መረጃውን ያደረሱት ምንጮች ይገልጻሉ።

በመጠለያው እንዲያርፉ የተደረጉት ነዋሪዎች እንደሚሉትም ከአንድ ቀን በፊት ከአራዳ ክፍለ ከተማ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በመጠለያው እንዲያርፉ ተደርጓል።
ይህንን ተከትሎም ቁጥራቸው ከ200 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች መጠለያ ቤቶቹ ለእኛም ይገባናል በሚል አካባቢውን መውረራቸውን ይናገራሉ።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የተዘጉ ቤቶችን ብቻ ሳይሆን ግለሰቦች የገቡበትን ቤት ሳይቀር ወጣቶቹ በሃይል ለመያዝ ሞክረዋል።
ቁጥራቸው ከመብዛቱና ከቤቶቹ ቁጥር ጋር ባለመመጣጠኑ ለነዋሪዎቹ የተሰሩትን የጋራ ማብሰያ ቤቶችንም ለመካፈል ሲሞክሩ ነበር ብለዋል ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360።


ወጣቶቹ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው የሚሉት ነዋሪዎች ወጣቶቹ በሃይል የሚያስቆማቸውን አካል ለማጥቃት በሚመስል መልኩ ምስማር የተመታበት ዱላ ይዘው እንደነበርም ተናግረዋል።
መረጃው የደረሰውና ሁኔታው ያልተዋጠለት የአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደርም ሁኔታውን ለፖሊስ በመጠቆሙ ወጣቶቹ ሊያደርሱት የነበረውን ጥቃት መከላከል ተችሏል ባይ ናቸው።
በተሽከርካሪ ተጭነው መምጣታቸው የተገለጸው ወጣቶች እነሱ ከገቡ እኛስ የማንገባበት ምክንያት ምንድን ነው በሚል ቤቶቹን ላለመልቀቅም ሲያንገራግሩ እንደነበር ታውቋል