
ሃገር አቀፍ ፈተና በመጣ ቁጥር ከተፈታኞች ቀጥሎ ጭንቀት ውስጥ የሚገባው የበይነ-መረብ [ኢንተርኔት] ተጠቃሚው ነው።
ባለፈው ሳምንት፤ ማክሰኞ የሆነው ይህ ነው። ሃገር አማን ብለው ዓለም እንዴት እንዳደረች ለመቃኘት የጎገሉ አንጀት የሚያርስ መረጃ ማግኘት አልቻሉም። ኧረ እንደውም ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት ይቅርና የሞባይልም ሆነ ኮምፒውተር ስክሪናቸው ላይ ብቅ ሊል አልቻለም።
ተጠቃሚው የሞባይልና ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት እንደተቋረጠ የገባው ዘግየት ብሎ ነው። ኢንተርኔት ብትጠበቅ የውሃ ሽታ ሆና ቀረች። ከሰዓት በኋላ አካባቢ ግን ብቅ አለች።
ደግሞ በነገታው አንዲሁ. . .ኢትዮ-ቴሌኮም ምን ገጠመህ? ተብሎ ቢጠየቅ እኔ ‘ማውቀው ነገር የለም ሆነ ምላሹ። እንደው ክቡር ሚኒስትሩ ያውቁ ይሆን ቢባል ‘ኢትዮ-ቴሌኮም እንጂ እኛ ምን አገባን’ ነበር ለመገናኛ ብዙሃን የተሰጠው መልስ።
እርግጥ ሰዎች የኢንተርኔት መቋረጡ ከሃገር አቀፍ ፈተናዎች ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል [አምና፣ አቻምና የተከሰተውን ልብ ይሏል]፤ ይህ ግን መላ ምት እንጂ የተጨበጠ መረጃ አይደለም።
ሐሙስ ዕለት ከኢንተርኔቱ አልፎ አጭር የፅሑፍ መልዕክት አገልግሎት እንደተቋረጠ ተሰማ። ‘ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላማ እንዲህ ዓይነት ነገር አይታሰብም?’ ያሉ ሁኔታው ግራ አጋባቸው።
በጉጉት ስትጠበቅ የነበረችው ኢንተርኔት አርብ ጀምበር ልትጠልቅ ስታኮበኩብ ገደማ ብቅ አለች። አጭር የፅሑፍ መልዕክቱ ግን እንደቀለጠ ቀረ። አሁንም ቢሆንም የኢንተርኔት አገልግሎት ተመልሶ ያልመጣባቸው ሥፍራዎች እንዳሉ ይነገራል።
«ኢትዮ-ቴሌኮምን እከሳለሁ»
የሕግ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ እንየው በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር እና የዲጂታል መብት አማካሪ ናቸው። ከሰሞኑ በተፈጠረው ጉዳይ ኢትዮ-ቴሌኮም በሕግ ሊጠየቅ ይገባል ከሚሉ ሰዎች መካከል ናቸው።
«ኢንተርኔት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከመጡ ወዲህ እንኳ አራት ጊዜ ያክል ተቋርጧል። እርግጥ ጉዳዩ እንደ ቅንጦት ነው የሚታየው። በሕግ ባለሙያዎች አንድም አንገብጋቢ ከሚባሉ ጉዳዮች ተርታ አይመደብም። ወደሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ስትመጣ ግን መንግሥት መሰል ድርጊቶችን ሲፈጽም ይከሰሳል። ብሩንዲ ብትል፣ ታንዛኒያ ሆነ ኡጋንዳ ብትሄድ ኢንተርኔት ሲቋረጥ ይከሳሉ። እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን በቀላል አይልፏቸውም ሌሎች ሃገራት። እኛ ጋር ግን እንደ ቀልድ ነው የሚታየው፤ ማንም ተጠያቂ አይሆንም።»
እርግጥ አቶ ዮሐንስ እና ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች ጉዳዩ ውልብ ያለላቸው ከሰሞኑ ነው፤ ሂደቱም ገና ጅማሬ ላይ ነው። ቢሆንም እንደውም ሃሳቡን ማጫር በራሱ አንድ እርምጃ ነው ይላሉ ባለሙያው።
«እንደው ውይይቱን ብናስጀምረው ብለን ነው። በቀጣይ መንግሥትም ይሁን ኢትዮ-ቴሌኮም፤ አሁን ደግሞ ሌሎች ‘ኔትዎርክ ፕሮቫይደሮች’ እየመጡ ስለሆነ [ፕራይቬታይዝ እየተደረገ ስለሆነ] ወደፊት ለሚያጋጥሙ የተለያዩ ክስተቶች አላግባብ በሆነ መልኩ ከሕግ ውጭ መሰል ድርጊት እንዳይጸሙም ነው።»
ምን ተብሎ ይከሰሳል?
ባለፈው ሳምንት እንደ ፌስቡክና ትዊትር ያሉ ማህበራዊ ድር አምባዎች ጭር ብለው ነው የከረሙት [ዕድሜ ለኢንተርኔት መቋረጡ]። ከሃገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ግን ተቃውሟቸውን ‘በነፃነት’ ሲገልጹ ከርመዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም ተከሰሰ እንበል. . .በዋናነት ክሱ የሚሆነው ምንድን ነው? የመረጃ ነፃነት መግፈፍ? ተጠቃሚዎች ለገዙት ‘ዳታ’ ሳይጠቀሙበት መክሰሩ ነው? ግራ ያጋባል።
«እርግጥ ነው ኢንተርኔት መዘጋት ብዙ ችግር ፈጥሯል። ግን እኛ በዋናነት ከምንም በላይ የመናገር ነፃነት፤ ሁለተኛ ደግሞ መረጃ የማግኘት መብት ላይ ነው የምናተኩረው። ምናልባት ሌሎችም ክሱን ፋይል ስናደርግ የሚቀላቀሉን ካሉ ያስከተለውን ኪሳራን ልናካታት እንችላለን። ለምሳሌ አንድ ሪፖርት ኢንተርኔት መቋረጥ ሃገሪቱን 4.5 ሚሊዮን ዶላር በቀን ያሳጣታል ይላል። ይህ ማለት የማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ መብቶችንም ይነካል ማለት ነው።»
«የተደራጁ ማህበራት ቢኖሩን. . .» ይላሉ አቶ ዮሐንስ፤ «የተደራጁ ማህበራት ቢኖሩን ክሱ በተነፃፃሪ ቀላል ይሆን ነበር። ለምሳሌ የብሎገሮች [ጦማሪያን] ማህበር ቢኖር በኢንትርኔት መቋረጡ የደረሰባቸውን ተፅዕኖ አስረድቶ ክስ ማቅረብ ይቻላል። ሌሎችም አሁን ስማቸውን መጥቀስ የማያስፈልግ ማህበራት እና የግል ተቋማትም ይመለከታቸዋል።»
እርግጥ ነው ቴሌ ቢከሰስ የክሱ ፋይል በርካታ ወረቀቶች እንደሚፈጅ ይታሰባል። ከምጣኔ ሃብት፣ ከማህበራዊ ትስስር፣ እና ከሰብአዊ መብት ጥሰት አንፃር ጉዳዩን ማየት ይቻላልና።
• ኢትዮ-ቴሌኮም፡ አንድ ወደፊት ሁለት ወደኋላ?
ምናባዊ ክስ
ኢትዮ-ቴሌኮምን የመክሰስ ሂደቱ ገና እንጭጭ ቢሆንም፤ ሃሳቡ ግን መንሸራሸር ጀምሯል። ድርጅቱ ከሰሞኑ ለፈፀመው ድርጊት በፍርድ አደባባይ ሊቆም እንደሚገባ በርካታ የሕግ ሰዎች ይስማማሉ።
‘ኢትየ-ቴሌኮም ሊከሰስ እንደሆነ ሰምተው ይሆን?’ ብለን የጠይቅናቸው ታዋቂው የሕግ ሰው አቶ አምሃ መኮንን «እርግጥ ጉዳዩ ለእኔ አዲስ ነው ግን ኢትዮ-ቴሌኮም መከሰስ እንዳለበት አምናለሁ» የሚል ምላሽ ነበር የሰጡን።
እስቲ ክሱ ፋይል ተደረገ እንበል። የፍርድ ቤት ምላሽ ምን ይሆናል ብላችሁ ታስባላችሁ? ለሕግ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ያቀረብነው ጥያቄ።
«ፍርድ ቤቱ ሥልጣን የለኝም ሊለን ይችላል። ጥቅም የላችሁም ሊል ይችላል። በፍትሀ-ብሔር ጉዳይ ወይንም በሕዝብ ጥቅም ጉዳይ አንድ ክስ ሲቀርብ ጥቅም ሊኖር ይገባል። ጥቅም የሚባለው የንብረት ወይንም መብት ማስከበር ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን አሁን እኛ የምናቀርበው ‘ስትራቴጂክ ሊቲጌሽን’ [ሰብዓዊ መብትን ለማስከበር የሚቀርብ ክስ] ስለሆነ የሕዝብ ጥቅም ጉዳይ ነው። ሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 37 ላይ ፍትህ የማግኘት መብት የሚለውን መሠረት አድርገን ነው ክሱን ለማቅረብ የምንሞክረው።»
ክሱ ተሳካም አልተሳካ፤ ፍርዱ የሕግ ባለሙያዎቹ የሚሹት ሆነም አልሆነ፤ አንድ ጉዳይ ግን ግልፅ ይመስላል። ሰማይ አይታረስም ንጉሥ አይከሰስ ተደርምሶ፤ ሰማይ ባይታረስ ንጉሥ ግን ይከሰስ ሆናል። ንጉሡ ኢትዮ-ቴሌኮም መሆኑ ነው እንግዲህ።