June 18, 2019

Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት (ዩኤንዲፒ) በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የዴሞክራሲ ተግባራትን ለመደገፍ የሚያገልግል የ40 ሚሊየን ዶላር ዕርዳታ ሰጠ፡፡

የገንዘብ ሚንስትር አቶ አህመድ ሽዴ ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እና የዩኤንዲፒ ሃላፊዎች በተገኙበት ስምምነት ተደርጓል፡፡

ድጋፉ በቀጣይ ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ አቅምን ለማሳደግ፣ግልፅ፣ፍትሐዊና ተዓማኒ ተቋም እንዲሆን ለማድረግ ያግዛል፡፡

የገንዘብ ሚንስትር አቶ አህመድ ሽዴ እንዳሉት ባለፈው ዓመት በኢትዮጲያ የመጣው ለውጥ ዴሞክራሲ እንዲያብብ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋና ሁሉንም በእኩልነት የሚያገለግል ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው በቀጣይ የሚደረገው ምርጫ ባለፋት ምርጫዎች የታዩ ችግሮችን በማረም፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋትና አሰራሮችን በማሻሻል ከዚህ በፊት ከተደረጉ ምርጫዎች የተሻለ ትርጉም ያለው ለማድረግ የተገኘው ገንዘብ ያግዛል ብለዋል፡፡

ድጋፋን የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅትና አስራ አንድ የተለያዩ ሀገራት በጋራ እንዳደረጉት ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡