https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=442742289856920&id=100023634581032
ዳር ልንቆም አይገባንም

የተወደዳችሁ ወገኖቼ! የትውልድ ዘመን ተጋሪዎቼና ከእኛ በኋላ የተከተላችሁ ሁሉ፤ በዚህች መዳረሻዋ ባልለየላት፣ እንደሀገር በመቀጠልና ባለመቀጠል መስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኝ ሀገር ዜጎች ሁሉ በምንም መመዘኛ ቢሆን ዳር ቆመን ልንመለከት አይገባንም።የትውልድ ዘመን ተጋሪዎቼ ያለምንም ማጋነን ከራሳችን በላይ ለኢትዮጵያንና ለሕዝቧ አስበን ወደተሻለ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እናሻግራለን ብለን ታላቅ ዓላማ ይዘን የተነሳን ነበርን። ብዙዎች ዓላማቸውን ከግብ እንድናደርስና አደራ እየተዉልን የተሰዉብንና መቼም ቢሆን ልንረሳቸው የማይቻለንን ድንቅ የኢትዮጵያን ልጆች ከጎናችን ያጣን ነን። የቃል ዕዳ ያለብን፤ የኒያ ታጋዮች ድምጽ ሁሌም በጆሮአችን የሚጮህብን ሰዎች። ይዘናቸው የተነሳናቸው ጥያቄዎች (ሕዝባዊ መንግሥት፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነትና ፍትሕ…) ዛሬም ያልተመለሱባት አገር ውስጥ የምንኖር። ከምንጊዜውም በከፋ ሁኔታ ዜጎች በአገራቸው ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው የሚፈናቀሉባትና የሚሞቱባት፤ ዜጎች ያለምንም ዝግጅት “በሕገወጥነት” ስም ቤታቸው የሚፈርስባትና በላስቲክ መጠለያ ውስጥ በጋና ክርምትን እንዲያሳልፉ የሚገደዱባት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን በማንነት ላይ በተመሰረተ ግጭት እርስ በእርስ የሚገዳደሉባት፣ ጥቂቶች በስርቆትና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚበለጽጉባት ብዙኃኑ አስከፊ የድህነት ሕይወት የሚገፉባትና ልጆቿ በየጎዳናው የወደቁባት፣ ጀንበር በወጣች ቁጥር የሚጨምር በሚመስል የኑሮ ውድነት የሚፈተን ሕዝን ያላት… ሀገር ውስጥ እየኖርን የእኒያን ሰማዕታት ጩኸት አንሰማም ብለን የመኖር የሞራል ብቃት አይኖረንም፤ በመሃላችን ያሉ ጥቃቅን ቅራኔዎች ከኢትዮጵያና ከሕዝቡ አይበልጡምና ተለያይተን እንድንቆም ምክንያት ሊሆኑን አይገባም። ከእኛ ጋር የዓላማ አንድነት የሌላቸው ወገኖች እንደሚቀቡን ጥላሸት ሳይሆን ያለፈውን የፖእቲካ ትርክት በሚገባ ፈትሸን በእኛ ምክንያትነት የተከሰቱ አገራዊ ችግሮች ቢኖሩ ይቅርታ በሚያስጠይቁት አገርንና ሕዝብን ይቅርታ ጠይቀን አንገት የማያስደፋ የማንነታችንን ታሪክ ለሕዝብ የማሳወቅ ግዴታችንን በመወጣት እኒያ ሕይወታቸውን የከፈሉ ሰማዕታት የሚገባቸውን ታሪካዊ ቦታ እንዲያገኙ ማድረግም ይኖርብናል። በዚህ አያበቃም፤ ዛሬ በተፈጠረው የተሻለ ፖለቲካዊ ሁኔታ  ውስጥ የጓዶቻችንን ትግል በሰላማዊ መንገድ የማስቀጠል የውዴታ ግዴታ ተጭኖናልና ትልቁን ስእል ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ተመልክተን የልቦቻችን ዝማሬ የሆነውን ለሀገርና ለሕዝብ የመቆም ዓላማ በተባበረ ክንዳችን እናንሳ! በምንም መመዘኛ በኢትዮጵያ ጉዳይ ዳር ልንቆም አይገባንም!

ከእኔ ትውልድ በኋላ የተፈጠራችሁ ጎልማሶችና ወጣቶች! ለእናንተም ቢሆን በዚህች አገር ላይ የተፈጠረውን ክፋት ሁሉ በቀደማችሁ ትውልድ ላይ ጭናችሁ ለዘመናት እያወገዙ መኖር መፍትሔ ሊሆን እንዳልቻለ አይታችሁታል። አንድ ቦታ ላይ የተጫነባችሁን ስነልቡናዊ ሸክም አሽቀንጥራችሁ በመጣል ትክክል ነው የምትሉትን መፍትሔ የመሻት ግዴታ አለባችሁ። መንስኤው ምንም ይሁን ምን ይህ ትውልድም ለሀገሪቱ በዚህ ሁኔታ መገኘት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም መዘንጋት ትክክል አይሆንም። የቀደማችሁ ትውልድ ያለምንም ተሞክሮ ለሀገሩ መልካም ለመሥራት ሲል የወቅቱን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ተከትሎ የተሳሳታቸው ስህተቶች ቢኖሩትም በእጅጉ ሚዛን የሚደፉ መልካም ተግባራት እንዳሉትም መካድ አይቻልም። ላለፉት በርካታ አስርተ ዓመታትም ሳይታክት ሀገሩን ከገባችበት ችግር ለማውጣት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ በተለያዩ መንገዶች ሲታገልም ቆይቷል። ዛሬም ኑ! እንነጋገር፣ ሀገራችንንም እንታደግ እያለ ይገኛልና ይህን ጥሪ ተቀብለው ሀገርን በመታደግ ሰላማዊ ትግል ውስጥ እጅ ለእጅ ተያይዘው ለመጓዝ ቁርጠኝነት ያሳዩትን የእድሜ ተጋሪዎቻችሁን ፈለግ ተከትላችሁ፤ ትናንትን ሳንዘነጋ ዛሬን በአግባቡ እየኖርን ለነገዋ  ለኢትዮጵያ ሰላምና ለሕዝቧም ነጻነትና እኩልነት አብረን እንሥራ።ውጤታማ ለመሆን ደግሞ መደራጀት ግድ ነው፤ ፓርቲዎች በሌሉበት ዲሞክራሲን ዕውን ማድረግ ስለማይቻል ጠንካራ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ። ጠንካራና ተፎካካሪ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ለመፍጠር ደግሞ በማንነት ላይ በተመሰረቱ በርካታ ድርጅቶች ውስጥ ከመበታተን በማንነታችን ተከባብረን የጋራ አጀንዳችንን ሊያስተናግዱ በሚችሉ ድርጅቶች ውስጥ መሳተፍ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው። ያኔና ያኔ ብቻ የሕዝቧ እኩልነት የሚረጋገጥባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ ይቻላል። ማንነት ሳይሆን ሀሳብ የሚታይበት፣ በመነጋገር ላይ የተመሠረተ በሀሳብ የበላይነት የሚመራ ሰፊና የሰለጠነ ፖለቲካዊ ምህዳር ለመፍጠር ሁላችን ኃላፊነት አለብን። ሁሉ ሕዝብ ፖለቲከኛ ባይሆንም የሚደግፈውንና የሚቃወመውን በትክክል የተገነዘበ ሕዝብ መሆንም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም። ማናችንም ብንሆን አያገባኝም ብለን ዳር ልንቆም አይገባንም።

ኢትዮጵያ በልጆቿ መከባበርና አንድነት ለዘለዓለም ትኖራለች!

እግዚአብሔርም ይባርካታል!