
ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ባህር ዳር ውስጥ የተከሰተው ነገር ለብዙዎች ያልተጠበቀ ነበር። ድንገት ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድሩ ቢሮ አካባቢ የተሰማው ተኩስ ለሰአታት ቀጥሎ ከተማዋን ያደናገጠ ሲሆን፤ ምን እንደተከሰተ ሳይታወቅ ቆይቶ የተኩስ ልውውጡ በሌሎች አካባቢዎችም አጋጥሟል።
የተኩሱ ምክንያት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መሆኑ በፌደራል መንግሥት ከተነገረ በኋላ እንደ ባህር ዳሩ ከባድ ባይሆንም አዲስ አበባ ውስጥ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ መኖሪያ ቤት አካባቢም ተኩስ ተሰምቶ ነበር።
• ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን መገደላቸው ተነገረ
• የሰኔ 16ቱ ጥቃትና ብዙም ያልተነገረላቸው ክስተቶች
በሁለቱ ከተሞች የተከሰተው ነገር በተቀራራቢ ጊዜ ያጋጠመ መሆኑ ደግሞ ምናልባት ተዛማጅ ጉዳዮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲጠረጠር ነበር። ቅዳሜና ዕሁድ ምን ተከሰተ? ስለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውና ስለግድያው እስካሁን የምናውቃቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
ባህር ዳር
ቅዳሜ ሰኔ 16/2011 ዓ.ም
- ከሰዓት በኋላ በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ከፍተኛ የክልሉ ባለስልጣናት ለስብሰባ ተቀምጠው ነበር።
- አመሻሽ ላይ የክልሉ ጸጥታ ተቋም ውስጥ ካሉ ኃላፊዎች መካከል ናቸው የተባሉ ሰዎች ወደ ስብሰባ ስፍራ በመግባት ጥቃት ፈጸሙ።
- በጥቃቱም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ ቁጥራቸው ያልተገለጸ ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ።
- ይህንንም ተከትሎ በባሕር ዳር ከተማ የተለያዩ ስፍራዎች የተኩስ ልውውጦች ተደረጉ።
- ምሽት አንድ ሰዓት ሊሆን ሲል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው በክልሉ አመራሮች ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መደረጉን ይፋ አደረጉ።
- በባህር ዳር ከተማና በዙሪያዋ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ክስተቱን ለመቆጣጠር መሰማራታቸው ተነገረ።
- ከባድ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ጋብ ያለ ቢሆንም ምሽቱን አልፎ አልፎ ተኩስ ይሰማ ነበር።
- ምሽት ከአምስት ሰዓት በኋላ የክልሉ ገዢ ፓርቲ አዴፓ በብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ የተመራ ክልላዊ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መደረጉን አሳወቀ።
አዲስ አበባ
ቅዳሜ ሰኔ 16/2011 ዓ.ም
- ምሽት ሁለት ሰዓት ከመሆኑ በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሙ ላይ የግድያ ሙከራ መደረጉን የሚያመለክቱ መረጃዎች መውጣት ጀመሩ።
- በከተማዋ ውስጥም የተኩስ ድምጽ መሰማቱን ነዋሪዎች ሲገልጹ፤ የአሜሪካ ኤምባሲም ለሰራተኞቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ሰጠ።
- በአዲስ አበባ መግቢያና መውጫዎች እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች ከሌላው ጊዜ በተለየ በስፋት ተሰማርተው ቁጥጥር ማድረግ ጀመሩ።
- በአዲስ አበባና በአካባቢዋ ሊካሄዱ የነበሩ የተለያዩ ሕዝብን አሳታፊ ዝግጅቶች እንደተሰረዙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሳወቀ።
- ከዕኩለ ሌሊት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በወታደራዊ የደንብ ልብስ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው በአማራ ክልል የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መደረጉንና በጄኔራል ሰዓረ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አረጋገጡ።
ዕሁድ ሰኔ 17/2011 ዓ.ም
- ጠዋት የትግራይ ክልል መገናኛ መገናኛ ብዙሃንና ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙና ጄነራል ገዛኢ ህይወታቸው ማለፉን አመልክቶ የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰማውን ሃዘን ገለጸ።
- የአማራ ክልል መንግሥትም በተፈጸመው ጥቃት ርዕሰ መስተዳድሩና አማካሪያቸው ሲገደሉ ሌሎች ባለስልጣናት መቁሰላቸው ተነገረ።
- የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በባህር ዳርና በአዲስ አበባ በተፈጸሙ ጥቃቶች አራት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደተገደሉ ይፋ ሆነ።
- ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በተሰጠ መግለጫም ሁለቱ ጄነራሎች የተገደሉት በኤታማዦር ሹሙ ጠባቂ እንደሆነና ገዳዩም መያዙ ተገለጸ።
- አቶ ላቀ አያሌው የተገደሉትን ዶ/ር አምባቸው መኮንንን መንበር ተክተው ጊዜያዊ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር መሆናቸው ተነገረ።
- የተለያዩ ክልሎችም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውንና ግድያውን አወገዙ።
የመከላከያ ሠራዊት በባህር ዳር ከተማ ከተሰማራ በኋላ ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ፈጻሚዎች ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ እንዳሉና ያልተያዙ ሰዎች እንዳሉም እየተገለጸ ነው።
የአማራ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ላቀ አያሌው ለክልሉ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ እንዳልተያዙና እየተፈለጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ውስጥ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡና ላይ በሌላ ጄነራል ላይ ጥቃት የፈጸመው ጠባቂ መያዙ የተገለጸ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሊት ላይ በሰጡት መግለጫ በድርጊቱ እጃቸው ያለበት በሙሉ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።