June 23, 2019

June 23 2019

የትላንቱ ቀን በጣም የሚያሳዝን ቀን ነው። ለሞቱት ነፍስ ይማር ፣ ለወዳጅ ዘመድም መጽናናቱን ይስጥልን እላለሁ። ከነ ዶ/ር አምባቸውና ጀነራል ሰአረ መኮንን በተጨማሪም ስማቸው የተጠቀሰ ያልተጠቀሰም ብዙ ሞተዋል። ጀነራል አሳምነውንም ገድለዉታልም ይባላል። ያ ሁሉ መሆን አልነበረበት ፣ ግን ሆኗል።

እግዚአብሄርን የተመሰገነ ይሁን፣ ዛሬ ነገሮች ተረጋግተው ነው የዋሉት። የፈሰሰ ደም ስለመኖሩ የሰማነው ነገር የለም።

ሆኖም ትላንት ለተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት፣ በመመሪያ በተደረገ መልኩ፣ በዘመቻ ጀነራል አሳምነው ጽጌንና አንድ ወገንን፣ demonize የማድረግ፣ የመክሰስ፣ የመወንጀል እንቅስቃሴ እያየን ነው።  በጀነራል አበበ ጁላ የሚመራው የፌዴራል ጦር የአማራ ክልልን ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል ተቆጣጥሯል። አዴፓ ውስጥ በነበሩ አለመስማማቶችና ግብግቦች አፍቃሪ ኦዴፓ የሚባለው አንጃ፣ በመከላከያ ሰራዊት ታግዞ የበላይነቱን በባህር ዳር የያዘ ይመስላል። በክልሉ ያሉ ፣ የክልሉ የጸጥታ ሃላፊዎች እነ ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ኮሎኔል አለበል የመሳሰሉት በሙሉ እንደታሰሩ እየሰማን ነው። ይሄው አንጃም ለተፈጠረው ቀውስ በመግለጫ ጀነራል አሳምነው ጽጌ እንደመሩት አድርጎ እየለፈፈ ነው። ልክ በደርግ ጊዜ መንግስቱ ሃይለማሪያም እነ ኮሎነል አጥናፉ አባተን ካስረሸነ በኋላ “ከሃዲው አጥናፉ አባተ” እያለ ነጋሪት ሲያስጎስም እንደነበረው፣ አሁንም በጀነራል አሳምነው ጽጌ ላይ ተመሳሳይ ነገር አያየን ነው። የራስን ጉድ ሸፍኖ ሌላው ላይ ብቻ ማላከክ።

ጀነራል አሳምነው ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ የሚታወቅ ነገር የለም። ተይዘዋል፣ ተተኩሶባቸው ቆስለዋል፣ ተገድለዋል ..የሚሉ መረጃዎችን እየሰማን ነው። የኦዴፓው አዴፓ፣ “ጀነራል አሳምነው አምልጠዋል” የሚል መግለጫም ሰጥቷል። የሕዝብን ቁጣ ለማብረድ። በኔ እይታ የጀነራሉን ሁኔታ በጭራሽ ላናውቅ እንችላለን የሚል ስጋት አለኝ።

ጀነራል አሳምነው፣ በተለይም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ልዩ ፖሊሶች ካስመረቁ በኋላ በአራት ኪሎና በኦህዴዶች አካባቢ ምቾት እንዳልፈጠሩ የሚታወቅ ነው፡፡

በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በየትም ክልል ሚሊሺያ መኖሩ ለአገር አንድነት አስጊ ነው። በተለይም በአገራችን ያሉ ክልሎች በዘር ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው። ሆኖም አንድ ነገር ለአንዱ ጥሩ ሆኖ ለሌላው ግን መጥፎ ተደርጎ ማየት አድሎአዎነት ነው። ኦሮሞ ክልልና ትግራይ እንድ ጽድቅ ተቆጥሮ አማራ ክልል እንደ ሐጢያት መቁጠር ግብዝነት ነው።

በኦሮሞ ክልል ሕዝብንና ሌሎች ማህበረሰባትን የሚያሸብሩ፣ ባንክ የሚዘርፉ፣ ዜጎችን የሚያፈናቅሉ ታጣቂዎች ፣ የኦነግ/ኦዴፓ ካድሬዎች፣ ጽንፈኛ ቄሮዎችና፣ በትግራይ ክልል ደግሞ በራያና በወልቃይት እንዲሁም በትግራይ ዜጎችን የሚያሰሩና የሚገድሉ፣ ከሕግ በላይ የሆኑት የትግራይ ልዩ ፖሊሶችን ፣ መኖራቸው ያላሳሰባቸው፣ እነርሱም ላይ እርምጃዎች ለመዉሰድና የመከላከያ ሰራዊት ለማሰማራት ያመነቱት፣ አራት ኪሎ ያሉ የኦህዴድ ባለስልጣናት፣ በአማራ ክልል ያሉ ሚሊሺያዎችን ብቻ እንደ ስጋት መቁጠራቸው ትልቅ ስህተት ነው። አላማቸው ለአገር ከማሰብ የተነሳ ሳይሆን ፣ ላለፉት 27 አመታት እንደነበረው፣ አማራ የሚባለውን ማህበረሰብ ሆን ብሎ ለመምታትትና ለማዳከም እንደሆን አድርገው ሰዎች ቢያስቡ ሊያስደንቀን አይገባም።

በአማራ ክልል ሚሊሺያዊች ላይ እንዳደረጉት በኦሮሞ ክልልና በትግራይም ተመሳሳይ እርምጃ ካልወሰዱ፣ መከላከያ በሁሉም አገሪቷ የዜጎች ደህንነት ማስጠበቅ ካልቻለ፣ “አማራን አንገት ሊያስደፉ ነው፣ በአማራ ላይ ሆን ተብሎ የተዶለተ ስራ ነው” የሚል አስተያየት ቢሰጥ ትክክል አይደለም ማለት አይቻልም።

ከአንድ አመት በፊት የታላቁ የኢትዮጵያ ልጅ የኢንጂነር ስመኝም ግድያ ተመልክቶ ኦህዴዶች የሚቆጣጣሩት የፌዴራል መንግስት ያወጣዉን የዉሸት ሪፖርት ሁላችንም የምናስታወሰው ነው። በተመሳሳይ ሁኔታም እነርሱ አድራጊ፣ እነርሱ ፈራጅ፣ እነርሱ መግለጫ ሰጪ፣ እነርሱ አጣሪ ሆነው የሚናገሩትን አሁን ማመን አስቸጋሪ ነው።

በመሆኑም ከመንግስት ነጻ የሆነ ገለልተኛ ኮሚሽን ተቋቁሞ፣ በአዲስ አበባና በባህር ዳርም የሆነውን ሁሉ እንዲያጣራ መደረግ አለበት። በዚህ ሂደት ጀነራል አሳምነውም ሆነ ሌሎች በመረጃ ላይ ተመርኩዞ ጥፋተኛ ከተባሉ ተገቢዉን ቅጣት መቀበላቸውን የሚቃወም ይኖራል ብዬ አላስብም።

ያ እስኪሆን ድረስ የኦዴፓ አገዛዛ ባለስልጣናት (ባህር ዳር ያሉትም) ጀነራል አሳምነው ላይ የሚያቀርቡትን መሰረተ ቢስ ክስ፣ መፈንቀለ መንግስት የሚሉትን አባባል በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እጠይቃለሁ። ጀነራል አሳምነው አመለጠ የሚሉትን ቀልድም እዚያው ያድርጉት። ያ ሁሉ ፌዴራል እያለ፣ ትንሽ በሆነችው ባህር ዳር ከተማ ጀነራል አሳምነው የትም ሊሄድ አይችልም። ወይ አስረዉታል፤ አሊያም ገድለዉታል። እንደውም ሳይገድሉት አልቀረም የሚል ያልተረጋገጠ መረጃ ነው እየደረሰኝ ያለው። አስረዉት ከሆነ በስቸኳይ በገለልተኛ አካላት ፣ በቤተሰብ መጠየቅ አለበት። ገድለዉትም ከሆነ አስክሬኑን ለቤተሰብ ማስረከብ አለባቸው። እንዳይታወቃባቸው ብለው ይሄን ትልቅ ሰው የትም የሚቀብሩት ከሆነ ግን ከወያኔ አስር እጥፍ ጭራቆች መሆናቸው አስመሰከሩ ማለት ነው።