24 ጁን 2019

የሃገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንንና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ጄነራል ገዛኢ አበራን ተኩሶ ገደለ የተባለው የጄነራል ሰዓረ ጠባቂ ራሱን ያጠፋው ወዲያው መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ዛሬ በሰጡት መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል።
ሰኞ ምሽት ፌደራል ፖሊስ በብሔራዊው ቴሌቪዥን (ኢቢሲ) ቀደም ሲል ራሱ የሰጠውን መግለጫ አስተባብሎ ጠባቂው በሕይወት እንደሚገኝ አስታውቋል።
ቢቢሲ ማክሰኞ ጠዋት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት እንደሻው ጣሰው ጋር በመደወል ትናንት በሰጡት መግለጫ እና ማታ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በቀረበው መግለጫ መካከል ስለተፈጠረው ልዩነት ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋቸው ነበር።
ኮሚሽነሩ በአጭሩ “በአጭሩ ልጁ ተመትቷል። ከፍተኛ ህክምናና ክትትል የሚደረግበት ክፍል ውስጥ ነው ያለው። እኛ የወሰድነው መረጃ ሞቷል የሚል ነበር። አሁን ግን በሕይወት አለ። በመሞትና በሕይወት መካከል ነው የሚገኘው” ብለዋል።
ዕሁድ ስለጥቃት ፈጻሚው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢሮ በተሰጠ መግለጫ ጠባቂያቸው ቆስሎ መያዙ ቢገለፅም ሰኞ ጠዋት በተሰጠው የፌደራል ፖሊስ መግለጫ ላይ ግን ወዲያውኑ ራሱን ማጥፋቱ ተነግሮ ነበር። ሆኖም ማምሻውን ፌዴራል ፖሊስ ይህንኑ መግለጫ በድጋሚ አስተባብሏል።
• ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ያሉበት እንደማይታወቅ የአማራ ክልል ገለፀ
በጠዋቱ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ገለፃ መሰረት በወቅቱ ከጄኔራሎቹ ጋር የነበረው ጠባቂ ሁለቱንም ተኩሶ የገደላቸው ሲሆን፤ በቦታው የነበሩ ሌሎች ጠባቂዎች በጥቃት ፈጻሚው ላይ ቢተኩሱበትም ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበትና ግለሰቡም ወደነበረበት ክፍል ተመልሶ በመግባት ራሱን ማጥፋቱን ኮሚሽነሩ ገልፀው ነበር።
“ጠባቂው በጄኔራል አሳምነው የተመለመለ ሲሆን፤ ራሱን ማጥፋቱ የሚያሳየው የተሰጠው ተልዕኮ ከፍተኛ ግዳጅን የሚጠይቅ መሆኑን ነው። ይህም የአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮ ነው” ብለዋል ኮሚሽነሩ በመጀመርያው መግለጫ።
• ስለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውና ስለግድያው እስካሁን የምናውቀው
ኮሚሽነሩ ባህርዳር ተፈጸመ ከተባለው “የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ” በፊት ብርጋዲየር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ የክልሉ ፀጥታ ኃላፊዎችን በየቢሯቸው አስረዋቸው እንደነበርም አብራርተው ነበር። ኮሚሽነሩ አክለውም በብርጋዲየር ጄኔራል አሳምነው ስር ያሉ ሰዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።