
አቶ ቹቹ አለባቸው ከጥቂት አመታት በፊት ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እስከተለያዩበት ጊዜ ድረስ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ነበሩ። የሟች ዶ/ር አምባቸው መኮንንም የቅርብ ጓደኛ ነበሩ። ቢቢሲ በአዴፓ ውስት አሉ ስለሚባሉ ልዩነቶች አነጋግሯቸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ) ውስጥ ልዩነቶች እየጎሉ መጥተዋል፤ መካረሮችም ነበሩ ይባል ነበር?
አቶ ቹቹ፡ ቆይቷል፤ ከአንድ ዓመት በላይ ይሆነዋል። የድርጅቱ ባህሪ እየተቀየረ አንድ ቡድን የበላይነቱን ይዞ ለመውጣት የሚያደርገው ትግል (እኔ የዚያ አካል ስለነበርኩ ነው የምነግርሽ)። ቀድሞ መካረርም ቢኖር ድርጅቱ ወደዚህ ደረጃ የሚያመራ ባህል አልነበረውም። በተለይም ባለፉት አንድ ሁለት አመታት እንደዚህ ያለው የስልጣን ሽኩቻና ፍትጊያ እንዲሁም በጎጥና በአካባቢ መሿሿም ከባድ ችግር ነበር።
ልዩነቱና መካረሩ ምን ሀሳብ በሚያራምዱና ምን በሚፈልጉ መካከል የተፈጠረ ነው?
አቶ ቹቹ፡ ዋነኛው ጉዳይ ከህወሓት ጋር ያለ የግንኙነት ችግርን የመፍታትና ያለመፍታት ጉዳይ ነው። አንዱ ቡድን በተለይ እነ አምባቸው ፤ የለውጥ ኃይል የሚባለው ችግር መኖሩን አምኖ፣ ችግሩን የምንፈታው ግን በውይይትና በድርድር፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ነው የሚል አለ። ቀደም ሲል የነበሩት፣ የተወገደው የነበረከት ቡድን የሚባለው ደግሞ የአማራን ሕዝብ ጥቅም አሳልፎ የሰጠ የሚል ከፍተኛ ክስ ነበረበት። አሁን ነገሩ የተባባሰው ግን ለውጡን ተከትሎ ምህረት ተደርጎላቸው ከስር የተፈቱት ወደ ድርጅቱ እንደገና እንዲቀላቀሉ ሲደረግ ነው። እኒህ ኃይሎች ነገሮችን በሚዛኑ ካለው አመራር ጋር ተጣጥሞ መሄድ አልቻሉም። ብሶቱ፣ ቁጭቱ አለ። የአማራን ሕዝብ በደልን በስፋት ያነሳሉ። ወጣቱ በስሜት ይከተላል። ማስተዋል፣ መምከር ላይ በጣም ከፍተኛ ችግር አለ። በእነዚህ ጉዳዮች ትንሽ ልምድ ያለው ነባሩ አመራር ጉዳዩን በተረጋጋ መልኩ መፍታት ይፈልጋል። ይሄኛው ኃይል ደግሞ አሁንም ብአዴንን [የአሁኑ አዴፓ] የህወሃት ተላላኪ ነው፣ የአማራን ሕዝብ ጥየቄ አይመልስም የሚል ጫፍ የወጣ ነገር እየያዘ ሄደ። ሁለቱም ላይ መካረሮች ተከስተዋል።
• በሃየሎም ይምሉ የነበሩት ጄነራል ሰዓረ መኮንን ማን ናቸው?
መካረሮቹ ምን ደርሰው ነበር?
አቶ ቹቹ፡ እዚህ ላይ እንደሚደረስ ለድርጅቱ አመራሮች በፅሁፍ፣ በግል፣ በአካል አግኝቼ ተናግሬአለሁ።ነገር ግን አብሮ ማደግ ችግር ነው፤ ያጣጥሉታል። አካሄዱ እንዳለ እዚህ ደረጃ ላይ ሊደረስ እንደሚችል የሚያሳይ ነበር። ከውስጥ የምናገኘው መረጃም ስለነበር አንድ ሁለት ሶስት ብለን ነግረናቸዋል። የኢህአፓና መኢሶን ነገር አማራ ክልል ላይ ሊከሰት ይችላል ብዬ ተናግሬ ነበር። ከጥቂት ቀናት በፊት የድርጅቱ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዮሃንስ ቧያለውን አግኝቼ ነግሬዋለሁ። “ይሄ የሚባል ሰው ይሄን ክልል ያፈርሰዋል ብዬ ተናግሬአለሁ”
“ይሄ ሰው” የሚሉት ማንን ነበር?
አቶ ቹቹ፡ ከጀነራሉ ጋር አይደል መካረር የደረሰው፤ ግን ከእሱ ጋር ብቻም ሳይሆን ሌሎችም አሉ። የመድረክ ንግግሮችን ተከታትለሽ ከሆነ መካረሮች ይታዩ ነበር እና ከዚህ ሰው ጋር ያለው ልዩነት ካልተፈታ ነገሩ ክልሉን ወደ ማፍረስ ይሄዳል ብለን ነበር። ለፕሬዘዳንቱም ነግሬው ነበር። የቅርብ ጓደኛዬ ነበር፤ በአንድ ወቅት ምክትሉም ነበርኩ። ከፌደራል ወደ ክልል እንዳይሄድ ተነጋግረን ተማምነን ቃል ገብቶልኝም ነበር።
• ስለ’መፈንቅለ መንግሥት’ ሙከራው እስካሁን የማናውቃቸው ነገሮች
ለምን ነበር የክልል ሹመት ተቀብለው እንዳይሄዱ የነገሯቸው?
አቶ ቹቹ፡ የማውቃቸው የማይመቹ ብዙ የተበላሹ ነገሮች ነበሩ። እዚህ ሚዲያ ላይ ላወጣቸው አልችልም። አልሄድም ብሎ ቃል ገብቶልኝ ከዚያ በኋላ ሳይነግረኝ መሾሙን ሰማሁ። በዚህ ተኮራርፈን ቆይተን በመጨረሻ ለአንድ ጉዳይ ከመሞቱ ሳምንት በፊት ተደዋወልን። ልንገናኝ ነበር ሳይመቻች፣ ሳንገናኝ በዚያው እንደተለያየን ቀረን።
ያደዋወላቹህና ሊያገናኛችሁ የነበረው ጉዳይስ ምን ነበር?
አቶ ቹቹ፡ በኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ጉዳይ አንዲት ስብሰባ ነበራቸውና ስለዚያ እንድንመካከር ፈልገው ነበር።
አሁን የተፈጠረው ነገር በፓርቲው ቀጣይ እርምጃ ላይ ምን ዓይነት ተፅእኖ ሊያሳድር ይችላል ብለው ይገምታሉ?
አቶ ቹቹ፡ ይህ ነገር መከራ ብቻም ሳይሆን ተስፋም ይዟል ብዬ አምናለሁ። ትንሽ ዋጋ ሊያስከፍለን ቢችልም ድርጅቱ ቆሞ ራሱን የሚገመግምበትና ራሱን የሚያስተካክልበት እድል ስለሚኖር። ብቁ መሪ ከተገኘ የበለጠ ጉልበት አግኝቶ ወደ ፊት ለመስፈንጠር አንድ እንድል አድርጎ መጠቀም የሚቻል ይመስለኛል።