ዐብይ አህመድ፣ ዐብይ አህመድ
ያህያ ሥጋ አልጋ ሲሉት ዐመድ፡፡
መስፍን አረጋ
መንደርደርያ
ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው፡፡ የዚህ ጦማር ዓላማ ደግሞ /መደመር/ የሚሰኘው ያብይ አህመድ /የመቀነስ/ ጎርፍ ጦቢያን ጠራርጎ ከመውሰዱ በፊት ጦቢያውያን እንዲገድቡት ለማሳሰብ ነው፡፡ እኔ እራሴ መስፍን አረጋ ይህ የዐብይ ጎርፍ እያሳሳቀ ከወሰደኝ አያሌ ጦቢያውያን ውስጥ አንዱ ነበርኩ፡፡ ጎርፉ ከማሳሳቅ አልፎ አጃጅሎኝ ስለነበር፣ ጎርፉን በማሞገስ የሚከተለውን መወድስ እስከመክተብ ደርሸ ነበር (የመጀመርያው ስንኝ ከሕዝብ የተወሰደ ነው)፡፡
ከጀታው ተላቆ ወደቀ ምሣሩ
ይሻለው ነበረ ተዋዶ መኖሩ፡፡
ብቻውን በቁሙ ስለማይኖረው ኃይል
ትንቆ ይኖራል ዝጎ እስከሚጣል፡፡
ጎጠኛ ማይም ነው ደንቆሮ የማያውቅ
ከክፍሎቹ ድምር ሙሉው እንደሚልቅ፡፡
ይህንን እውነታ ሲገልጥ አሳምሮ
መደመር ብሎታል ዐብይ ዘአጋሮ፡፡
የሥሁልን ሽንሽን ቴድሮስ እንደሰፋ
የመለስን ክልል ዐብይ አህመድ ያስፋ፡፡
ቴድሮስ ይሆናል ያልነው ዐብይ ዳግማዊ ሥሁል ሆነና አረፈው፡፡ ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ፡፡ ዐብይ ያበደ መሰለ፡፡ ያበደው ግን ዐብይ አህመድ ሳይሆን እኛው እራሳችን አገር ወዳድ ጦቢያውያን ነን፡፡ ገና በልጅነቱ ጫካ ገብቶ በፀረጦቢያው ወያኔ የጎጠኝነት መርዝ እየተጋተ አድጎ በወያኔ ቁንጮ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ሹም ለመሆን የበቃ ግለሰብ በድንገት ተነስቶ ስለመደመር ሲሰብክ፣ በመጠራጠር እንዴት ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ በሰበካው ደንዝዞ ቀልብ በማጣት ግለሰቡን ከነብይ መቁጠር እብደት እንጅ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡
ጦቢያዊነትን መቀመቅ በከተተው በወያኔ አንጀታችን የቆሰለው ጦቢያውያን፣ የጦቢያዊነትን ማንሰራራት ለማየት እጅግ ከመጓጓታችን የተነሳ የምናየው ለማየት የምንፈልገውን ብቻ ነው፡፡ ይህን ድክመታችንን በደንብ የሚያውቁት ፀረጦቢያ ኦነጋውያን (በተለይም ደግሞ ዐብይ አህመድና ለማ መገርሳ) ደግሞ በዚህ ድክመታችን በደንብ ገቡብን፡፡ ዐብይ አህመድ ስለ መደመር እየደሰኮረ ቀናሾችን አጠናከረ፡፡ ለማ መገርሳ በጦቢያ ሱስ እያታለለ፣ በኦነግ ጭስ አፈናቀለ፡፡ ሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም ደግሞ የኦነግን እኩይ ዓላማ ለማሳካት የመጨረሻው መጀመርያ የሆነውን ከፍተኛ ድል ዐብይ አህመድና ለማ መገርሳ ባሕርዳር ላይ ተጎናጸፉ፡፡
ዐብይ አህመድን በጽኑ የምቃወመው ባጀማመሩ ሳይሆን አካሄዱን አይቸ መዳረሻው በጽኑ ስላስፈራኝ ነው፡፡ የሚወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል፣ የማይወጣም እንደዚሁ፡፡ የዐብይ አህመድን ቅኔ ስንሰማ ወርቁን ሳንረዳ በሰሙ ብቻ ቀያኒውን (ማለትም ባለቅኔውን) ከሚገባው በላይ አሞገስን፡፡ ወርቁ መደመር ሳይሆን መቀነስ መሆኑን ስንረዳ ደግሞ በድንጋጤ በረገግን፡፡ የጦቢያ ጉዳይ ስለሚያስጨንቀን፣ የጦቢያን ስም በበጎ የሚጠራ ሁሉ በጎ የሚመኝላት እየመሰለን እንደበግ እየተነዳን ገደል ገባን፡፡ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል፣ እንደወለደች ገደል ይገባል፡፡
እርካብና መንበር
ባብይ አህመድ ንግግር ተማርከን ጀሌወቹ ከመሆናችን በፊት ያብይን የቀደመ ምንነት በተለይም ደግሞ ‹‹እርብና መንበር› በተሰኘው መጽሐፉ ገጽ 38 ላይ ‹‹ሰወች ራስ ወዳድ ናቸውና በጥቅም ሂድባቸው፡፡ የሚፈልጉትን ነገር እያሳየህ ወደሚፈልጉት ውሰዳቸውና ጣላቸው፡፡ ከዚህም ‹በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ› የሚባለውን ተረት ተርትባቸው›› ማለቱን በደንብ አጢነን ቢሆን ኖሮ፣ ጦቢያ፣ ጦቢያ የሚለው ወደ ኦሮሚያ ገደል እያታለለ ሊወስደን እንደነበር ግልጽ በሆነልንና ፋራህን ብላ ባልነው ነበር፡፡
በዚሁ መጽሐፉ፣ በዚሁ ገጽ ላይ ‹‹እንዳይመለስ ሁኖ ያልተሸኘ ጠላት ጊዜ ጠብቆ ዳግም ለማጥቃት እንድሚመጣ ጥርጥር የለውምና ሕልሙን ባንድ ጀንበር ማምከን መረሳት የለበትም›› ማለቱን አስተውለን ቢሆን ኖሮ፣ ዐብይ አህመድ ባንድ የሰኔ 15 ጀምበር የፈጸመውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ እንዲፈጽም እድል ባልሰጠነው ነበር፡፡ ይሄው ጥቅስ እንደሚያመለክተው ደግሞ አማራ እንዳይመለስ ሁኖ እስካልተሸኘ ድረስ የዐብይ አህመድ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ይቀጥላል፡፡ አማራ በልቶት እስከሚቀደስ ድረስ፣ የኦነግ ጅብ አማራ መብላቱን ይቀጥላል፡፡
እያወራረደ በዐብይ ጠላ
ብርሃኑ ጁላ ያማራን ልጅ በላ፡፡
ኤዶልፍ ሂትለር (Adolf Hitler) ‹‹ተጋድሎየ›› (Mein Kampf) በተሰኘው መጽሐፉ በግልጽ ያስቀመጠውን የወደፊት እቅዱን፣ አይሁዶች በደንብ አንብበው አስፈላጊውን እርምጃ አስቀድመው ባለመውሰዳቸው፣ ስድስት ሚሊዮን ወገኖቻቸውን ላረመነዌ የሂትለር ጦር ገበሩ፡፡ እኛ ጦቢያውያን ደግሞ የዐብይ አህመድን እርካብና መንበር በደንብ ባለማጤናችን፣ የሐገር መከላከያ ሽፋን እንዲላበስ ለተደረገው ለአረመኔው የኦነግ ጦር የገበርናቸውን፣ እየገበርናቸው ያለውንና ወደፊት የምንገብራቸውን አማሮች ቁጥር ‹‹እንዳይመለስ ሁኖ ያልተሸኘ ጠላት …› ከሚለው የዐብይ አህመድ ንግግር በቀላሉ መገመት ይቻላል፡፡
ያብይ አህመድ የመከላከያ ድቅረጻ
ዐብይ አህመድ የኦነግን እኩይ ዓላማ ለማሳካት ከሠራቸው ዐበይት ሥራወች ውስጥ ዋናው የመከላከያ ዳግም ቀረጻ ወይም ባጭሩ ድቅረጻ (reformation) በሚል ሽፋን የወያኔን ጦር በኦነግ ጦር (በተለይም ደግሞ አመራሩን) ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ የተካበት ሸፍጡ ነው፡፡
እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል ባለችው እንስሳ መርሕ የሚመራው ወያኔ የጦቢያን ሠርዶ እንዳሻው መጋጡ ስላከተመ ጦቢያ ብትሞት ዴንታ የለውም፡፡ ስለዚህም ኦነግ በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ የኦሮምያን አጼጌ (empire) ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ወያኔ ባይደግፈውም እንደማይቃወመው ወያኔ ጉያ ሥር ያደገው ዐብይ አህመድ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በመሆኑም ወያኔ የፈለገውን ያህል ልዩ ሃይል ቢያሰለጥንና የፈለገውን ዓይነት መሣርያ ቢታጠቅ ዐብይን ቅንጣት አያስጨንቀውም፡፡ እንደውም በተቃራኒው የዐብይ ፍላጎት ወያኔ በጦር ኃይል ይበልጥ ተደራጅቶ የኦነግን እኩይ ዓላማ የሚፋለመውን ጦቢያዊ (በተለይም ደግሞ ያማራውን) ሙሉ ትኩረት ይበልጥ እንዲስብለት ነው፡፡ ስለዚህም ወያኔ እንዲጠናከርና አማራ ደግሞ በዚያው ልክ እንዲዳከም የተቻለውን ያህል ይጥራል፡፡ የሰኔ 15ቱ የባሕርዳር ጭፍጨፋ የዚህ ጥረቱ ውጤት ነው፡፡
ጎጠኛው ወያኔ በለስ ቀንቶት ጦቢያን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር የመከላከያን ከፍተኛ አመራር ሙሉ በሙሉ የወያኔ ክበብ አደረገው፡፡ ዐብይ አህመድ ከወያኔ ሲረከብ ደግሞ የመከላከያን የወያኔ ክበብ በኦነግ ክበብ ተካው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በጦቢያ ውስጥ ወታደራዊ እውቀት (በተለይም ደግሞ የአመራር ክሂሎት) የሚኖራቸው ወያኔወችና ኦነጋውያን ብቻ ሲሆኑ፣ አገር ወዳዱ ጦቢያዊ (በተለይም ደግሞ አማራው) ግን በወታደራዊ ጥበብ የተካኑ ወታደራዊ መሪወች አይኖሩትም ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ፀረጦቢያው ኦነግ (ጦቢያውን ይገዳደሩኛል ብሎ ሳይሰጋ) ባሕር ዳር ላይ እንዳደረገው ያሻውን ሁሉ፣ ባሻው ጊዜ፣ ባሻው ቦታና፣ ባሻው ዘዴ የማድረግ ብቃት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ የዐብይ የመከላከያ ድቅረጻ ዋና ዓላማ ይሄና ይሄ ብቻ ነው፡፡ ጀነራል አሳምነው ጽጌ በኦነጋውያን ጥርስ የገባው ደግሞ የዐብይን የመከላከያ ድቅረጻ ዓላማ በመቀናቀኑ ነው፡፡ የኦሮምያ ክልል የሐገር መከላከያን የሚገዳደር ልዩ ኀይል አሰልጥኖ ሲያስመርቅ የዐብይን እቅድ እያሳካ በመሆኑ ይወደሳል፡፡ አሳምነው ጽጌ ተመሳሳይ ያማራ ኀይል ሲያደራጅ ግን ….
የዐብይ አህመድ ዓላማ ኦነግ የፈለገውን መሬት በመለጸቅ (annex) ወደ ኦሮሚያ ቢያጠቃልል፣ የፈለገውን አፈናቅሎ የፈለገውን ቢያሰፍር ሃይ ሊባል የማይቻል፣ በጉልበቱ የሚተማመን የማይጋፉት ባላጋራ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ዓላማው መሠረት ኦነግ የኔ ናቸው የሚላቸውን ሁሉ በጁ እስከሚያስገባ ድረስ የባሕርዳር ዕልቂት በሌሎች ያማራ ከተሞችም መደገም ብቻ ሳይሆን ይደጋገማል፡፡
ባጠቃላይ ደግሞ የዐብይ አህመድ ዓላማ፣ የባንኮች ባንክ የሆነውን ንግድ ባንክን በባቻ ጊና እየተቆጠጠረ፣ የጦቢያ የባህል፣ የፖለቲካና የምጣኔ ሐብት ሞተር የሆነችውን በራራን በታከለ ኡማ እያስተዳደረ፣ የማጥቃት ሠራዊቱን በለማ መገርሳ እየዘወረ፣ አልኦሮሞውን ደግሞ በሰላ አንደበቱ እያደናበረ፣ የኦነግን እኩይ ዓላማ ባጭር ጊዜ ውስጥ አሳክቶ በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ የኦሮምያን አጼጌ (empire) መገንባት ነው፡፡
በነገራችን ላይ አነግ ባንክ ስላልዘረፈ፣ ዘረፈ የሚሉት የዋሆች በሕግ የሚያስጠይቅ የስም ማጥፋት ጥፋት ፈጽመዋል፡፡ ኦነግ ባቻ ጊና በየጊዜው የሚልክለትን ከፍተኛ ገንዘብ በከፍተኛ አክብሮት ተቀበለ እንጅ አልዘረፈም፡፡ ይህ ዘዴ ደግሞ ወያኔ በሽፍትነቱ ዘመን ደጋግሞ የተጠቀመበት የተበላ ቁማር ነው፡፡
ዐብይ አህመድ እቅዱ ከተሳካለት በቅርብ ለምትፈርሰው ጦቢያ ዴንታ ስለሌለው፣ በጦቢያ ውጫዊ ገጽታ ላይ የሚያተኩረውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ማንም ይምራው ማን ዴንታ የለውም፡፡ አለያማ ጌታቸው አሰፋ ሁለት መቶ ሺ የኦሮሞ ወጣቶችን ባንድ ቀን ጀንበር ለማሠር ሲዝት አንድም ቃል ላልተነፈሰው ለቱርቂው ለማ መገርሳ መከላከያን ሰጥቶ፣ ጌታቸውን በግልጽ የተቃወመውን ገዱ አንዳርጋቸውን ውጭ ጉዳይ ባልወረወረው ነበር፡፡ ገዱ ውጭ ውጩን ሲባጅ፣ ዐብይ ውስጥ ውስጡን ያበጅና በሩን ይዘጋበታል፡፡ ባሕር ዳር ላይ ያደረገውም ይህንኑ ነው፡፡
ሲጥል እንጅ ሲታገል አይታይም የሚባለው ገዱ አንዳርጋቸው፣ ጭምትነቱ ትዕቢተኛውን ወያኔን ለመታገል እጅጉን ቢጠቅመውም፣ አፈ ምላጩን ዐብይን ለመታገል ግን በዚያው ልክ ጎድቶታል፡፡ ጉልቤን የሚረታው ጉልቤ፣ ጮሌን የሚረታው ጮሌ ነው፡፡ ገዱ አንዳርጋቸው ጮሌ ቢሆን ኖሮ፣ ጮሌው ዐብይ አህመድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በሚስማማው መንገድ አበጃጅቶ ከጨረሰ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኔስቴርነትን ሲሰጠው፣ እጅ እግሩ የተሳሰረ፣ ምንም የማይተክር ሥራ ፈት ጡረተኛ ሊደርገው ማሰቡን ተረድቶ እምቢ አሻፈረኝ ባለው ነበር፡፡ በተጨማሪ ደግሞ እሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለማድረግ የፈለገው፣ በሌሎቹ ቁልፍ ሚኒስትሮች ላይ ኦነጋውያንን ያለ ምንም ይሉኝታ መሾም ስለሚያስችለው ብቻና ብቻ መሆኑን በተገነዘበ ነበር፡፡
ጀኔራል አሳምነው ጽጌ በኦነጎችና ለኦነግ ባደሩ ብአዴኖች ጥርስ ውስጥ የገባው የኦነግን ሰይጣናዊ ሽል ማስጨንገፍ የሚቻለው ጎንደር ላይ ሳይሆን ላኮመልዛ (ያሁኒቷ ወሎ) እና ሸዋ ላይ በማትኮር መሆኑን በደንብ ስለተገነዘበና በዚህ ግንዛቤው መሠረት አስፈላጊወቹን እርምጃወች መውሰድ ስለጀመረ ነው፡፡ ወያኔ ወደ ወረቀት ነብርነት ስለተለወጠ፣ ጦቢያዊን (በተለይም ደግሞ አማራን) የሞት ሽረት ትግል የሚጠብቀው ከኦሮሞ ጎጠኞች ጋር ነው፡፡ ስለዚህም ለመጭው የሞት ሽረት ትግል ወሳኞቹ ቀጠኖች ሸዋ፣ ደቡብ ወሎና ምዕራብ ጎጃም እንጅ ጎንደር አይደለም፡፡
የሱማሌን ጅራፍ እየሸሸ ግራኝን እግር በእግር በመከተል ብቻ ያለ ምንም መስዋእትነት ከተስፋፋ ወራሪ የመነጨው፣ በወያኔ አንቀልባ ታዝሎ ስልጣን ኮርቻ ላይ የወጣው፣ የሞት ሽረት ትግል አንዴም አድርጎ የማያውቀው ኦነግ፣ በወኔውና በወታደራዊ ችሎታው እጅግም ባያስፈራም በጭካኔው ግን ጭራቅን የሚያስመሰግን የጭራቆች ጭራቅ ስለመሆኑ አርባጉጉን መጥቀስ ይበቃል፡፡ ዐብይ አህመድ ይህን የጭራቆች ጭራቅ የኦነግ ሚሊሻ በመከላከያ ሠራዊት ስም መረን ለመልቀቅ የፈለገው ደግሞ የምድረገኝ (ያሁኒቷ ከሚሴ)፣ የአጣየ እና የማጀቴ የቅርብ ጊዜ ክስተቶች በመላው ጦቢያ ላይ ለመከስተት ነው፡፡ ባሕርዳር ያደረገውም ይህንኑ ነው፡፡
የዐብይና የለማ አረመኔያዊ አካሄድ ተገትቶ፣ ነፍሰበላው ብርሃኑ ጁላ የጁን አግኝቶ፣ መከላከያ የኦነግ ኢንትራሃምዌ ማሰልጠኛ መሆኑ እስከሚቀር ድረስ፣ አገር ወዳድ ጦቢያውያን (በተለይም ደግሞ አማሮች) ይህን ኢንትራሃምዌ ጦር ለመመከት ብሎም ድባቅ ለመምታት የሚያስችላቸውን ሙሉ አቅም ባስቸኳይ መገንባት አለባቸው፡፡ በተለይም ደግሞ የኢንተራሃሚዌው መሪወች ነጋ ጠባ እንደሚዝቱት የበራራን ጉሮሮ ለማነቅ በሮቿን ቢዘጉ፣ ከበባውን በፍጥነት የሚያስከፍት ልዩ ተወርዋሪ ጦር ተዘጋጅቶ ነቅቶ መጠባበቅ አለበት፡፡ እነዚህን ሁሉ ለማድረግ ደግሞ አማራ ክልል ተብሎ የተሰየመው ባብዛኛው አገር ወዳድ ጦቢያውያን የሚኖሩበት ቀጠና ከበቂ በላይ ክሂሎት አለው፡፡ የጀነራል አሳምነው ጽጌ ኀጢያት አማራን ከኦነግ ጭራቅ ለመከላከል የግድ መሠራት የነበረባቸውን እነዚህን ወሳኝ ሥራወች ለመሥራት በቁርጠኝነት መነሳሳቱ ነበር፡፡ ጀነራል አሳምነው ጽጌ አማራን ለመታደግ የሚደረገውን መራራ ትግል አስከተወሰነ ደረጃ አድርሶት ተሰውቷል፡፡ የቀረውን መፈጸም የኛ ድርሻ ነው፡፡ ዘለዓለማዊ ክብር ለጀነራል አሳምነው ጽጌ፡፡
ኦነጋዊ ግማሽ አማሮች
አብዛኞቻችን አገር ወዳድ ጦቢያውያን በኢተስፋ ላይ በመተሰፍ (hope against hope) የዐብይ እናት አልኦሮሞ (non-oromo) መሆን የዐብይን የኦሮሞ ጎጠኝነት ስሜት ያለዝበዋል የሚል እምነት ነበረን፡፡ ታሪክ የሚመሰክረው ግን የዚህን ተቃራኒ ነው፡፡ በዘር ወይም በብሔር አባልነት የሚጠረጠሩ ግለሰቦች የዘሩ ወይም የብሔሩ አባል መሆናቸውን ለማስመስከር ሲሉ ብቻ የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ ሂትለር ይሁዳወችን የጨፈጨፈበት አንዱ ምክኒያት የይሁዳ ደም አለበት የሚባለውን ጭምጭምታ ለማስተባበል ነበር፡፡ የጌታቸው አሰፋ ፀራማራነት ምንጭ ደግሞ በባቱ በኩል ከፊል አማራ መሆኑ ነው፡፡ ግራኝ ሙሐመድም እንዲሁ፡፡
ዐብይ አህመድን እና ፀጋየ አራርሳን የመሳሰሉ ግማሽ አማራ የኦሮሞ ጎጠኞች በኦሮሞነታቸው ስለሚጠረጠሩ እያንዳንዷ ድርጊታቸው በጢኖፓይፋ (microscope) እንደምትመረመር አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ትንሽ ቢሳሳቱ ግዙፍ ውለታቸው መና ቀርቶ ከሃዲወች እንደሚባሉ ነጋሪ አያስፈልጋቸውም፡፡ እስከጣፈጡ ድረስ ተላምጠው /እንደሚተፉ/ በደንብ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህም እነዚህ ግማሽ ኦሮሞወች ለኦሮሞ ጥቅም ሽንጣቸውን ገትረው የቆሙ መሆናቸው ጥርጣሬ ውስጥ እንዳይገባ ሲሉ ብቻ ከኦሮሞወች የጸነፉ ጽንፈኞች ይሆናሉ፡፡ ከለማበት የተጋባት፡፡ ያብይ አህመድ የባሕርዳር አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የሚመሠክረው ይህነኑ ነው፡፡
ዐብይ አህመድ ለኦነግ ዓላማ መሳካት ሲል ማናቸውንም ጭራቃዊ ድርጊት ለማድረግ ቅንጣት እንደማያቅማማ በባሕርዳር ድርጊቱ በግልጽ ቢያሳይም፣ ግማሽ ኦሮሞ በመሆኑ ብቻ ኦነጋውያን በሙሉ ልብ መቸም ቢሆን አያምኑትም፡፡ ስለዚህም ኦነጋውያን ትናንት ከሚያምኑት የበለጠ ዛሬ እንዲያምኑት ከፈለገ ትናንት ካደረገው የከፋ ዛሬ ማድረግ አለበት፡፡ ስለዚህም አገር ወዳድ ጦቢያውያንን (በተለይም ደግሞ አማሮችን) በተመለከተ የበለጠ እና የበለጠ ጭራቅ እየሆነ ይሄዳል፡፡ ባጭሩ ለመናገር ዐብይ አህመድ በማንነቱ ምክኒያት እኩይ አዟሪት (vicious circle) ውስጥ የገባ የኦነግ አውሬ ነው፡፡ ካዟሪቱ ነጻ የሚያወጣው ሞቱ ብቻ ነው፡፡ ሌሎቹ ግማሽ ኦሮሞ ኦነጋውያንም እንዲሁ፡፡
ሌላ ምሳሌ ለመስጠት ያህል የቡርቃ ዝምታን ምንነት በትክክል የተረዳውን ወያኔን ለረዥም ጊዜ ያገለገለውን አዲሱ አረጋን እንውሰድ፡፡ የቡርቃ ዝምታ ማለት አማራንና ኦሮሞን እሳትና ጭድ በማድረግ የከፋፍለህ ግዛው ዘመኑን ለማራዘም ወያኔ የቀመመው የውሸት ትርክት ማለት ነው፡፡ የትርክቱ ውሸትነት በኦፒዲኦ አባል በግልጽ ተነገረ ማለት ደግሞ የኦነግ የውሸት ትርክት የማዕዘን ዲንጋይ ተፈነቀለ ማለት ነው፡፡ የማዕዘን ዲንጋዩ ተፈነቀለ ማለት ደግሞ የኦነግ ትርክት ሙሉ በሙሉ ተንኮታኮተ ማለት ነው፡፡ የኦነግ የውሸት ትርክት ተንኮታኮተ ማለት ደግሞ የኦነጋውያን እንጀራ ተዘጋ ማለት ነው፡፡
እንጅራቸው /ሊዘጋ/ በመሆኑ ክፉኛ የተደናገጡት ኦነጋውያን አዲሱ አረጋን ከፉኛ በማስደንገጥ ተንበርክኮ ይቅርታ እንዲጠይቅ አስገደዱት፡፡ ይቅርታ መጠየቁ ስላላረካቸው ደግሞ በማንነቱ ላይ መጡበት፡፡ አዲሱ አረጋ ደግሞ በማንነቱ ሊጠረጠር እንደማይገባ ለማሳየት ሲል ብቻ የጽንፈኞች ጽንፈኛ ለመምሰል ሞከረ፡፡ ስለዚህም አዲሱ አረጋ ሐቁን ባወጣ የተቀጣ፣ መናገር ያልፈለገውን እንዲናገር የተገደደ፣ ሊታዘንለት እንጅ ሊታዘንበት የማይገባ የኦነግ እስረኛ ነው፡፡ ከኦነግ እስር ተፈትቶ ቀን ሲወጣለት፣ የኦሮሞ ጽንፈኞችን ለማስደሰት ሲል ብቻ የበለጠ ጽንፈኛ በመምሰል ካንገት በላይ የዘለፈውን እስክንድርን ከልቡ ያወድሰዋል፡፡ የዚያ ሰው ይበለን፡፡
ለማጠቃለል ያህል ዐብይ አህመድ ማለት ያህያ ሥጋ አልጋ ሲሉት ዐመድ ማለት ነው፡፡ አብዛኛው አገር ወዳድ ጦቢያዊ በንግግሩ ብቻ በመማረክ ዐብይን ያለልኩ አግዝፎ ግዙፍ አልጋ ላይ ቢያስቀምጠው፣ ምቾቱ በዝቶበት ወደ ለመደው ኦነጋዊ ዐመዱ ተመለሰ፡፡
ዐብይ አህመድ፣ ዐብይ አህመድ
ያህያ ሥጋ አልጋ ሲሉት ዐመድ፡፡
በተጨማሪ ደግሞ ባመት 365 ቀን፣ በቀን ሃያ አራት ሰዓት የወያኔን ባላንጣወች ሲሰልልና ሲያስሰልል የኖረው ዐብይ አህመድ የዲባቶነት (doctor) ጉላፑን (degree) በተዘረፈ ገንዘብ ካልገዛው በስተቀር በትክክለኛ መንገድ ሊያገኘው አይችልም፣ ዲባቶ ለመባል ባመት 365 ቀን፣ በቀን አስራስድስተ ሰዓት፣ ቢያንስ ለአራት ዓመታት ባላሰለሰ ትጋት መታተርን ይጠይቃልና፡፡ ስለዚህም ዐብይ አህመድ ያለ ማዕረጉ ማዕረግ ተሰጥቶት ዲባቶ መባል የለበትም፡፡ ሌሎቹ የኢህአደግ ዲባቶወች እንደ ዐብይ አህመድ የቁጩ ዲባቶወች ናቸው፡፡ ኧረ ለመሆኑ ወርቅነህ ገበየሁ ሰድረቁን (thesis) ማለትም የመመረቂያ ጽሑፉን በምን ቋንቋ ጻፈው? ይህን የምጠይቀው ለዲባቶነት አጽንኦት ለመስጠት ሳይሆን፣ ዐብይ አህመድና መሰሎቹ የማንነት ቀውስ ያቀወሳቸው ውሸታሞች ለመሆናቸው ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ያህል ብቻ ነው፡፡
ዐብይ አህመድ አሊ የኦነጉ ኦቦ
ሲዋሽ የማያፍር ዓይኑን በጨው አጥቦ፡፡
የባሕርዳር ጭፍጨፋ፣ ያብይ አህመድ አሸብራቂ ድል
ዐብይ አህመድ በግልጽ ጦርነት ያወጀበት እስክንድር ነጋ ባሕርዳር በገባበት ሰዓት የተፈጸመው የባህርዳር አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ያብይ አህመድ ሤራ መሆኑን የማይረዳ ግለሰብ፣ በቅርበት ተጠጋግተው በቀጥታ የተደረደሩ ነጥቦችን በቀጥታ መስመር ማገናኘት የማይችል ሕጻን ወይም ሕጹጽ መሆን አለበት፡፡ የመረጃ ምንጮችን ሁሉ ዘጋግቶ ትክክለኛ መረጃ እስከሚወጣ ድረስ ተረጋጉ የሚባለው ተረት ደግሞ ሁለተኛው የዐብይ አህመድ ሤራ ነው፡፡ የዚህ ሤራ ዓላማ ደግሞ ገሃዱን ሐቅ የሚያድበሰብሱ ጭፍጨፋውን የሚመለከቱ በርካታ መላምቶች እስከሚመለመቱ ድረስ ጊዜ ለመስጠት ነው፡፡ ንጉሡ ጥላሁን ጭፍጨፋው እየተካሄደ ባለበት ሰዓት በሙሉ እርግጠኝነት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው ካለ በኋላ ድምጹ የሚጠፋበት ሌላ ምንም ምክኒያት የለውም፡፡
ከአምባቸው መኮንን በተጨማሪ ዐብይ አህመድ ዐብይ አህመድ የረሸነው ወይም ያስረሸነው የምድረገኝ (ያሁኒቷ ከሚሴ)፣ የአጣየ እና የማጀቴ ኦነጋዊ ጭራቆችን ባስቸኳይ እንዲፈታ በዐብይ አህመድ የተሰጠውን ቀጭን ትእዛዝ አለቀበልም ያለው ያማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ ነው፡፡ ሌላው የዐብይ ጭፍጨፋ ሰለባ ደግሞ የአማራ ክልል የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ የነበረውን አቶ አዘዘ ዋሴን መሆኑ በደንብ መጤን አለበት፡፡ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ የሚለው ሊደምቅና ሊሰመርበት ይገባል፣ የኦጋውያን በተለይም ደግሞ የቀጣፊው ዐብይ አህመድና የመሠሪው ለማ መገርሳ ትልቁ ፍራቻ የአማራ መደራጀት ነውና፡፡
ዐብይ አህመድ ሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም (June 22, 2019) ባሕርዳር ላይ የተጎናጸፈው ድል፣ ግራኝ ሙሐመድ መጋቢት 1522 ዓ.ም (March, 1529) ሽምብራ ቁሬ (ማለትም የሽምብራ ኩሬ ወይም ያሁኒቷ ዱከም) ላይ ከተጎናጸፈው ቢልቅ እንጅ አያንስም፡፡ የግራኝ አህመድ ድል ለገዳ ተስፋፊ በር እንደከፈተለት፣ የዐበይ አህመድ ድል ደግሞ ለኦነግ ተስፋፊ በር ከፍቶለታል፡፡ ኦነግ የፈለገውን ሁሉ በፈለገው ሰዓት፣ በፈለገው ቦታ፣ በፈለገው ዘዴ ማድረግ ይችላል፡፡ ጥያቄው ያደርገዋል አያደርገውም ሳይሆን፣ ማድረጉ ያዛልቀዋል አያዛልቀውም ነው፡፡
ባሕርዳር ላይ በተጎናጸፈው አሸብራቂ ድል የተኩራራው ዐብይ አህመድ፣ የግራኝ ሙሐመድን ፈለግ በመከተል የጦቢያን (በተለይም ደግሞ ያማራን) ትውፊቶች በያሉበት እየሄደ መዝብሮ፣ አርክሶ፣ አቃጥሎ ይደመስሳቸው ይሆናል፣ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡ ባንድ ነገር ላይ ግን መጠራጠር የለብንም፡፡ በተለያዩ ጊዜወች ሞተ ሲባል አፈር ልሶ የተነሳው ያማራ ሕዝብ ለገራኝ አህመድ ያጠጣውን ጽዋ፣ ለዐብይ አህመድም ያጠጣዋል፡፡ ግራኝ በር በጎንደር ዐብይ በር ባንኮበር፡፡
መስፍን አረጋ